1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሲሰረዝ ዜጎቿ ኤኮኖሚው ያንሰራራል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2016

ሶማሊያ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ በተሰረዘላት በሣምንቱ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 100 ሚሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት ጸድቆላታል። የሶማሊያ የውጭ ብድር ከ5.3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ መንግሥት እና የሶማሊያ ዜጎች የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ያንሰራራል የሚል ተስፋ አላቸው።

https://p.dw.com/p/4aMSC
ሶማሊያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብን በይፋ የተቀላቀለችበት መርሐ ግብር
ሶማሊያ ባለፉት ጥቂት ሣምንታት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ስምንተኛ አባል ሀገር ሆናለች፤ ለረዥም ዓመታት ተጥሎባት የቆየው የጦር መሳሪያ ግዢ ማዕቀብ በጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ተነስቶላታል። የሀገሪቱ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንዲሰረዝም ተወስኗል። ምስል Presidential Press Unit Uganda

ሶማሊያ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ከተሰረዘላት በኋላ 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ጸድቆላታል

ሶማሊያ ተግባራዊ ለምታደርገው ኤኮኖሚያዊ ማሻሻያ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) 100 ሚሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት አጽድቋል። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተቋም ትላንት ማክሰኞ ታኅሳስ 8 ቀን 2016 ካጸደቀው ብድር ውስጥ 400 ሚሊዮን ዶላር በአፋጣኝ ለበጀት ድጋፍ የሚለቀቅ ነው። ለሦስት ዓመታት የሚዘልቀው የተራዘመ የብድር አቅርቦት የጸደቀው ሶማሊያ ለረዥም ዓመታት ሰቅዞ ከያዛት የዕዳ ጫና ፋታ ባገኘች በሣምንቱ ነው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ ባለፈው ሣምንት ለሶማሊያ የ4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ስረዛ አጽድቀዋል። ውሳኔው የሶማሊያን የውጭ ዕዳ ከ5.3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያወርደዋል። የሶማሊያ አበዳሪዎች የወሰዱት እርምጃ ለፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ መንግሥት ከፍ ያለ እፎይታ የሚሰጥ ነው።

“ይኸ ሒደት ከአስር ዓመታት በላይ ወስዷል። የተሳካው በበርካታ ተከታታይ የሀገሪቱ መሪዎች እና መንግሥታት ጥረት ነው” ያሉት ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ “በስተመጨረሻ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሀገሪቱን ዕዳ ሰርዘዋል። አሁንም ሊሰረዝ የማይችል የተወሰነ ቀሪ ዕዳ አለብን። ነገር ግን ሒደቱን በመከተል ደረጃ በደረጃ መልሰን እንከፍላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ለፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ እና ለመንግሥታቸው ታላቅ እፎይታ የሰጠው የዕዳ ስረዛ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ይጽደቅ እንጂ በርከት ያሉ አበዳሪዎች የተካተቱበት ነው። በዓለም ባንክ ሥር የሚገኘው ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር 448 ሚሊዮን ዶላር፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 343 ሚሊዮን ዶላር በመሰረዝ ቀዳሚ ናቸው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፈንድ 131 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ለሶማሊያ የሰረዘ ሲሆን ፓሪስ ክለብ፣ የግል አበዳሪዎች እና የአረብ ሀገራት ጭምር በድምሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ለሶማሊያ ሰርዘዋል። በጎርጎሮሳዊው 2018 ከሶማሊያ አጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን (GDP) 64 በመቶ የነበረው ዕዳ ወደ 6 በመቶ ዝቅ ብሏል።

የሶማሊያ የፋይናንስ ሚኒስትር ቢሒ ኢግሔ ሀገራቸው ተግባራዊ በምታደርገው ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ መርሐ ግብር መሠረት የተደረገላትን የዕዳ ስረዛ “የተለየ የስኬት ታሪክ” ሲሉ ይገልጹታል። “ባለፉት 30 ዓመታት በጣም ከባድ ጊዜ አሳልፈናል” የሚሉት የፋይናንስ ሚኒስትሩ የዕዳ ስረዛ ሒደቱ ሲጀመር ሶማሊያ ከውድቀት አፋፍ ይገኝ የነበረውን መንግሥታዊ መዋቅር መልሳ የመገንባት ውጣ ውረድ ላይ እንደነበረች ያስታውሳሉ።

የዕዳ ስረዛው ከጸደቀ በኋላ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉት ቢሒ ሶማሊያ ፈታኝ ተግዳሮቶች ቢገጥሟትም በተከታታይ ሥልጣን የያዙ መንግሥታት ለሒደቱ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ከማድረግ እንዳላፈገፈጉ ተናግረዋል። 

የሶማሊያ የፋይናንስ ሚኒስትር ቢሒ ኢግሔ “በዚህ ሒደት ውስጥ ከባድ ተግዳሮቶች ቢገጥማቸውም የማሻሻያ መርሐ-ግብሩን ያስቀጠሉ ሦስት ተከታታይ አስተዳደሮች አይተናል። የኮቪድ ወረርሽኝ ገጥሞን ነበር። ባለፉት አስር ዓመታት የሶማሌ ሕዝብን የጎዱ ተደጋጋሚ የከባቢ አየር ለውጥ አደጋዎች አስተናግደናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የፋይናንስ ሚኒስትሩ “ሁለት ፕሬዝደንታዊ፣ ሦስት ምክር ቤታዊ ምርጫዎች አልፈናል። የሕዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ያወደመ የአንበጣ መንጋ አስተናግደናል። ይኸ ሁሉ ፈተና ቢገጥመንም የሶማሊያ መንግሥት የማሻሻያውን ፍጥነት አስቀጥሎ ቆይቷል” ሲሉ አድንቀዋል።

ሶማሊያ ዕዳዋ በዚህ መጠን እንዲቀንስ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ከ27 ዓመታት በፊት በጀመሩት ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው ሀገሮች ኢንሺየቲቭ (Heavily Indebted Poor Countries (HIPC) Initiative) ጥብቅ ሒደት ውስጥ ማለፍ ነበረባት።

የሶማሊያ ድርቅ
ሶማሊያ ባለፉት ዓመታት ተከታታይ እና ብርቱ ድርቅ ስትጋፈጥ ቆይታለች። ምስል Mulugeta Ayene/UNICEF/AP/picture alliance

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሀ ሀገሮች ያለባቸውን የዕዳ ጫና በዚህ ኢንሺየቲቭ እንዲሰረዝላቸው በርከት ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። ሶማሊያ የመንግሥት ወጪ፣ የግብር አሰባሰብ፣ አስተዳደር እና ድሕነት ቅነሳን ጨምሮ በሒደቱ ከተቀመጡ አስራ አራት ቅድመ-ሁኔታዎች አስራ ሦስቱን ተግባራዊ አድርጋለች።

ሶማሊያ በዚህ ረዥም እና ውስብስብ ሒደት የዕዳ ስረዛ እንዲደረግላት ጉዞ የጀመረችው የርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭት፣ የአል-ሸባብ ጥቃት እና የከባቢ አየር ለውጥ እየተፈታተኗት በሚገኙበት ወቅት ነበር። በዓለም ባንክ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ ሒደቱ ተጠናቆ መሥሪያ ቤታቸው ዕዳ መሰረዙን ይፋ ሲያደርግ ለሶማሊያ “አዲስ ምዕራፍ” ተከፈተ ነበር ያሉት።

ቪክቶሪያ ክዋክዋ “ዛሬ ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው ሐገሮች ኢንሺየቲቭ ሲጠናቀቅ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ የምርት መጠን 70 በመቶ የነበረው የሶማሊያ ዕዳ ወደ 6 በመቶ ይቀንሳል” ሲሉ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ ገልጸዋል። 

“ይህ ለሕዝቧ አስፈላጊ አገልግሎቶች እንድታቀርብ፤ የከባቢ አየር ለውጥ ዳፋን እንድትቋቋም እና ኤኮኖሚያዊ ዕድገትን እንድታፋጥን የሚያስችል ገንዘብ የምታገኝበትን ዕድል ይከፍታል። እነዚህ በሙሉ ድሕነትን ለመቀነስ እና የሀገሪቱን የመፍረስ አደጋ ለማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ናቸው” ሲሉ ላቅ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያጸደቁት የዕዳ ስረዛ በየርስ በርስ ጦርነት እና ሽብርተኝነት ስትፈተን የቆየችው ሶማሊያ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት እንድትመለስ መንገድ የሚጠርግ ነው። ሶማሊያ ኤኮኖሚዋን ለማጠናከር፣ ድህነትን ለመቀነስ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከዓለም አቀፍ ተቋማት ተጨማሪ ገንዘብ እንድታገኝ ያስችላታል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የመካከለኛው ምሥራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር ጂሐድ አዙር የሀገሪቱ ዕዳ መሰረዝ “የሶማሊያ ሕዝብ ሐብት እና ሥራ የሚፈጥር መዋዕለ-ንዋይ እንዲያበጅ ዕድል ይፈጥራል። ይኸ ዕድል እንደ ድሕነት ሥር ለሰደዱ ችግሮች መፍትሔ ለመፍጠር ያግዛል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ከሶማሊያ ሕዝብ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው በቀን ከ2 ዶላር በታች በሆነ ገቢ የሚተዳደር ነው። አሁን ለዚህ ድሕነት መፍትሔ ለማበጀት፣ የማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተቋማትን ማዕቀፍ ለማጠናከር ዕድል አግኝተናል” ያሉት ጂሐድ አዙር “ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታም ለማሻሻል ይረዳል። ምክንያቱም ያለ ጸጥታ ልማት ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ
የቀድሞው ፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ ከሥልጣን ተወግደው ሶማሊያ እልም ያለ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች በኋላ ላለፉት 32 ዓመታት ገደማ የመገበያያ ገንዘብ አላተመችም። ምስል picture-alliance/dpa

በገንዘብ መመንዘር ሥራ የሚተዳደረው ኢብራሒም ሐሰን አብዲ የሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ነዋሪ ነው። ብዙ ግን ደግሞ አሮጌ የሶማሊያ ሺልንግ ፈጠን ፈጠን እያለ የሚቆጥረው ኢብራሒም ሐሰን አብዲ “ኤኮኖሚያችን ሲሻሻል ልናይ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን። ይህ ከከባድ ሸክም ይገላግለናል” ሲል ተስፋውን ተናግሯል።

ሶማሊያ እልም ያለ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባችበት ከጎርጎሮሳዊው 1991 በኋላ ባለፉት 32 ገደማ ዓመታት የመገበያያ ገንዘብ አላተመችም። በሥራ ላይ የነበረው አብዛኛው የመገበያያ ገንዘብ ደብዛው ጠፍቷል አሊያም እጅግ አርጅቷል። በገበያው የሶማሊያ ሽልንግ አንድም በአሜሪካ ዶላር ወይም ከሀገሪቱ መገንጠል በሚሹ ግዛቶች በነጋዴዎች እና በጦር አበጋዞች በታተመ ሐሰተኛ ገንዘብ ተተክቷል።

አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ማተም ባለፉት ዓመታት የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ ተቀዳሚ ዓላማ ነበር። ይኸን ዕቅድ ማሳካት እንደ አብዱልቃድር ሞሐመድ ሮብሌ ያሉ ነጋዴዎች በጉጉት የሚጠብቁት ነው።

“በተደረገው የዕሳ ስረዛ በጣም ተደስተናል። ምክንያቱም የመገበያያ ገንዘባችን ደቅቋል” ያሉት አብዱልቃድር ሞሐመድ ሮብሌ “ሶማሊያ ለ32 ዓመታት ገደማ የመገበያያ ገንዘብ አላተመችም። የሀገሪቱን ኤኮኖሚ ለማሳደግ የሚረዳ እና በቅጡ የሚሰራ የመገበያያ ገንዘብ ሊኖረን ስለሚችል ከዕዳ ስረዛው ተጠቃሚ መሆን እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል። 

“የመገበያያ ገንዘባችን አርጅቷል” የሚሉት አብዱልቃድር ሞሐመድ ሮብሌ “አሁን በመላው ዓለም ተቀባይነት የሚኖረው አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ያስፈልገናል” የሚል አቋም አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ጉሌሕ፣ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ እና ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ በሞቃዲሾ
የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ መንግሥት አል-ሸባብን ለማጥፋት በጀመረው ውጊያ በቀጥታ ከሶማሊያ ከሚጎራበቱ ሀገሮች ጋር ጥምረት ፈጥሯል። ምስል Ethiopian PM Office

የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ በጎርጎሮሳዊው 2024 አጋማሽ አራት የተለያየ መጠን ያላቸው የመገበያያ ገንዘቦች ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ባንኩ ይኸ እርምጃ በገበያው የሚገኘውን ሐሰተኛ የመገበያያ ገንዘብ ገፍቶ ያስወጣል የሚል ተስፋ አለው። ከዚህ በተጨማሪ በገበያው ውስጥ የሚዘዋወረውን ገንዘብ መቀነስ እና የዋጋ ንረትን መቆጣጠር የባንኩ ዓላማዎች ናቸው።

ከተሳካ ይኸ የሶማሊያ ማዕከላዊ ባንክ የሀገሪቱን የሞነታሪ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር አቅም ይፈጥርለታል። እንደ አሊ አብዲ ያሉ የሀገሪቱ ዜጎች ግን የሶማሊያ ዕዳ ሲሰረዝ ከዚህ ከፍ ያለ ለውጥ ይፈጥራል ብለው ይጠብቃሉ።

አሊ አብዲ “ሶማሊያ ከዚህ ግዙፍ የዕዳ ሥረዛ ተጠቃሚ ትሆናለች። ሶማሊያ አሁን የራሷን የመገበያያ ገንዘብ ማተም ትችላለች። ኤኮኖሚው ይሻሻላል። እንደ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ መሠረተ-ልማቶች መገንባት እንችላለን” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

አል-ሸባብን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ ላይ የሚገኘው የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ መንግሥት ባለፉት ወራት ተደጋጋሚ በጎ በጎ ዜናዎች ገጥመውታል። ሀገሪቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተጥሎባት የቆየው የጦር መሣሪያ ግዢ ማዕቀብ ተነስቶላታል።

በመጪው ዓመት በሶማሊያ የሠፈረው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ በከፍተኛ ቁጥር ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ሣምንት ደግሞ በይፋ ስምንተኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል ሆናለች።

አበዳሪዎቿ ሶማሊያ መክፈል የተሳናትን ዳጎስ ያለ ዕዳ ሲሰርዙ የፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ መንግሥት እና የሀገሪቱ ዜጎች ድሕነትን በመቀነስ ኤኮኖሚውን የማሳደግ ውጥን አላቸው።

እሸቴ በቀለ