በሶማሌ ክልል ጎርፍ ሰዎች ገደለ፣ ሺዎችን አፈናቃለም
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27 2016
በሶማሌ ክልል ባለፉት ተከታታይ ቀናት የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ በትንሽ ግምት 24 ሰዎች ገደለ፣ ሌሎች ከ40 ሺሕ በላይ ጎዳ፣ ሺዎችን አፈናቀለ።የክልሉ አደጋ ስጋት ቅነሳ ፅ/ቤት እንዳስታወቀዉ በተከታታይ የጣለዉ ዝንብ በክልሉ 8 ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎችን አጥለቅልቋል።የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በአደጋዉ የተጎዱትን አካባቢዎች ዛሬ ጎብኝተዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት በክልሉ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር የሚያመልክተው የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ችግሩን እንዳያባብስ ተሰግቷል።በሶማሌ ክልል አደጋ መከላከል ቢሮ የቅድመ መከላከል ቡድን መሪ አቶ በሽር አረብ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሲጥል በቆየው ዝናብ ሳቢያ የተከሰተ ጎርፍ እና የወንዝ ሙላት ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሃያ አራት መድረሱን እንዲሁም ሃያ ሶስት ሺህ አባወራዎች መፈናቀልቸውን ገልፀዋል።
በክልሉ ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች በስምንት የተከሰተው ችግር በተለያየ መጠን ጉዳት ማድረሱን የጠቀሱት አቶ በሽር አስቀድሞ ሲደረግ በቆየው ዝግጅት የነፍስ አድን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል ።በብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰረት ቀጣዮቹ ቀናት በክልሉ ዝናብ የሚጠበቅበት መሆኑን አመላካች መሆኑ ስጋት የሚፈጥር መሆኑንም ቡድን መሪው ተናግረዋል።በአካባቢያቸው የተከሰተው ጎርፍ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መግባቱን የገለፁት የጎዴ አካባቢ ነዋሪው አቶ ሻፊ በርካታ ቤቶች በውሀ መጥለቅለቃቸውን ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።
አቶ ሻፊ ጎርፉ በንብረት እና በመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማስከተሉንም ጠቅሰዋል።ጉዳቱን ተከትሎ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች እየጎበኘ መሆኑ ተገልፆል።
መሳይ ተክሉ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ