1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ በሁለት ወራት ገደማ የመጨረሻውን ሥምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2016

ለሶማሌላንድ እውቅና ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር በኪራይ የሚሰጠው ሥምምነት በሁለት ወራት ገደማ ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይል የጦር ሠፈር ልትከራይ የምትችላቸው ሦስት አማራጭ ቦታዎች መለየታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4fJoS
የሶማሌላንድ የባሕር ዳርቻ
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በሶማሌላንድ በኪራይ የጦር ሠፈር ሊያቋቁምባቸው የሚችል ሦስት ሥፍራዎች በአማራጭነት መለየታቸውን የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ በሁለት ወራት ገደማ የመጨረሻውን ሥምምነት ይፈራረማሉ ይጠበቃል

የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ዲፕሎማቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈራረሙት “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” በመጪዎቹ ወራት ወደ ተግባር ይሸጋገራል ብለው እየጠበቁ ነው።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ከአራት ወራት በፊት ታህሳስ 22 ቀን 2016 ሲፈረም ድርድሩ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ የመግባቢያ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን እና የቴክኒክ ኮሚቴዎች መታጨታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ነበር” ያሉት ዶክተር ኢሳ ካይድ በረመዳን የጾም ወር ወቅት ሒደቱ ቢቀዛቀዝም በመጪዎቹ ወራት ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ሥምምነቱን ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የመጨረሻውን ሥምምነት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“ሁሉም ነገር ሁለቱ ቡድኖች በሥምምነቱ ላይ ለመደራደር ሲገናኙ ይወሰናል” ያሉት ዶክተር ኢሳ “የሕግ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች አሉ። በመጪዎቹ ወራት ምን አልባትም በሁለት ወራት ገደማ ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሶማሊላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ
ሥምምነቱ ተፈርሞ ሶማሌላንድ የምታገኘው እውቅና ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ ሥምምነቱ ተፈርሞ “ዕውቅና ስናገኝ በዓለም አቀፍ መድረክ ድምጽ ስለሚኖረን በፖለቲካ ረገድ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ተስፋቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ሶማሌላንድ የምታገኘው ዕውቅና “ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድ፣ ለጉዞ እና በዕድገት በር ስለሚከፍት በኤኮኖሚ ረገድ ጠቃሚ ይሆናል” የሚሉት የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሶማሌላንድ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት እንድትተሳሰር ይረዳታል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

“ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ መበደር እንችላለን” ሲሉ የተናገሩት ዶክተር ሳዓድ አሊ “በዕውቅናው ምክንያት እጅግ በርካታ በሮች” ለሶማሌላንድ እንደሚከፈቱ ይጠብቃሉ።

ሥምምነቱ ከተፈረመ ሶማሌላንድ ዕውቅና ስታገኝ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር የምታቋቁምበትን ወደብ በኪራይ ታገኛለች። ሶማሌላንድ 850 ኪሎ ሜትር ገደማ በሚረዝመው የባሕር ዳርቻ ኢትዮጵያ ልትከራይ የምትችልባቸውን ሦስት ቦታዎች በአማራጭነት መለየታቸውን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ አረጋግጠዋል።

“የለየናቸው የተወሰኑ ቦታዎች አሉ። ከኢትዮጵያ አቻዎቻችን ጋር ከተገናኘን በኋላ አንዱ ይመረጣል” ያሉት የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተለዩትን ሦስት ቦታዎች ስሞች ከመናገር ተቆጥበዋል።

ኢትዮጵያ የደርግ ሥርዓተ መንግሥት ወድቆ ኤርትራ ነጻነቷን ስታውጅ የፈረሰውን የባሕር ኃይል መልሳ ያቋቋመችው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረንሳይ እና የቀድሞ የባሕር ኃይል መኮንኖች ድጋፍ የባሕር ኃይሉን በአዋጅ መልሶ ያቋቋመው በ2011 ነበር።

የሶማሌላንድ ዋና ከተማ ሐርጌይሳ
በሐርጌይሳ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ በተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ዕውቅና እንደምታገኝ ከፍ ያለ ተስፋ አለ። ምስል Eshete Bekele/DW

ለሶማሌላንድ የመጀመሪያውን ዕውቅና የሚሰጠው ሥምምነት ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በ50 ዓመታት ኪራይ የጦር ሠፈር እንዲያገኝ ያደርጋል። ዶክተር ኢሳ እንደሚሉት “ሁለት የተለያዩ ነገሮች አይደሉም። እርስ በርስ የተገናኙ ሁለት ነገሮች ናቸው።”

“የኪራይ ሥምምነቱን ለመፈራረም ስንስማማ በተመሳሳይ ጠረጴዛ እና በተመሳሳይ ቀን ለሶማሌላንድ ዕውቅና የሚሰጠው የኢትዮጵያ አዋጅ ወዲያው መከተል አለበት” ሲሉ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ሶማሌላንድ ነጻነቷን ያወጀችው ከ33 ዓመታት በፊት ማለትም በጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 18 ቀን 1991 ነበር። ይሁንና እስካሁን ድረስ ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘችም።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ለሶማሌላንድ እውቅና እንደሚሰጥ በይፋ አላረጋገጠም። ዶይቼ ቬለ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።

የመግባቢያ ሥምምነቱ “በሒደት ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብ” እንደሚያካትት የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት አስታውቆ ነበር።

በመግባቢያ ሥምምነቱ ረገድ “አዲስ ወይም የተቀየረ ነገር” አለመኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምት ኢትዮጵያ ለንግድ አገግሎት የሚውል ወደብ (commercial maritime) እንዲኖራት የሚፈቅድ መሆኑን በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ የነበሩት ሬድዋን ሑሴይን ተናግረው ነበር።

የሶማሌላንድ በርበራ ወደብ
የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ዶክተር ሳዓድ አሊ ሽሬ ግን የበርበራ ወደብ “የኢትዮጵያን ነጋዴዎች እና መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች እንዲጠቀሙበት ክፍት ይሆናል። ስለዚህ ሌላ ወደብ መገንባት አያስፈልግም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ዶክተር ሳዓድ አሊ ሽሬ ግን የበርበራ ወደብ “የኢትዮጵያን ነጋዴዎች እና መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች እንዲጠቀሙበት ክፍት ይሆናል። ስለዚህ ሌላ ወደብ መገንባት አያስፈልግም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ሥምምነት የሶማሊያ መንግሥትን በኃይል ያስቆጣ፤ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብም ያሳሰበ ጉዳይ ነው። የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ማሕሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው ሥምምነት የሶማሊያን አካል ልትገነጥል ነው ሲሉ ወንጅለዋል። መንግሥታቸው የመግባቢያ ሥምምነቱን “የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ” ብሎታል።

የቡድን ሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ሣምንት በጣልያኗ ካፕሪ ደሴት ያደረጉትን ስብሰባ ሲያጠናቅቁ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ሥምምነት እንደሚያሳስባቸው ሥጋታቸውን ገልጸዋል። ሶማሊያ እና ኢትዮጵያም በመግባቢያ ሥምምነቱ ምክንያት በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት በውይይት እንዲያረግቡ አበረታተው ነበር።

“ሶማሌላንድ ሉዓላዊ ሀገር ሉዓላዊ መንግሥት ናት። በዚህም ከፈለግንው ሀገር ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ማበጀት እና ሥምምነት መፈራረም እንችላለን” የሚሉት የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር ኢሳ ግን የሶማሊያ ተቃውሞ እንቅፋት ይሆናል የሚል ሥጋት የላቸውም።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ማሕሙድ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ማሕሙድ እና መንግሥታቸው ጠንካራ ተቃውሞ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ውል ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ሥጋት የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር የላቸውም። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

“ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ እና ቡድናቸው ወደ ተለያዩ ሀገሮች እና የተለያዩ አጋሮች በመሔድ የመግባቢያ ሥምምነቱ ውድቅ እንዲሆን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን እናውቃለን። ነገር ግን ያንን ማድረግ የሚችሉበት አንዳች ዕድል አለ ብዬ አላስብም” ሲሉ ዶክተር ኢሳ የሶማሊያ ፌድራል መንግሥት ጥረት እንደማያሳስባቸው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን የጦር ሠፈር ልትመሠርትበት የምትችለው የኤደን ባሕረ ሰላጤ በሕገ- ወጥ መንገድ ተረፈ ምርት እና ዝቃጭ የሚደፋበት ለመሆን እንደበቃ ዶክተር ኢሳ ሳይድ ይናገራሉ። የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትሩ እንደሚሉት አካባቢው የባሕር ላይ ውንብድና፣ ሕገ-ወጥ የአሳ ማስገር ሥራ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የዱር እንስሳት ዝውውር ጨምሮ በርካታ ችግሮች በርትቶበታል። 

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በሶማሌላንድ የባሕር ዳርቻ በኤደን ባሕረ ሰላጤ የጦር ሠፈር ሲኖረው ችግሮቹን ለመቆጣጠርና ለማቃለል ተጨማሪ ዋስትና እንደሚሰጥ ዶክተር ኢሳ ካይድ ገልጸዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ