1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቃለ መጠይቅ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስና የድርድር ሐሳብ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 14 2014

በአካባቢዉ የሚታየዉ የሠላም መድፈረስ ገና ቅርፅ ያልያዘዉን የድርድር ሐሳብ ያስተጓጉለዋል የሚል አስተያየት አስከትሏል።ድርድር ጨርሶ አያስፈልግም የሚሉ ወገኖችም አሉ።በጦርነቱ የተሳተፉት ወገኖች በርካቶች በመሆናቸዉ ሁሉንም የሚያረካ ድርድርና ስምምነት መደረጉም ብዙዎችን እያጠራጠረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4D1qR
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed im Parlament
ምስል Solomon Muche/DW

«ድርድሩ ከተጀመረ (የተፋላሚ ኃይላት) አቋም ሊለዝብ ይችላል---» ዶክተር አደም ካሴ



የኢትዮጵያ መንግስትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሪዎች ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸዉን ባለፈዉ ሳምንት በየፊናቸዉ አስታዉቀዋል።ሁለቱ ወገኖች ባለፈዉ መጋቢት ያወጁት የሰብአዊነት ተኩስ አቁም ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ባይሆንም አሁንም  እንደተጠበቀ ነዉ።ይሁንና ሁለቱ ወገኖች የሚያደርጉት ወታደራዊ ዝግጅት አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።አንዱ ሌላዉን ማዉገዙና ማሳጣቱም ቀዝቀዝ ከማለት በስተቀር ሙሉ በሙሉ አልቆመም።ከዚሕ በተጨማሪ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ከተሞች የሚደረገዉ ግጭት፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመዉ ዘርን መሰረት ያደረገ ግድያና ጥቃት መደጋጋሙ የድርድሩን ተስፋ ያጨልመዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።
ባለፈዉ ሳምንት ጋምቤላ፣ ደምቢዶሎና ጊምቢ ዉስጥ የብዙ ሰዉ ሕይወት ያጠፋዉን ዉጊያ  የጫረዉ ከሕወሓት ጋር የጋራ ትብብር የመሰረተዉ የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም መንግስት ኦነግ ሸኔ የሚለዉ አማፂ ቡድን እንደሆነ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።በሳምንቱ ማብቂያ ጊምቢ አጠገብ በመቶ የሚቆጠሩ በአብዛኛዉ ሰላማዊ የአማራ ተወላጆችን በመደዳ የጨፈጨፈዉም የኦሮሞ ነፃነት ጦር (ኦነግ ሸኔ) እንደሆነ እየተዘገበ ነዉ።
በአካባቢዉ የሚታየዉ የሠላም መድፈረስ ገና ቅርፅ ያልያዘዉን የድርድር ሐሳብ ያስተጓጉለዋል የሚል አስተያየት አስከትሏል።ድርድር ጨርሶ አያስፈልግም የሚሉ ወገኖችም አሉ።በጦርነቱ የተሳተፉት ወገኖች በርካቶች በመሆናቸዉ ሁሉንም የሚያረካ ድርድርና ስምምነት መደረጉም ብዙዎችን እያጠራጠረ ነዉ።የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ቀዉስና የድርድሩን ሐሳብ በሚመለከት የዓለም አቀፉን የዲሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ሰጪ ተቋም (IDEA-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ባልደረባ ዶክተር አደም ካሴን አነጋግረናል።ሙሉዉን ቃለ ምልልስ እነሆ፣-

ነጋሽ መሐመድ