ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት በተለይ በኦሮሚያ ክልል ዉጊያና በጎሳ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነበር።ዉጊያና ጥቃቱ በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ወቅትና በኋላም ቀጥሏል።የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ዉል ካበቃ በኋላ ደግሞ በአማራ ክልል ሌላ ግጭት ተቀስቅሷል።የፕሪቶሪያዉ ስምምነት የተፈረመበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ማብቂያ ያጣዉን የኢትዮጵያ ግጭትና ምሥቅልቅልን አንስተን ከቀድሞዉ የኢሕአፓ ታጋይ፣ የኢሕዴን መሥራችና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገናል።
ከሁለት ዓመቱ ጦርነት ያተረፉት የኤርትራ መሪ ናቸዉ
አንዳዴ የትግራይ ጦርነት፣ ሌላ ጊዜ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የሚባለዉ ዉጊያ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ ዉድመት አስከትሏል።በመላዉ ኢትዮጵያ ብዙ ጥፋት ደርሷል።በአንዳዶች ግምት አንድ ሚሊዮን ያክል ሕዝብ ተገድሏል፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አፈናቅሏል፤ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሐብትና ንብረት ወድሟል።
የቀድሞዉ የኢሕአፓ ታጋይ፣ የኢሕዴን መስራችና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ እንደሚሉት ከአዉዳሚዉ ጦርነት ያረፈ ወገን ካለ «የኤርትራዉ መሪና መንግሥታቸዉ ብቻ ናቸዉ።»
ተጠያቂዉ ማነዉ?
ሥለጦርነቱ መነሻ እስካሁን ድረስ በግልፅ የወጡት መረጃዎች የሚቃረኑ ናቸዉ።ተፋላሚ ኃይላት በየፊናቸዉ የሚሰጧቸዉ ምክንያቶች አሉ።እስካሁን ሥለጦርነቱ መነሻ በገለልተኛ ወገን የተደረገ ጥናት ወይም ይፋ የሆነ መረጃ የለም።በዚሕም ምክንያት ለጦርነቱ መጫርና ላደረሰዉ ጥፋት ተጠያቂ የሚባል ወገንን ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነዉ።
«አንድ የሚያሳዝነዉ ነገር---የፕሪቶሪያዉም ሥምምነት ብዙም ትኩረት ያልሰጠዉ የጦርነቱ መንስኤ ምን ነበር? ማነዉ ትክክለኛዉ ተጠያቂዉ-----ተስማሚዎቹ ሁለቱ ወገኖች (የጦርነቱ ዋና አራማጆች) ሥለሆኑ ተጠያቂነትን ለማንሳት የፕሪቶሪያ አመቺ አልነበረም---ሥንት ሰዉ ሞተ የሚለዉ እንኳ ተጠንቶ---»
የፕሪቶሪያ ሥምምነት
በፕሪቶሪያዉ ሥምምነት መሠረት አዉዳሚዉ ጦርነት ቆሟል።የጦርነቱ መቆም ድፍን ሁለት ዓመት ፍዳዉን ሲያይ ለነበረዉ ሕዝብ እፎይታ ነዉ።ይሁንና ሥምምነቱ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም።«በኔ በኩል በሁለቱም ወገን ነዉ ችግር ያለዉ የሚመስለኝ----ምዕራቦች ባንድ በኩል ግፊት የሚያደርጉ ይመስላሉ----ግን ተ,ጨባጭ ርምጃ ለማስወድ---»
የድሕረ ጦርነት-ጦርነትና የሰላም ዉል ማግሥት ጦርነት
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ኦሮሚያ ዉስጥ የሸመቁት መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚላቸዉ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ታጣቂዎች ከመንግሥት ኃይላት ላይ የገጠሙት ዉጊያ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላም እንደቀጠለ ነዉ።የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት ከቆመ በኋላ ደግሞ አማራር ክልል ዉስጥ የሸመቁ የፋኖ ኃይላት ከመንግሥትና ከደጋፊዎቹ ኃይላት ጋር እየተዋጉ ነዉ።
በየአካባቢዉ የሚፈፀመዉ ግድያ፣ እገታና ዘረፋም ተባብሶ ቀጥሏል።ሰዎች በሰላም ወጥተዉ መግባት፣ ሠርተዉ መኖር አልቻሉም።የዚሕ ምሥቅልቅል ምክንያት ምን ይሆን? መቆሚያስ አለዉ?
«ሁሉ ዓይነት የጥፋት ኃይሎች አንገታቸዉን ያቀኑበትና ሐገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አደጋ እየገባች የምትሔድበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ---ጥጋብና ማንአለብኝ ስሜት እየገነገነ
ሙሉ ቃለ ምልልሱን ያድምጡ
ነጋሽ መሐመድ