በሀሰተኛ ማስረጃና ቅጥር የፈተነው የደቡብ ክልል
ዓርብ፣ ጥቅምት 11 2015
ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃና በዝምድና ላይ የተመሰረቱ የሥራ ቅጥሮች በመንግሥት ተቋማት ሲፈጸሙ ማየት እየተለመደ ሥለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ ፡፡ በወላይታ ሶዶ ከተማ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም መድረኩን ያካሄደው የደቡብ ክልል የህዝብ አገልግሎትና የሰው ሀብት ልማት ቢሮም በሠራተኞች ቅጥር ላይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳጋጠሙት ይፋ አድርጓል፡፡ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ፣ በሥራ ቅጥርና እድገት ዙሪያ በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም በዘርፉ ከታዩት ችግሮች መካከል መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡ በአንጻሩ በክልሉ በ2014 የበጀት ዓመት በስራ አፈጻጸም የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ለተባሉ ተቋማትና ግለሰቦች በመድረኩ እውቅናና ማበረታቻዎች ተሰጥተዋል። በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በቅጥር ስርዓቱ ላይ የታዩ ክፍተቶች ህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃዎች፣ በዘመድ አዝማድ መጠቃቀም፣ በደረጃ እድገት ዙሪያ እየታዩ ያሉ ችግሮች መታረም እንደሚገባቸው አሳስበዋል። እውቅና የተሰጣቸው ተሸላሚ ግለሰቦችና ተቋማት በቀጣይ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት እንዳለባቸውም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት ።
5 ሺህ 480 የቅጥርና የዕድገት ሰነዶች የተሰረዙበት እርምጃ
ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችና ህገ ወጥ የሥራ ቅጥር የፌዴራል ተቋማትን ጨምሮ የክልላዊ መንግሥታት ፈተና እንደሆነ ይገኛል ፡፡ ይሁንእንጂ አብዛኞቹ ክልሎች ለጉዳዩ ትኩረት ሲሰጡም ሆነ እርምጃዎችን ሲወስዱ ብዙም አይስተዋልም ፡፡ በአንጻሩ የደቡብ ክልል በተለያዩ ጊዚያት በጉዳዩ ዙሪያ በሚሰጣቸው መግለጫዎችና በሚወስዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ችግሩን በመጋፈጥ ረገድ የተወሰነ ርቀት እንዲጓዝ ሳያስችለው አልቀረም ፡፡ የክልሉ የህዝብ አገልግሎትና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘይኔ ቢልካ ክልሉ በሰው ሀብት ልማት ረገድ በእቅድ የሚመራበትን ስርዓት በመከተል ህገ ወጥነት እና ብልሹ አሰራሮች ላይ የእርምት እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ይላሉ ።
በክልሉ ባለው አንድ ዓመት ብቻ በመንግስት መስሪያ ቤቶች በ32 ሺህ 238 ፋይሎች ላይ በጥናትና በጥቆማ ላይ የተመሠረተ የማጥራት ስራ መከናወኑን የጠቀሱት አቶ ዘይኔ ‹‹ በውጤቱም በ5 ሺህ 480 ህገ ወጥ ቅጥርና የደረጃ ዕድገት በመገኘቱ እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ በማጥራት ሥራው ከ117 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ሀብት ከብክነት ማዳን ከመቻሉም በላይ 11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ደግሞ ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ በዚህ ህገወጥ ተግባር ተሳትፈው በተገኙ 1 ሺህ 54 አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ›› ብለዋል ፡፡
የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃዎች ጉዳት እስከምን ድረስ ?
ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የንግድና የምጣኔ ሀብት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ናቸው ፡፡ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች መበራከትና በዘመድ አዝማድ የሚከናወኑ የሥራ ቅጥሮች እንደሀገር ጉዳታቸው ምን ድረስ ነው ሲል ዶቼ ቬለ DW ጠይቋቸዋል፡፡ ዶ/ር ወገኔ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚቀጠሩና ያለብቃታቸው በእድገት በሃላፊነት የሚቀመጡ ሠዎች በአገር ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ ፡፡ በሀሰተኛ ማስረጃ ወደ ሥራ የገባ የመንግሥት ሠራተኛ በቂና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ይቸገራል የሚሉት ዶ/ር ወገኔ ‹‹ ይህም የማህበራዊና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል የአገሪቱ ምርትና ምርታማነት እንዲጎዳ ያደርገዋል፡፡ ማህበረሰቡም የሚጠበቀውን ሥለማያገኝ በአገልግሎቱ እንዳይረካ ያደርገዋል ፡፡ በዚህም የተነሳ ህዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርብት ምክንያት እስከመሆን ሊደርስ ይችላል ›› ብለዋል፡፡
አዳዲስ አሠራሮችን መዘርጋት እንደአማራጭ መፍትሄዎች
ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ለመለየት የተለያዩ አገራት የተለያዩ ልምዶች አሏቸው የሚሉት የሀዋሳው ዩኒቨርሲቲ የንግድና የምጣኔ ሀብት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ የሥራ ቅጥር እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በተናጠል ከሚያከናውነው ይልቅ በአንድ ማዕከል ቢሠራ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በጤና ዘርፍ የሚገኙ ተቋማት የአንድ ማዕከል ቅጥር አሠራር እንደሚከተሉ የጠቀሱት ዶ/ር ወገኔ ‹‹ በጤናው ዘርፍ የታዩ በጎ ልምዶችን በመለየት በሌሎች የመንግሥት ተቋማት መተግበር ይገባል፡፡ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን በተመለከተም አንዲሁ ተመሳሳይ አሠራሮችን መዘርጋት ይገባል ፡፡ ለአብነት በአገሪቱ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች መረጃ የሚገኝበት አገር አቀፍ ቋት ማዘጋጀት ይቻላል ፡፡ በዚህ አገር አቀፍ የመረጃ ቋት ውስጥ ማን ፣ መቼ ፣ በየትኛው ተቋም ፣ በምን የትምህርት ዘርፍ እንደተመረቀ የሚያሳይ መረጃዎ የሚይዝ ይሆናል፡፡ ይህም ቅጥር የሚፈጽሙ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ሥለሚቀጥሩት ሠው ማንነት ከአገር አቀፉ የመረጃ ቋቱ ጋር በማገናዘብ የትምህርት ማስረጃዎችን በቀላሉ መለየት ይችላሉ ›› ብለዋል ፡፡
ሸዋን ግዛዉ ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ