1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ወንጀልአፍሪቃ

በሃሰተኛ ሰነድ ገንዘብ በማዘዋወር የተጠረጠሩት የሃይማኖት አባት ጉዳይ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2016

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብና ከአፍሪካ ኅብረት የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

https://p.dw.com/p/4f3tt
ቀሲስ በላይ መኮንን
ቀሲስ በላይ መኮንንምስል Seyoum Getu/DW

በሃሰተኛ ሰነድ ገንዘብ በማዘዋወር የተጠረጠሩት ቀሲስ በላይ

ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብና ከአፍሪካ ኅብረት የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ የተያዙት ቀሲስ በላይ መኮንን ዛሬም በቁጥጥር ስር ይገኛሉ።  

ቀሲስ በላይ መኮንን የተጠረጠሩበት የሰነድ ማጭበርበር 

የፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ቀሲስ በላይ መኮንን ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲያቀርባቸው፤ ሰነዱን ይዘው ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማዘዋወር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ በአካል ተገኝተው የኅብረቱ የፀጥታ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ካዋሉዋቸው በኋላ ለፌዴራል ፖሊስ እንዳስረከባቸውም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች እና ደኅንነታቸው
ፌደራል ፖሊስም ቀሲስ በላይ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል ቀርበው ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመያዝ፣ ለሦስት ግለሰቦችና ለአንድ የግል ድርጅት የባንክ ሒሳቦች በድምሩ ስድስት ሚሊዮን 50 ሺሕ ዶላር ሊያዘዋውሩ ሲሉ በአፍሪካ ኅብረት የፀጥታ ሠራተኞች ተይዘው ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ተላልፈው መሰጠታቸውን በመጥቀስ፣ የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት ለችሎቱ በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁ ተዘግቧል፡፡
ተጠርጣሪ ቀሲስ በላይ በበኩላቸው የተባለውን ድርጊት እንደፈጸሙ አምነው፤ በወንጀል ድርጊት ግን እንዳልተሳተፉ ገልጸው፤ ችሎቱም ለፖሊስ የሰባት ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅደው ነበር።

 ዶላር
ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ የተያዙት ቀሲስ በላይ መኮንን ዛሬም በቁጥጥር ስር ይገኛሉምስል Karel Navarro/AP Photo/picture alliance

በድርጊቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን አስተያየት

ስለሁኔታው የተጠየቀችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግለሰቡ በቤተክርስቲያኗ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚገለግሉ ቢሆንም፤ ተጭበርብሯል ከተባለው ሰነድ ጋር ግን ቤተክርስቲያኗን የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ አስታውቃለች፡፡ መምህር ዶ/ር አካለወልድ ተሰማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶመምስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመምበረ ፓቲሪያርክ ህዝብ ግንኙነት የሚዲያ ክፍል ዋና ኃላፊ ናቸው፡፡ “ሊቀአዕላፍ በላይ መኮንን በህግ ጥላ ስር በዋሉበት ጉዳይ ላይ ቤተክርስቲያን ጉዳዩን የመከታተል ጥረት ላይ ትገኛለች፡፡ እስካሁን በተደረገው ክትትል ግን በህግ ጥላ ስር የዋሉበት ጉዳይ ከቤተክርስቲያናችን ጋር የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ እንደሌለና በግል ህይወታቸው ውስጥ የገጠማቸው ነገር እንደሆነ ነው የተረዳነው” ያሉት ኃላፊው በቀጣይ ግን ጉዳዩ የቤተክርስቲያንን የሚጎዳ ነገር አለወይ ለሚለው በህግ ክፍል በኩል ማጣራት እንዲደረግ ትዕዛዝ መተላለፉን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረገው የባንኮች መጭበርበርና አንድምታው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ሚያዚያ 03 ቀን 2016 ዓ.ም. የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነትን በመገምገም ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ የአገሪቱ ባንኮች በበይነ መረብ ማጭበርበርያ ሥልቶች፣ ከባንኮች የውስጥ ሠራተኞችና ከሦስተኛ ወገን በሚደርሱባቸው የምዝበራ ድርጊቶች እየተጋለጡ ነው ብሎ ነበር። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ማለትም እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ በሐሰተኛ ሰነዶችና በሌሎች የማጭበርበር ድርጊቶች ባንኮች አንድ ቢሊዮን ብር ማጣታቸውን፣ ብሔራዊ ባንክ በግምገማ ሪፖርቱ ገልጿልም። ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው እጥፍ መሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀውስ ለባንኮች የማንቂያ ደወል ይሆን?
የፖሊቲካል ኢኮኖሚው ተንታኝ እና የዲመቴ መጽኃፍ ደራሲ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን እንደሚሉት የፋይናንስ ደህንነቱ ጉዳይ በአጠቃላይ የአገሪቱ ምጣኔ  ሃብት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው አንድምታ ጉልህ ነው ይላሉ፡፡ “አጭበርባሪዎች ልጠቀሙበት ከሚችሉ የላቀ የቴክኖሎጂ ልእቀት ጥቅም ላይ እስካለ ድረስ የንግዱ ማህበረሰብ እና የፋይናንስ አንቀሳቃሾች በጉዳዩ ላይ እምነት ካጡ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል” ብለዋል፡፡ 
በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲስተም ማስተካከያ ሂደት ውስጥ ባጋጠመው ተግዳሮት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ተመዝብሮ 95 በመቶውን ማስመለሱ መግለጹ ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ