በማላዊ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች አበሳ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 17 2015ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሞትና፣ የአካል ጉዳትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ስቃይና መከራ ከሚደርስባቸው የደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራት አንዷማላዊ ናት። ማላዊን በሚጨምረው ወደ ደቡብ አፍሪቃ በሚወስደው የስደት መስመር ላይ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስከሬን በየቦታው መለቀም ከጀመረ ሰንብቷል። በማላዊ ደን ውስጥ በአጋጣሚ የተገኘው የኢትዮጵያውያን ሳይሆን እንዳልቀረ የተገመተ የ30 ስደተኞች አስከሬን የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው። ሞዛምቢክ ውስጥ በጉዞ ላይ የነበሩ የ64 ኢትዮጵያውያን አስከሬን በኮንቴይነር ታጭቆ መገኘቱም ሌላው ከሁለት ዓመት በፊት የተሰማ አሳዛኝ ዜና ነበር።ከሞት የተረፉትም በማላዊ እስር ቤቶች በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አንድ ኢትዮጵያዊው የማላዊ ነዋሪ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ስደተኞች በዋነኛነት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር እንደመተላለፊያ የሚጠቀሙባት ማላዊ አማካይ መንገድ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት። በዚህ የስደት መስመር ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት አልሞ ጉዞ የሚጀምረው ሁሉ ይሳካለታል ማለት አይደለም። ከመካከላቸው መጨረሻቸው ሞት የሆነ ኢትዮጵያውያን ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከአንድ ወር በፊት ማላዊ የተገኙት 30 የኢትዮጵያውያን ሳይሆን እንዳልቀረ የተገመተ አስከሬን እንዲሁም በተጫኑበት ኮንቴነር ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት ዚምባብዌ የተገኘው የ64 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስከሬን የዚህ ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ በአጋጣሚ የተገኙ አስከሬኖች ሲሆኑ በእግርም በመኪናም በሚካሄደው በዚህ አደገኛ በሚባለው የስደት ጉዞ ብዙዎች መንገድ ላይ በተለያዩ አደጋዎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ አንድ ኢትዮጵያዊ የማላዊ ነዋሪ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉት እኚህ ኢትዮጵያዊ እንደሚሉት ስደተኞቹን ከሀገር ወደ ሀገር የሚያሸጋግሩት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ደላሎች ናቸው ። ስደተኞቹም ለአደጋ የሚጋለጡት ደላሎቹ እነርሱን በድብቅ ለማጓጓዝ በሚሞክሩበት ወቅት ነው።
«ብዙ ጊዜ ከሆሳእናና ከሀድያና ከምባታ አካባቢ ነው የሚመጡት ከዱራሜ አካባቢም ወደ ሞያሌ ይሄዳሉ ሞያሌ ያለው ደላላ ይቀበላቸውና ለኬንያ ላለው ያቀብላቸዋል።ኬንያው ደግሞ ታንዛንያ ላለው ።የታንዛንያው ደግሞ ለማላዊ ላለው ማላዊ ያለው ደግሞ እያሉ እየተቀባበሉ በŀneደዚህ ዓይነት መንገድ ነው የሚሄዱት።»
ከሞት አምልጠው በሕይወት ማላዊ መድረስ ከቻሉት ውስጥ ደግሞ የአብዛኛዎቹ መጨረሻ የማላዊ አስከፊ እስርቤቶች ናቸው። ኢበአመዛኙ እድሜያቸው ከ20 እስከ 30 ዓመት የሚገመት ኢትዮጵያውያን በሕገ-ወጥ መንገድ ማላዊ ገብታችኋል ተብለው በተለያዩ የማላዊ እስር ቤቶች ውስጥ እየተሰቃዩ ነው። ትዮጵያዊው የማላዊ ነዋሪ እንዳሉት ብዙዎቹ ተስፋ የቆረጡ ናቸው።
« እስር ቤት ሲመጡ የጠበቁት ነገር ስለማይሆን መሬት ላይ ነው የሚተኙት ።ገንፎ ነው የሚሰጣቸው።ያልለመዱት ዓይነት ምግብ ነው።በሽታ እከክ ይታመማሉ ተጨናንቀው ስለሚያዙ ፤እስር ቤቶቹ ራሳቸው ደስተኛ አይደሉም።አንዳንድ ጊዜ የኢትዮጵያ እስረኛ ስለሚበዛ በጀታችንን እየወሰዱብን ነው የሚል ቅሬታ አላቸው።ሲታመሙ ህክምና አያገኙም እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነው የሚታይባቸው ሰዎቹ።»
በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን ዩኒቨርስቲ፣ ከፍልሰት ልማትና እኩልነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ባልደረባ አቶ ዮርዳኖስ ሰይፉ እስጢፋኖስ በተለይ ከዚህ ቀደም ማላዊ የሚገኙ ስደተኞች ይዞታ የከፋ ከሆነበት ምክንያት አንዱ በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አለመኖር መሆኑን ያስታውሳሉ
«ከኢትዮጵያ ተነስቶ ደቡብ አፍሪቃ ሲኬድ መሸጋገሪያ አገራት አሉ።ስድስት ሰባት ።ከነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚገኘው ኬንያ፣ ታንዛንያ ፣ደቡብ አፍሪቃ ነው ።ማላዊ ላይ የለም።»
እስረኞቹን አስፈላጊ ሲሆን በትርጉም የሚረዷቸውና በኮቪድ ምክንያት ተቀዛቀዘ እንጂ ከሌሎች ኢትዮጵያውያንም ጋር በመሆን ምግብ ይዘው የሚጠይቋቸው በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊ እንደሚሉት ግን ከአንድ ወር በፊት ታስረው የነበሩት የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር አሁን ቀንሷል። ይህ የሆነውም ከኬንያ ኤምባሲ ማላዊ የሄዱ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ለታሰሩት ስደተኞች አስፈላጊ የጉዞ ሰነዶችን ከሰጧቸው በኋላ ወደ ሀገራቸው መመለስ በመቻላቸው ነው።
«ከአንድ ወር በፊት ወደ 500 የሚጠጉ እስረኞች ነበሩ እዚህ ሀገር ኢትዮጵያውያን እስረኞች።አሁን የተወሰኑትን አይ ኦ ኤም በሚባለው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ጉዳይ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ መንግሥት መጥቶ የጉዞ ሰነድ ሰጥቷቸው የተወሰኑት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ግን አሁንም 200 300 የሚጠጉ እስረኞች ማላዊ ውስጥ እንዳሉ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል።የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተበታትነው ይገኛሉ።አንዳንድ ጊዜ ይመጡና (የመንግሥት ባለሥልጣናት)ሰነድ ሰጥተው ሄደው ሳምንት ሳይሞላቸው ሌላ መቶ ሰው ይታሰራል ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የጉዞ ሰነድ እስኪያገኙ 8 ወር 9 ወር ሊፈጅ ይችላል።»
ከአንድ ወር በፊት ማላዊ በሚገኝ፣ጥብቅ ደን ውስጥ በጅምላ መቃብር ውስጥ ከተገኘው 30 የኢትዮጵያውያን ሳይሆን እንዳልቀረ የተገመተ አስከሬን ጉዳይ ጋር በተያያዘ የቀድሞ የማላዊ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪክ እንጀራ ልጅ ታዲኪራ ማፉብዛ ተጠርጥረው ታስረዋል። የማላዊው ነዋሪ እንደሚሉት በዚህ ስደተኞችን ከሀገር ወደ ሀገር የማሻገር ሰንሰለት ውስጥ ሌሎች ባለስልጣናትም ይገኙበታል ተብሎ ይታመናል።
ኂሩት መለሰ