በርካቶችን እየጎዳ የሚገኘው የምግብ መውረጃ ቧንቧ ካንሰር
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2016የምግብ ቧንቧ ካንሰር ምንነት
በምግብ ቧንቧ ላይ የሚከሰተው ካንሰር ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የዘርፉ ባለሙያ ይናገራሉ። በዓለም ላይ ሲታይ ወደ ምሥራቅ እና ደቡባዊ እስያ፤ አፍሪቃ ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ ሃገራት በብዛት የሚታይ በሽታ መሆኑንም ያስረዳሉ። የምግብ ቧንቧ ላይ ካንሰር ኢትዮጵያ ውስጥም በተለይ በብዛት የሚከሰትባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ነው የተረዳነው። ለምን? መንስኤውስ?
የምግብ መውረጃ ቧንቧ ላይ የሚከሰተው ካንሰር አካባቢዎችን ለይቶ በብዛት በሰዎች ላይ እንደሚገኝ የገለጹልን የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ተፈራ በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። የምግብ መውረጃ ቧንቧን የሚያጠቃው ካንሰር እሳቸው በቅርብ ባስተዋሉት መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በብዛት በሰዎች ላይ የሚገኝ የካንሰር አይነት እንደሆነ ነው ያመለከቱት።
ለምግብ ቧንቧ ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች
ለምግብ ቧንቧ ካንሰር አጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ መንስኤዎችን በተመለከተ ምርምር ያካሄዱት ሌላኛው የአዳማ ሆስፒታል ጆሌጅ የስነምግብ ረዳት ፕሮፌሰር፤ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሀጂ አማን በበኩላቸው ይህ የካንሰር አይነት በሚያደርሰው ጉዳት በዓለም በሰባተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ። ለሞት ከሚያጋልጡ የካንሰር አይነቶችም ስድስተኛው መሆኑንም አመልክተዋል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የምግብ መውረጃ ቧንቧን የሚያጠቃው ካንሰርበብዛት የገጠሩን ኅብረተሰብ ነው። በመንስኤነት ትኩስ ገንፎ፤ ትኩስ ቡናም ሆነ ሻይ መጠኑን አብዝቶ መጠጣት፤ አትልክትልም ሆነ ፍራፍሬ አለመመገብ የመሳሰሉት ከአመጋገብ ጋር በተገናኘ ተጠቅሰዋል። የምግም መውረጃ ቧንቧ ካንሰር በብዛት የሚከሰትባቸው አካባቢ ነዋሪዎች የአመጋገብ ልማድ ከዚህ ጋር እንደሚገናኝ ምርምሩን ያካሄዱት ዶክተር ሀጂ አማን ተናግረዋል።
ከአመጋገብ እና ጭሳጭስ በተጨማሪ ለእርሻም ሆነ ለተለያዩ በሽታ አምጪ ተባዮች መከላከያ የሚረጩ ኬሚካሎች ጉዳይ ሌላው አጋላጭ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል። የኬሚካሎቹን መያዣ ዕቃ ለቤት ውስጥ አገልግሎት መጠቀምም ሌላው ለዚህ የጤና ችግር ከሚያጋልጡ መንስኤዎች አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል። በከተሞች አካባቢም የትንባሆና አልክሆል ተጠቃሚዎች ዋነኞቹ ለዚህ ካንሰር ተጋላጮች መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የህመሙ ምልክቶች
የምግብ መውረጃ ቧንቧ ካንሰር የተለያዩ የህመም ምልክቶች እንደሚያሳይ ነው ከባለሙያዎቹ የተረዳ ነው። ምግብ ለመዋጥ መቸገር ዋነኛው ሲሆን በመጠኑ የሚታየው ይህ ችግር ውሎ አድሮ ፈሳሽም ለመዋጥ እስከመቸገር ሊያደርስ እንደሚችል የካንሰር ከፍተኛ ህክምና ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ገልጸዋል።
ለዚህ የጤና ችግር የተጋለጡ ወገኖች ህመሙን ከተራ የጉሮሮ ህመም ጋር አመሳሰለው ይዘናጉና ወደ ሀኪም ቤት ስለማይሄዱ በሽታው ስር ከሰሰደደና ከተባባሰ በኋላ ህክምና የማይረዳበት አጋጣሚ በመኖሩ ለሞት የሚዳረጉት እንደሚበረክቱም ነው የገለጹት።
ይህ የምግብ መውረጃ ቧንቧ ካንሰር በአብዛኛው በዕድሜ ከፍ ያሉት ላይ የሚከሰት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን ልጆች ላይም እንደሚያጋጥም ነው ባለሙያዎቹ ያመለከቱት። በብዛትም ወንዶችን እንደሚያጠቃ የካንሰር ሀኪሙ ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ባላቸው መረጃ እንዳስተዋሉት ደግሞ የሴቶቹ ቁጥር ከፍ እንደሚል ዶክተር ቢንያም አመልክተዋል።
ችግሩ በተወሰነ አካባቢ ለምን በዝቶ ተገኘ የሚለውን ለማጥናትና የኅብረተሰቡንም ሆነ የጤና ባለሙያዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ አራት ዩኒቨርሲዎች ማለትም የአርሲ ዩኒቨርቲ፣ የመዳወለቡ ዩኒቨርሲቲ፣ የአርሲ ነገሌ ሆስፒታል እና አዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ፤ አዮፓ ከተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ የአሜሪካ ድርጅት ጋር በመተባበር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ዶክተር ቢንያም ገልጸዋል። ይህ በሽታ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ሊያውቅ ይገባል ያሉትን እንዲህ ተናግረዋል።
ዶቼ ቬለ ስለአሳሳቢው የምግብ መውረጃ ቧንቧ ካንሰር በሌላ ጊዜም የዘርፉን ባለሙያዎች በመጋበዝ መረጃዎችን ማቅረቡን ይቀጥላል፤ ለዛሬ ግን ማብራሪያ የሰጡንን ባለሙያዎች እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ