1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች “የምግብ እጥረት አጋጥሞናል” አሉ፡፡

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 1 2015

ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ተፈናቃዮች ለምግብ እህል እጥረት መዳረጋቸውን ተናገሩ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ በአንዳንድ የመጠለያ ጣቢያዎች የእርዳታ እህል መዘግየቱን አምነዋል። ሆኖም በቀጣይ ሳምንት የእርዳታ እህል እንደሚደርሳቸው አረጋግጠዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4I283
ደብረ ብርሃን የሚገኙ ተፈናቃዮች ዕርዳታ ለመቀበል ተሰልፈው
ከምዕራብ ኦሮሚያ ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን የሚገኙ ተረጂዎች ምስል North Shewa Zone communication Office

በሰሜን ሸዋ የሚገኙ ተፈናቃዮች አቤቱታ

በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች “የምግብ እጥረት አጋጥሞናል” አሉ፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ተፈናቃዮች ለምግብ እህል እጥረት መዳረጋቸውን ተናገሩ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ በአንዳንድ የመጠለያ ጣቢያዎች የእርዳታ እህል መዘግየቱን አምነዋል። ሆኖም በቀጣይ ሳምንት የእርዳታ እህል እንደሚደርሳቸው አረጋግጠዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የሰሜን ሸዋ ዞን ተፈናቃዮች ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች በተፈጠሩ ግጭቶች ቀያቸውን ለቅቀው የመጡ እንደሆኑ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ አስታውቋል፡፡  ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ከአንድ ዓመት በፊት ከማንነት ጋር በተፈጠረ ግጭት ከቀያቸው ተፈናቅለው  በደብረብርሀን “ቻይና ካምፕ” ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አንዱ የምግብ እርዳታ ከተቋረጠ ወራት መቆጠራቸውንና ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡ የችግሩ ምክንያትም ቀደም ሲል በጎ አድራጊ ተቋማት ቀጥታ ይሰጡን የነበረውን እርዳታ ከተማ አስተዳደሩ በመከልከሉ ነው ይላሉ፡፡

ተፈናቃዩ “በፊት የከንቲባ ቢሮ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እርዳታ እያመጡ ያስገቡ የነበረውን እዛ መግባት የለበትም ከእኛ መጋዝን ገብቶ ከዚያ በኋላ ነው የሚከፋፈለው እንጂ መግባት የለበትም ከሚል አንፃር በጎ አድራጊዎች ከእኛ እንዲሸሹ ሆነ፣ እነሱ ሸሹ እየገቡ አይደለም ። አሁን ከመንግስትም የተሰጠ ምንም ነገር የለም፤ በጎ አድራጊም እየመጣ አይደለም፤ አሁን ተፈናቃዩ በሀይለኛው ርሀብ ላይ ነው ያለው” ብለዋል ፡፡

ሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤትና ደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር በተደጋጋሚ እየሄዱ እርዳታ ቢጠይቁም ምላሽ እንደማይሰጣቸው የሚናገሩት ተፈናቃዮቹ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ እርዳታ ካልቀረበ ብዙ ሰዎች በርሀብ ሊሞቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እንደተፈናቀሉ የሚናገሩት ሌላው ተፈናቃይም ለሶስት ወር ያህል የተሰጠ የምግብ እርዳታ ባለመኖሩ በመጠለያ ጣቢያዎች በሚኖሩ በተለይም በህፃናትና በአቅመ ደካማ ሰዎች ላይ ችግሩ መበርታቱን ገልጠዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ወላጋ ዞን የተፈናቀሉ አንድ አስተያየት ሰጪም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ነው የሚናገሩት፡፡

የደብረብርሐን ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ በየነ በበኩላቸው ማንኛውም እርዳታ የሚሰጥ አካል ከተማ አስተዳደሩ አውቆት እንዲሰጥ እንጂ እርዳታ ተቀብሎ ላከፋፍል አላለም ብለዋል፣ በአንድ ወቅት ከተማ አስተዳደሩ ሳያውቀው ተፈናቃዮች የተበላሸ ምግብ ተመግበው የምግብ መመረዝ አጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰው አሁንም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ የከተማ አስተዳደሩ የሚሰጡ እርዳታዎችን ማረጋገጥ እንዳለበትና አንዳንድ አካላት እርዳታን እንደ ንግድ እየተጠቀሙበት በመሆኑም ያን የመከላከል ስራ እንጂ እርዳታ ለተፈናቃዮች እንዳይደርስ ከሚል መነሻ አሰራሩ እንዳልተቀየረ አረጋግጠዋል፡፡

ጽ/ቤት ኃላፊው ፣ “ (ባለፈው ጊዜ) የምግብ መመረዝ ያመጣው እኛ የማናውቀውና ከእኛ ፈቃድ ውጪ ገብቶ ነው፤ ሳናውቀው አይግባ ነው እንጂ ያልነው እና እንስታችሁ አላልንም ፤ አሁንም ሰዎች ይዘው ይመጣሉ፤ ይዘው የመጡትን ሀብት ይነግሩናል፤ እነማን እንደሆኑ እናውቃለን።  ባለው እጥረት መሰረት ከዚህኛው ካምፕ፣ ከዚያኛው ካምፕ ብለን የመደልደል ስራ ነው ምንሰራው፡፡ እኛ ተረክበን መጋዝን አስገብተን ለነሱ የምንሰጥበት እድልም የለንም፣ መጋዝንም የለንም፣ ከዚህ በፊትም እንደዚህ ያለ ነገር አልተፈጠረም፣ የሚመጣውን ሀብት አናውቀውም ሚሊዮን ይለመናል የሚሰጠው ትንሽ ነው፤ ስለዚህ ሊሰጥ የፈለገ የሀብቴ ምንጭ ይህ ነው፣ የምደግፈው ይህንን ነው፣ የሰበሰብኩት ይህንን ነው መባል ስላለበት ነው፤ በተፈናቃይ ስም ንግድ እየበዛ ሄደ ” በማለት ለዶይቼ ቬሌ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ በበኩላቸው፣ የምግብ መዘግየት በአንዳንድ መጠለያ ጣቢያዎች መኖሩን አምነው፣ ሆኖም በቀጣይ ሳምንት እርዳታው ከፌደራል አደጋ ስጋት አመራር እንደሚደርሳቸውና ለተፈናቃዮች እንደሚከፋፈል አረጋግጠዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከተለያዩ አካባቢዎች፣ በዋናነት ከኦሮሚያ ክልል፣ የተፈናቀሉ 90 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ