በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ችግር
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2 2017በተባበሩት መንግስት ድርጅት ስር በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ተልእኮ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ነው ሲል ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለ የመብት ተሟጋች ድርጅት ዐሳወቀ። የሰብአዊ መብት ተቋሙ የኢትዮጵያ መንግስት የሚገባቸው ክፍያቸው አልከፈላቸውም፣ ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱም የድህንነት ስጋት አለባቸው ብሏል።
ኢትዮጵያ በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የነበራትን የሰላም ማስከበር ሚና ተከትሎ በተልእኮው ተሳታፊ የነበሩ እና በኋላ ላይ በፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ ኃይሎች መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ አጠቃላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር 851 እንደሚደርስ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተሰኘው የመብት ተሟጓቾች ድርጅት ይገልፃል።
እነዚህ በወቅቱ የነበረውን ጦርነት በመሸሽ በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀው ይኖሩ የነበሩ የሰላም አስከባሪ ልኡክ አባላት የሆኑ የትግራይ ተወላጆች፥ አሁንም በአብዛኛው በሱዳን ገዳሪፍ እንዳሉ የሚገልፀው ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች፥ ወደ ሀገራቸው ላለመመለስ የድህንነት ሥጋት፣ በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ እና የገንዘብ አቅም እንቅፋት እንደሆናቸው ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል የሆኑ እና አንድ መቶ ገደማ የሚገመቱ በተለይም የሱዳን ጦርነት ከተባባሰ በኃላ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው መግባታቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኃላ በቤንሻንጉል ጉምዝ ተይዞ ወታደራዊ ፍርድቤት ቀርቦ ሶስት ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደበት የሰላም አስከባሪ ልኡክ መኖሩም በመብት ተሟጓቾች ሪፖርት ተጠቅሷል።
ለድህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ እና በሱዳን ዳርፉር ከነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰላም አስከባሪ ልኡክ አንድ የሆኑት፥ እንዲሁም ተልእኮው ሲጠናቀቅም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ሳይፈቅዱ ቀርተው በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀው ቀርተው ከነበሩት መካከል የሆኑት ዶቼቬሌ ያነጋገራቸ የሰላም አስከባሪ ልኡክ አባል፥ ወቅቱ የትግራይ ጦርነት የተባባሰበት እና በኢትዮጵያ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ደግሞ ከፍተኛ በደል ይደርስ የነበረበት ስለሆነ፥ እሳቸው ጨምሮ 122 የተልእኮው አባላት ወደ ኢትዮጵያ እንዳልተመለሱ ያስረዳሉ። ይሁንና ተዋጊዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ድህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ቢጠብቁም አሁንም ይህ አለመሆኑ ይናገራሉ።
ያነጋገርናቸው የቅድሚ ለሰብአዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ ድርጅታቸው የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የሰላም ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርተው በነበሩ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የመብት ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡ ገልፀውልናል። አቶ መብርሂ እንደሚሉት ተልእኳቸው ያጠናቀቁ ሰላም አስከባሪዎች የሚገባቸው ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም ተከልክለዋል እንዲሁም በከፍተኛ የድህንነት ስጋት ላይ ገብተዋል።
እነኚህ በዳርፉር ተሰማርተው የነበሩ የቀድሞ ሰላም አስከባሪ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስታት የተረከበው እና ለአገልግሎታቸው ሊሰጣቸው የሚገባ ደሞዛቸው እንዲከፍላቸው እንዲሁም የድህንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የእነዚህ ከፍተኛ ችግር ላይ ያሉ ሰላም አስከባሪዎች ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ አለመያዙ አሳሳቢ መሆኑ የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ ይገልፃሉ።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ባወጣው ሪፖርት እንደተጠቀሰው የሰላም አስከባሪ አባላቱ በወር 1428 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፈሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወስኖ የነበረ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግስት እንደዬማእርጋቸው እና የተለያዩ መለክያዎች የተለያየ የክፍያ ስሌት ያስቀምጥላቸዋል። በሰብአዊ መብት ድርጅቱ እና በቀድሞ ሰላም አስከባሪዎቹ ለቀረቡ ቅሬታዎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር፣ የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዲሁም ከትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር