1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ለተቸገሩ ከተመደበው ዕርዳታ ዝርፊያ ጀርባ ያለው ማነው?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 10 2015

በትግራይ ከ88 ሺሕ ኩንታል በላይ ስንዴ መዘረፉን የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር የሰየመው መርማሪ አስታውቋል። የትግራይ አስተዳደር መዋቅር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መዋቅር እና የኤርትራ ኃይሎች ዘረፋውን እንደፈጸሙ መርማሪ ኮሚቴውን የሚመሩት የትግራይ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሉቴናንት ጄኔራል ፍሰሐ ኪዳነ ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4SiNl
Symbolbild Welternährungsprogramm der Vereinten Nationen
ምስል AP Photo/picture alliance

በትግራይ ለተቸገሩ ከተመደበው ዕርዳታ ዝርፊያ ጀርባ ያለው ማነው?

ከፍተኛ መጠን ያለው የእርዳታ እህል በትግራይ አስተዳደር መዋቅር፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስታት መዋቅርና በኤርትራ ሐይሎች መዘረፉ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። የፌደራሉ መንግስት፣ የትግራይ አስተዳደር መዋቅሮች እንዲሁም የኤርትራ ሐይሎች በአጠቃላይ ከ88 ሺህ ኩንታል በላይ ለተቸገሩ ዜጎች መቅረብ ይገባው የነበረ ስንዴ ማዝረፋቸው፥ ማጭበርበሩ ያጣራው ግብረሃይል ገልጿል።

ከ5 ሚልዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ህዝበ ወደሚገኝባት ትግራይ የምግብ እርዳታ አቅርቦት መቋረጡ ያሳሰባቸው የተለያዩ አካላት፥ ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥል፣ ያጭበረበሩት ደግሞ ለሕግ እንዲቀርቡ እየጠየቁ ነው።

ዓለምአቀፍ እርዳታ አቅራቢ ተቋማት በትግራይ ለሚገኝ እርዳታ ፈላጊ ህዝብ ያቀርበው የነበረ ድጋፍ ዘረፋ እየተፈፀመበት ነው በማለት ማቋረጡ ተከትሎ፣ በትግራይ ተፈፀመ የተባለው ማጭበርበር የሚያጣራ ግብረሃይል በክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ይታወሳል። ይህ የእርዳታ ማጭበርበር እና ዘረፋ አጣሪ ግብረሃይል በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ እርዳታ በትግራይ አስተዳደር መዋቅር፣ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ የኤርትራ ሐይሎች እና ሌሎች አካላት መዘረፉ ይፋ አድርጓል።

Äthiopien | Nahrungsmittel Transport
ከ5 ሚልዮን በላይ እርዳታ ፈላጊ ህዝበ ወደሚገኝባት ትግራይ የምግብ እርዳታ አቅርቦት መቋረጡ ያሳሰባቸው የተለያዩ አካላት፥ ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥል፣ ያጭበረበሩት ደግሞ ለሕግ እንዲቀርቡ እየጠየቁ ነው።ምስል Million Haileselassie/DW

እንደ አጣሪው መረጃ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት አካላት፣ የኤርትራ ሐይሎች እና የትግራይ አስተዳደር መዋቅር በአጠቃላይ ከ88 ሺህ ኩንታል በላይ ለተቸገሩ መድረስ ይገባው የነበረ ስንዴ ያጭበረበሩ ሲሆን፥ ሌላ በመጠን የተገለፀ ዘይትና አተርም እንዲሁ መዘረፉ አስታውቋል። የትግራይ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሐላፊ እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ ማጭበርበር አጣሪ ግብረሃይል ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳነ እንዳሉት፥ ከኤርትራ፣ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ አስተዳደር መዋቅር በተጨማሪ የተፈናቃዮች አስተባባሪዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅት ሰራተኞች በእርዳታ ምግብ ማጭበርበር ላይ መሳተፉቸው ጠቁመዋል። ጀነራሉ እንዳሉት እስካሁን ከማጭበርበሩ ጋር በተያያዘ በርካታ ተጠርጣሪዎች መለየታቸው እና መያዛቸው ተናግረዋል።

እጣሪው እንደሚለው በተለይም የኤርትራ ሐይሎች በሸራሮ እና ሌሎች ከተሞች ከ28 ሺህ ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል መዝረፋቸው፣ በፌደራል መንግስት መዋቅርም እንዲሁ ከ43 ሺህ ኩንታል በላይ መጭበርበሩ ያነሳ ሲሆን፥ ከዚህ ባለፈ የፌደራል ሀይሎች የእርዳታ እህል እንዳይዘረፍ የመጠበቅ ሚናቸው አለመውጣታቸው ጀነራሉ ጨምረው ተናግረዋል። ማጣራቱ እና ተጠርጣሪዎች አድኖ ለፍርድ የማቅረብ ስራው እየቀጠለ ስለመሆኑ ተገልጿል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ትግራይ የተቋረጠው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀጥል የተለያዩ አካላት ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ። በእርዳታ ላይ የተፈፀመው ዝርፍያና ማጭበርበር ያወገዘው በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፥ ይሁንና መፍትሔ ማቋረጥ ሳይሆን ወንጀለኞችን ለይቶ ለፍርድ ማቅረብ፣ እንዲሁም የተቋረጠው የምግብ እርዳታ መቀጠል መሆኑ አውስቷል። የክልሉ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፥ በትግራይ ከ5 ሚልዮን በላይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ ፈላጊ ነው።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ
እሸቴ በቀለ