በትግራይ ክልል ለአስር ቀናት የሚዘልቅ የተለያዩ በሽታዎች መከላከያ ክትባት ዘመቻ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 10 2015ለሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት በተለይም በጤና ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በክትባቶች፣ በመድሃኒት እንዲሁም አስቀድሞ በሚሰሩ የመከላከል ሥራዎች ጠፍተው የነበሩ በሽታዎች ጭምር ዳግም ተመልሰው የኅብረተሰቡ የጤና ስጋት እንዲሆኑ ማድረጉገ ይገለፃል። የጤና ተቋማት ውድመት፣ የመድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ እጦት አልያም ውሱንነት አሁንም የትግራይ የጤና ስርዓት እየፈተኑ ነው። እነዚህ ችግሮች የሚፈጥሯቸውን የጤና ቀውሶች ለመቀነስ ደግሞ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እና ዮኒሴፍ በጋራ በክልሉ ለ10 ቀናት የሚቆይ ለስድስት የተለያዩ ዓይነት በሽታዎች መከላከያ የሚሆን ክትባትእንዲሁም የበሽታዎች ቅኝት ዘመቻ ጀምረዋል። ትናንት የተጀመረው የክትባት ዘመቻ ባለፉት የጦርነት ጊዜያት በትግራይ ጠፍተው የነበሩ ክትባቶች ያካተተ ሲሆን በተለይም ተጋላጭ የተባሉ ሕጻናት እና ሴቶች ላይ ትኩረቱ ያደረገ እንደሆነ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል። እንደ ጤና ቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሪኤ ኢሳያስ ገለፃ፥ የ10 ቀናት የክትባት ዘመቻው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የጤና ስጋቶችን የመለየት እና የማከም ሥራንም ያጠቃለለ ነው።
በዘመቻ ከሚሰጡ ክትባቶቹ መካከል የኮረና ተሐዋሲ ክትባትም የሚገኝበት ሲሆን፥ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ዘግይቶ የተጀመረው ይኽ ክትባት አሁን በስፋት ለመስጠት፥ ያልተዳረሰባቸው በታችኛው የዕድሜ ክልል ያሉ ሕጻናትን ለማካተት ታቅዶ ሥራ መጀመሩን ዶክተር ሪኤ ኢሳያስ ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል ለሚካሄደው ሰፊ የክትባት ዘመቻ ዮኒሴፍ 45 ሚልዮን ብር ወጪ ማድረጉን የገለፁት በዮኒሴፍ የትግራይ ክልል የጤና ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ዓይኒምሸት ገብረሕይወት በበኩላቸው፤ ለዚህ በኅብረተሰቡ ጤና መሠረታዊ ለውጥ ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቅ ዘመቻ አስፈላጊ አቅርቦት መዘጋጀቱን በዘመቻው ማስጀመርያ ስነስርዓት ላይ አንስተዋል። በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል 80 ከመቶ የጤና ተቋማት በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ውድመት እንደደረሰባቸው የክልሉ የጤና ቢሮ ጥናት ያመለክታል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ