በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ሮሮ
ረቡዕ፣ ሰኔ 12 2016በትግራይ ክልል በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ለዲፕሎማቶች እና ዓለምአቀፍ ተቋማት እንዲሁም ሚድያዎች ባሰራጨው መግለጫው በትግራይ የጦርነቱ ተፈናቃዮች ሁኔታ እየከፋ መሆኑ የገለፀ ሲሆን አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻ አንስትዋል። ያነጋገርናቸው የፓርቲው የፖለቲካ ጉዳዮች ሐላፊ አቶ ኪሮስ ሃይለስላሴ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ፥ ለፖለቲካ ትርፍ ከሚገባው ቃል በዘለለ ፍቃደኝነት ይሁን ቁርጠኝነት የለውም ብለዋል። የትግራይ ተፈናቃዮች እስከሰኔ መጨረሻ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ተባለ
በትግራይ የሚገኙ በተለይም ከምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ የተፈናቀሉ ዜጎች ዘንድሮ ከክረምት በፊት ወደቀዬአቸው እንደሚመለሱ ቃል ተገብቶላቸዋው የነበረ ቢሆንም ይህ አለመፈፀሙን ያነሳሉ። ከእንዳባጉና የተፈናቃዮች መጠልያ ያነጋገርናቸው ከምዕራብ ትግራይ ሑመራ የተፈናቀሉ የስድስት ልጆች እናት መብራት ጥሩነህ፥ ከነበረው በርካታ እና የተወሳሰበ ችግር በተጨማሪ የክረምት ወቅት መግባቱ ተከትሎ ለከፋ ሁኔታ መዳረጋቸውን ይናገራሉ። ወይዘሮ መብራት "አራት ዓመት ያገለገለ የፕላስቲክ መጠለያ እንኳን አሁን ተቀዶ ዝናብ እና ፀሐይ እየተፈራረቁብን ነው" ይላሉ። ትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች እሮሮ
ሌላው ተፈናቃይ ሙላት መኮንን በበኩላቸው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እስከ ሰኔ 30 ድረስ ወደ ቀዬአችሁ ትመለሳላችሁ ቢልም የተባለው እየተፈፀመ ባይሆንም አንዳንድ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ያደርጉት የነበረ ድጋፍ እያቋረጡ በቅርቃር ላይ ገብተናል ይላሉ።
ስለተፈናቃዮቹ ጉዳይ የተናገሩት የሳልሳይ ወያነ ትግራዩ አቶ ኪሮስ ኃይለስላሴ፥ እነዚህ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጣቸው ዓለምአቀፍ ጫና እንደሚፈጥሩ፥ ለትላልቅ ሀገራት ፈተና ሆኖ ያለ የስደተኞች ጉዳይንም እንደሚያባብስ ገልፀዋል።
አቶ ኪሮስ "ተፈናቃዮች ካልተመለሱ ወደ ስደተኝነት ነው የሚቀየሩት። ከትግራይ ከኢትዮጵያ ወጥተው ሌላ አማራጭ ያያሉ። በተለይም ወጣቶቹ አሁን ከተፈናቃዮች መጠልያ እየለቀቁ ወደ የመን እንዲሁም በሱዳን በኩል ወደ ሊብያ እያመሩ ነው" ሲሉ አክለው ገልፀዋል። የትግራይ ተፈናቃዮች ቅሬታ
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ