1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ወታደሮች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተጓጎላቸውን አሜሪካ አወገዘች

እሑድ፣ ግንቦት 8 2013

በኢትዮጵያ ወታደሮች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንዳይደርስ ያደረጉባቸው የተረጋገጡ ማስተጓጎሎች እየጨመሩ መምጣታቸው እንደሚያሳስባት አሜሪካ አስታወቀች። የአውሮፓ ኅብረት ወታደራዊ ኃይሎች የሰብዓዊ ዕርዳታን ለማስተጓጎላቸው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማረጋገጫ መገኘቱን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንኖ ነበር። 

https://p.dw.com/p/3tSzM
Belgien Treffen der NATO-Außenminister in Brüssel Antony Blinken
ምስል Yves Herman/AFP

በኢትዮጵያ ወታደሮች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንዳይደርስ ያደረጉባቸው የተረጋገጡ ማስተጓጎሎች እየጨመሩ መምጣታቸው እንደሚያሳስባት አሜሪካ አስታወቀች። 

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትናንት ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ “ይኸ ተቀባይነት የሌለው ባህሪ አፋጣኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው 5.2 ሚሊዮን ሰዎችን ለበለጠ አደጋ ያጋልጣል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ "የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት በትግራይ የሚገኙ ወታደሮቻቸው ይኸን የሚወገዝ ተግባር እንዲያቆሙ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ሁሉ እንዲወስዱ አሜሪካ ጥሪ ታቀርባለች" ብለዋል። 

የአውሮፓ ኅብረት ከትናንት በስቲያ አርብ ባወጣው መግለጫ ወታደራዊ ኃይሎች የሰብዓዊ ዕርዳታን ለማስተጓጎላቸው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማረጋገጫ መገኘቱን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንኖ ነበር። 

"የወታደራዊ ኃይሎች ክልከላ የሰብዓዊ ቀውስ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ በደረሰባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ዕርዳታ የማድረስ አቅምን በእጅጉ እያደናቀፈ ነው" ያለው የአውሮፓ ኅብረት በትንሹ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። 

የአውሮፓ ኅብረት በዉጪ ግንኙነት ኃላፊው ጆሴፕ ቦሬል እና የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነሩ ያኔዝ ሌናርቺች በኩል፤ እንዲሁም አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ምኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከን አማካኝነት ባወጧቸው መግለጫዎች የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ለቀው እንዲወጡ በድጋሚ ጠይቀዋል።

"የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ አሁንም መገኘት የኢትዮጵያን መረጋጋት እና ብሔራዊ አንድነት ጥያቄ ላይ ይጥላል" ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ይኸንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ከዚህ ቀደም ሁለቱ አገሮች በተደጋጋሚ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም “ለተግባራዊነቱ ምንም እንቅስቃሴ አላየንም” ሲሉ ወቅሰዋል። 

ከስድስት ወራት በላይ ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት እጃቸው ያለበት "ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች ደሕንነት ጥበቃ፣ ሁሉንም ግጭት በአፋጣኝ ለማቆም፣ ለተቸገሩ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ የሚፈቅዱትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋት ውስጥ የሚገኙ ግዴታዎቻቸውን እንዲወጡ" ጠይቀዋል።  አንቶኒ ብሊንከን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል ባወጡት መግለጫ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ረገድ ለግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሙሉ እና ያልተገደበ እንቅስቃሴ አሁኑኑ በማመቻቸት ግንባር ቀደም ሚና መጫወት አለበት።            

"በትግራይ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጾታዊ ጥቃት፣ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጭካኔዎች ለመፈጸማቸው በርካታ ተዓማኒ መረጃ" መኖሩን የገለጹት ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ በተለይ በኤርትራ ወታደሮች እና በአማራ ክልል ኃይሎች ተፈጽመዋል ያሏቸውን “አስከፊ” ብለዋቸዋል። 

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለተፈጸሙ ግፎች ኃላፊነት ያለባቸውን ተጠያቂ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት የአማራ ክልል ኃይሎችን ከትግራይ እንዲያስወጣ፤ የምዕራባዊ ትግራይ ቁጥጥር በትክክል አብርሃም በላይ ወደሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር መመለሱን እንዲያረጋግጥ ጭምር ጠይቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ