በኢትዮጵያ አዲሱ የአሜሪካ አምባሳደር እና አቋሟቸዉ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 2015አዲሱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በርካታ ስራወች መሰራት እንዳለባቸው ገለጹ። እየተባባሰ የሄደው አለመረጋጋትና በብሄር ላይ የተመሰረተው የእርስ በርስ ግጭት ሃገሪቷን ወደባሰ ቀውስ ውስጥ እየከተታት እንደሆነ የተቆሙት አምባሳደሩ መሰረታዊ የሚባሉ ዲሞክራሲያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆንና በጦረነቱ ወቅት ለተሰሩ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚያደርገው የሽግግር ፍትህ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።
አዲሱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር በርካታ ስራወች መሰራት እንዳለባቸው ገለጹ። እየተባባሰ የሄደው አለመረጋጋትና በብሄር ላይ የተመሰረተው የእርስ በርስ ግጭት ሃገሪቷን ወደባሰ ቀውስ ውስጥ እየከተታት እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደሩ መሰረታዊ የሚባሉ ዲሞክራሲያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆንና በጦርነቱ ወቅት ለተሰሩ ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚያደርገው የሽግግር ፍትህ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።
አምባሳደር ማሲንጋ በም/ል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማዕረግ የአፍሪካ ቢሮና የደቡብና ምዕራብ ኤዥያ ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል። የፓኪስታን ጉዳዮች ሃላፊ፣ የሱዳን እና የጊኒ ም/ል አምባሳደርም ነበሩ። በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በደህንነትና በንግድ ክፍል ሃላፊነትም በቻይና፣ በአይቮሪኮስት፣ በቺሊና በዶሚኒካን ሪፐብሊክ የአሜሪካ ኤምባሲወች ውስጥ አገልግለዋል።
አምባሳደሩ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ወዳጅነትን እንደምትሻ ገልጸዋል። የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን አጥብቀው እንደሚሰሩም ገልጸዋል። ኢትዮጱያ በታሪኳ ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿ ሰላም መከበር ትሰራ የነበረች ሃገር መሆኗን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ አሁን እየታየ ያለው በዘር ላይ የተመረኮዘ የእርስ በርስ ግጭት ሃገሪቷን ወደሌላ ቀውስ ሊያስገባት በሚችል ደረጃ ላይ መድረሱን አውስተዋል።
ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን፤ ከእርስ በርሱ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተጠያቂነትና ፍትህ መኖሩ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። አሜሪካ ይሄንኑ ጥረት በመደገፍ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ የማስፈን ራዕይን መሰነቋን አምባሳደሩ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጦርነትና በተያያዥ የእርስበርስ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሳቢያ እጀጉን መጎዳቱን አምባሳደሩ ጠቁመው፣ ሃገራቸው በኢኮኖሚው ትብብር በኩልም የበለጠ የተጠናከረ ግንኙነት ማድረግ ላይ እንደምትሰራ ቃል ገብተዋል። ቻይና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ውስጥ እጅጉን እየሰፋ የመጣ ተጸዕኖ መፍጠሯን ያስታወሱት አምባሳደሩ የቻይና የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያን የማይጠቅም መሆኑን ለማሳየት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በእናታቸው ከሉዚያና ግዛት በአባታቸው በኩል ደግሞ ከአፍሪካዊቷ ሞዛምቢክ ቤተሰብ የተገኙት አዲሱ የአሜሪካ አምባሳደር ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ እና ማንዳሪን ቋንቋወችን ይናገራሉ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በውጪ ግንኙነት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደሞ በህዝብ አስተዳደር ሰርተዋል።
አበበ ፈለቀ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ