በካማሺ ዞን ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል
እሑድ፣ ታኅሣሥ 21 2016በካማሺ ዞን ሶጌ ከተማ የደረሰው የታጣቂዎች ጥቃት
በካማሺ ዞን ቦሎጅጋንፎይ ወይም ምዥጋ ወረዳ ውስጥ ከትናንት በስቲያ ታጣቂዎች በመግባት ባደረሱት ጥቃት የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል፡፡ በወረዳው የሚገኙ ሁለት ባንኮች የአዋሽ ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች መዘረፋቸውን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞትሌ እምዬ ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ለደረሰው ጉዳትም ኃላፊው በሸኔ ስም የሚንቀሳቀሱ ሐይሎችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ መንግስት ሼኔ ብሎ የሚጠራቸውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራ ቡድን ሃሳብ ለማካተት የተደረገው ጥረት አልሰመረም ።
በሶጌ ከተማ በደረሰው ጥቃት የፖሊሲ ጣቢያና በርካታ ተሽከርካሪዎች ወድመዋል
ከትናንት በስቲያ አርብ ታህሳስ 19/2016 ዓ.ም በቦሎ ጅጋንፎይ/ምዥጋ ወረዳ ሶጌ ከተማ ጠዋት ታጣቂዎች ወደ ከተማው በመዝለቅ ከፍተኛ መድመት ማድረሳቸውን ነው የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞትሌ እምዩ የተናገሩት፡፡በከማሺ ዞን የመንገድ መዘጋት ኅብረተሰቡን ለችግር አጋልጧል በሰው ህይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የተለያዩ መጠን ያላቸው 8 ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ገልጸዋል፡፡ በወረዳው የነበሩ ጸጥታ አስከባሪዎች ለግዳጅ ወደ ለላ ስፋራ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ታጣቂዎቹ በቀላቀሉ ወደ ወረዳው በመግባት ጥቃት ማድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡ በዕለቱ ለ3 ሰዓታት ያህል ከተማውን ተቆጣጥረው እንደነበርና በሶጌ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አንድ ፖሊስ ጣቢያ መቃጠሉን፣ ሁለት በንኮችም መዘረፋውንና ሌሎችም በርካታ የመስሪያ ቤት ንብረቶች መዘረፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በዛሬው እለት በከተማው መረጋጋት መኖሩንና ከአካባቢው ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎችም እየተመለሱ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በወረዳው ያነጋገርናቸው ሁለት ነዋሪዎች በዕለቱ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ስለነበር አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ አካባቢውን ለቀው ሸሽተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በወረዳው አንድ ፖሊስ ጣቢያ መቃጠሉንና የቁም እንስሳትን ጨምሮ የንብረት ዝርፍያ መፈጸሙን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡ አምስት ተሸከርካሪዎች በአንድ ስፋራ መቃጠሉን የገለጹ ሲሆን መጠናቸው ያልታወቀ ሌሎች የወረዳው ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መወሰዱን አብራርተዋል፡፡ ጥቃቱን በመሸሽ ላይ የነበሩ 4 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን እንደሚያውቁም ጠቁመዋል፡፡ በወረዳው በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ሐይሎች መግባታቸው የገለጹት ያነጋርናቸው ነዋሪዎች በአካባቢው አሁንም ወደ ቤታቸው ያልተመለሱ የሸሹ ነዋሪዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ከሁለት ወራት በላይ ስልክና ኢንተርኔት የተቋረጠበት ካማሺ ዞን
አርብ ዕለት በሶጌ ከተማ የደረሰውን ጥቃት በወረዳው አቅራቢያ ይንቀሳቀሳሉ ያሏቸው የሼኔ ታጣቂዎች መፈጸማቸውን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ደርሰዋል የተባለው ጥቃት ጋር ተያይዞ ስማቸው የተጠቀሰው መንግስት ሼኔ የሚላቸውና ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠሩ ሀይሎች ሀሳብ ለማካተት ያደረኩት ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ በካማሺ ዞን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከክልሉ መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ በአካባቢው ሰላም መስፈኑን የክልሉ መንግስት ከዚህ ቀደም ገልጸዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ታምራት ዲንሳ