1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮሮና ቀውስ ጥላ ብቅ ያለው «እስላማዊ መንግስት»

ዓርብ፣ ሰኔ 12 2012

​​​​​​​ከአንድ ዓመት በፊት ሶሪያ ባጎዝ ላይ ከተደረገው ጦርነት በኋላ ነበር እራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ የሚጠራው ቡድን የካሊፋት ግዛት ማክተሙ የተነገረው። የካሊፋቱ ግዛት ኃያል በነበረበት ጊዜ ስምንት ሚሊዮን ነዋሪዎችን ተቆጣጥሮ አሰቃቂ ድርጊቶችን ሲፈጽም ነበር። ቡድኑ በኮሮና አጋጣሚ ዳግም እያንሰራራ ይኾን?

https://p.dw.com/p/3e0ko
Explosion eines Tanklasters in Syrien
ምስል AFP

በኮሮና አጋጣሚ ዳግም እያንሰራራ ይኾን?

በኤፍራጠስ ወንዝ ሸለቆዎች፥ ሶርያ ድንበር አካባቢ በተደረገው ብርቱ ፍልሚያ ነበር መካከለኛው ምስራቅን ሲያሸብር የቆየው እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው አክራሪ ቡድን የካሊፋት ግዛት ፍጻሜ የተነገረው። «እስላማዊ መንግስት» በአጭሩ «አይ ኤስ» የተሰኘውን ቡድን የመሰረተው አቡ ባክር ኧል ባግዳዲ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ከተገደለ በኋላ ቡድኑም እንደተንኮታኮተ የተነገረው ብዙም ሳይቆይ ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቡድኑ ኢራቅ ውስጥ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን መፈጸም ጀምሯል። ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ ቢያንስ 14.000 የአይ ኤስ አሸባሪዎች እንደሚገኙ ይነገራል። የተበታተኑ ቀሪ ተዋጊዎችን ደምስሶ ጸረ «እስላማዊ መንግሥት» ዘመቻውን ከፍጻሜው ለማድረስ የኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽ እንቅፋት መፍጠሩ አልቀረም። እናስ «አይ ኤስ» በዚህ አጋጣሚ ራሱን ዳግም እያጠናከረ ይኾን?

«የአጥፍቶ ጠፊ ፈንጂ በግልጽ የታጠቀ ሰው ከተሽከርካሪው ወርዶ በተረጋጋ ኹኔታ ወደ ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሕንጻ አመራ። የጸጥታ ኃይላት ሰውዬው ባለበት እንዲቆም ጮክ ብለው ቢናገሩም፤ ከቊብም አልቆጠራቸው። የተኩስ ሩምታ መክፈት እንደጀመሩ በወገቡ ዙሪያ በታጠቀው ፈንጂ ራሱን አነጎደ።» ሚያዝያ ወር ላይ ነበር ይኽን የሽብር ድርጊት በዐይኔ ተመልክቻለሁ ያለ እማኝ የተናገረው።

ሰሜን ኢራቅ ኪሩክ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ የፍንዳታ ጥቃት ሦስት የደኅንነት ባልደረቦች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ በሌላ ጥቃት የሺዓ ሚሊሺያ ቡድን ዐሥር አባላት እዛው ሰሜናዊ ኢራቅ ውስጥ ተገድለዋል። የአይኤስ አባላት መሪያቸው ተገድሎ ቡድናቸው ቢዳከምም የተናጠል የሽብር ጥቃቶችን ግን ማካኼዳቸውን ቀጥለዋል። የኢራቅ ርእሰ-ብሔር ሙስጣፋ ኧል ካጂሚ ቀሪ የቡድኑ አባላት ላይ ዳግም ጦርነት ዐውጀዋል።

 Explosion eines Tanklasters in Syrien
ምስል AFP

«ጦርነቱን መክፈታችን አይቀርም፤ እኔም በግንባር ከሚሰለፉት ቀዳሚው እኾናለሁ። አይኤሶችን የምላቸው፦ የጦርነቱ ጊዜ ተቃርቧልና ጠብቊን ነው።»

ከምንም በላይ ታዲያ የ«እስላማዊ መንግስት» ታጣቂዎች ኢራቅ ውስጥ በየመንገዱ ባጠመዷቸው ፈንጂዎች እና አነስተኛ የጥበቃ ኬላዎች ላይ በሚያደርሷቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች መኖራቸውን ዕያሳዩ ነው። ሚያዝያ ወር ላይ ቡድኑ ከአንድ መቶ በላይ ጥቃቶችን መፈጸሙን ዐስታውቋል። ያም ከዚያ ቀደም ብለው ከነበሩት ሦስት ወራት ከወሰዳቸው ጥቃቶች እጥፍ ነው። ጥቅምት፣ የካቲት እና መጋቢት ወራት ውስጥ በአማካይ ወደ 50 የሚጠጉ የሽብር ጥቃቶች በአይ ኤስ ቡድን ተፈጽሟል። የኢራቅ የፀጥታ ኃይላት ቡድኑ ላይ ብርቱ ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት በቅርቡ ነው። ሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ ውስጥም ቢኾን አሸባሪ ቡድኑ ዳግም ለማንሰራራት ጥረት ማድረጉን አብላጫ የኩርድ ሚሊሺያዎች ያሉበት የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት (SDF) ቃል አቀባይ ኪኖ ካብሪል ይናገራሉ።

«እስላማዊ መንግሥት ቡድን ከዚህ ቀደም ያጣውን ይዞታ ለማጠናከር እና እንደ አዲስ ለመደራጀት ጥረት እያደረገ መኾኑ የሚታወቅ ነው። በተለይ ደግሞ ባጎዝ ውስጥ ከተደረገው ከባድ ውጊያ በኋላ። ባለፉት ስድስት ወራት ግን የአባላቱ ቊጥር እየጨመረ ነው። አይ ኤስ በኤፍራጠስ ደቡብ እና ምዕራብ ክፍሎች እራሱን በማጠናከር ላይም ይገኛል። ከዚያ በተጨማሪ አይ ኤስ በኢራቅ ረባዳማ ሥፍራዎች፤ በሶሪያ እና ኢራቅ ድንበር እንዲሁም በሰሜን እና ሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ ግዛቶች በተደጋጋሚ ብቅ ይላል።»

የመንግሥት ኃይል የተዳከመባቸው እና አለመረጋጋት የሰፈነባቸው ሥፍራዎች ለ«እስላማዊ መንግሥት» ታጣቂዎች የሚመቹ ናቸው ይላሉ በሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ ቃሚሽሊ ከተማ ነዋሪ የኾኑት የፖለቲካ ሳይንስ ምሑሩ ዖስማን ዓሊ።

«አኹንም ተደጋጋሚ ግጭቶች አሉ አይ ኤስ ሊጠቀምባቸው የሚፈልጋቸው። ባግዳድ ውስጥ የመንግሥት ግንባታው ሒደት ላይ የታየው ክፍተት አይ ኤስን አጠናክሮታል። የጸጥታ ኃይላት መዳከምም ለአይ ኤስ መንገዱን ሊጠርግለት ችሏል።»

Nordsyrien  Sanjak Saadoun Abzug YPG Einheiten
ምስል Getty Images/AFP/D. Souleiman

ሶሪያ በተለይ ሰሜን እና ሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ አኹንም ድረስ ሰላም እንደራቃቸው ናቸው። ከፀጥታው ባሻገር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በራሱ ለአይኤስ ነገሮችን ያመቻቸ ይመስላል። እንቅስቃሴ በታገደባቸው ቦታዎች የፀጥታ ኃይሉ መኖር ለአይኤስ አጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት በቀላሉ እንዲጋለጥ ያደርገዋል። አሸባሪ ቡድኑ የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋትን አባላቱ በመጠቀም የመንግሥት ወታደሮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ጥሪ አስተላልፏል።

የአጥፍቶ ጠፊ የሽብር ጥቃቱ ታዲያ በአውሮጳ እና ሌሎች ቦታዎችም እንዲፈጸም ይሻል። የአይ ኤስ አባላትንም ከእስር ማስለቀቅ ይፈልጋል። ወደ ዐሥራ አንድ ሺህ የአይኤስ አባላት እና በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሚስቶቻቸው እና ልጆቻቸው የሶሪያ ኩርዶች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች ይገኛሉ። በሶሪያ ኩርዶች ተነጥለው የሚገኙት እነዚህ የአይኤስ አባላት በየጊዜው አነስተኛ ውጊያዎችን ለመፍጠር ይጣጣራሉ። አንዳንድ ጊዜም የተሳካላቸው ከበባውን ሰብረው ወደ ሶሪያ እና ኢራቅ ድንበር ገብተው ይሰወራሉ።

እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራው ቡድንን ለመውጋት የተጣመረው 82 አባላት ያሉት ዓለም አቀፍ ስብስብም በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ወደ ጦር ሰፈሩ ገብቶ ከትሟል። እነዚህ ጉዳዮችን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ካልሰጣቸው ቡድኑ ዳግም በመጠናከር ዓለም አቀፍ ስጋት ወደ መኾን ይሻገራል ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ