1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኪነ ጥበብኢትዮጵያ

በዓለም ሲኒማ ሲታይ የነበረው የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” ቴአትር ታገደ

Eshete Bekele
ሐሙስ፣ ጥር 2 2016

በአዲስ አበባ ላለፉት ሁለት ወራት ሲታይ የነበረው “ቧለቲካ” ቴአትር መታገዱን የአዘጋጆቹ የቅርብ ሰዎች ለዶይቼ ቬለ አረጋገጡ። ቴአትሩ የታገደው “የመንግሥት ሰዎች ነን” የሚሉ በሰጡት ትዕዛዝ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። “ቧለቲካ” በጦቢያ ፖኢቲክ ጃዝ መድረክ ላይ የተጀመረው የእያዩ ፈንገስ ጉዞ ሦስተኛ ምዕራፍ ነው

https://p.dw.com/p/4b8ru
አዲስ አበባ
እያዩ ፈንገስ ላለፉት አስር ዓመታት መድረክ ላይ ቆይቷል።ምስል Eshete Bekele/DW

በዓለም ሲኒማ ሲታይ የነበረው የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” ቴአትር ታገደ

የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” ቴአትር በዓለም ሲኒማ እንዳይታይ መታገዱን የአዘጋጆቹ የቅርብ ሰዎች ለዶይቼ ቬለ አረጋገጡ። ላለፉት ሁለት ወራት በዓለም ሲኒማ ሲታይ የቆየው ቴአትር እንዳይታይ መታገዱን የሚገልጽ መረጃ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ከተሰራጨ በኋላ በበርካቶች ዘንድ ሐዘኔታ ፈጥሯል።

“የመንግሥት ሰዎች ነን” የሚሉ ለዓለም ሲኒማ በሰጡት ትዕዛዝ “ቧለቲካ” እንዳይታይ መታገዱን አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ እና ጉዳዩን በቅርብ የሚያቁ ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለሙያ “ሕዝብን የሚያሳምጽ ነው። ከዚህ በኋላ እንዳታሳዩ” የሚል ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ዶይቼ ቬለ ከዓለም ሲኒማ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። ወደ ጸሐፊው በረከት በላይነህ እና ተዋናዩ ግሩም ዘነበ ስልኮች ያደረገው ጥሪም ምላሽ አላገኘም። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የመረጃ ምንጭ ትዕዛዙን ስለሰጡ ሰዎች ማንነት “መረጃው የለንም። ሲኒማ ቤቱን ነው እንደዚያ ያሉት እንጂ ወደ ሙያተኞቹ የመጡበት መንገድ የለም” ሲሉ አክለዋል።

የሚጨሰዉ ጠረጴዛ እና የሥነ-ጥበብ ባለሙያዉ

በበረከት በላይነህ ተጽፎ ግሩም ዘነበ የሚተውነው “ቧለቲካ” ሁለት ሰዓት ገደማ የሚረዝም ነው። የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” የአንድ ሰው ተውኔት ነው። ከጥቅምት 15 ቀን 16 ጀምሮ በሣምንት ሁለት ቀናት ማለት ሐሙስ እና እሁድ ሲታይ ቆይቷል። የተውኔቱ ዋና ገጸ ባሕሪ እያዩ የኢትዮጵያን ጉዳዮች እያነሳ የሚሳለቅበት ቴአትር በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ነበር።

“ሌብነትን ነው የሚተቸው። ሥርዓት ደግሞ ይተቻል። ዛሬም፣ ትናንትም ወደፊትም ሥርዓትን ትተቻለህ። ሌብነትን ትተቻለህ። እንዲህ ካልሆነ ደግሞ መንግሥት በአግባቡ ሀገርን ለመምራት [አይቻልም።]” ሲሉ ዝግጅቱን በቅርብ የሚያውቁት ባለሙያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ አበባ
የእያዩ ፈንገስ “ቧለቲካ” በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ዓለም ሲኒማ በሣምንት ሁለት ቀናት ሲታይ ቆይቷልምስል DW

“ይኸ መዝናኛ ነው። በቀልድ በዋዛ እያደረክ ለሕብረተሰቡ መልዕክትህን ታስተላልፋለህ” የሚሉት ባለሙያ ይኸ ቴአትር “ቢቻለው መንግሥት ይማርበት ነበር” የሚል አቋም አላቸው።

እያዩ ፈንገስ ወደ አዲስ አበባ መድረኮች ብቅ ካለ ዐሥር ዓመታት አስቆጥሯል። ገጸ ባህሪው ከተውኔት ወዳጆች የተዋወቀው ግጥም፣ የጃዝ ሙዚቃ እና የተለያዩ ግለሰቦች ዲስኩር ተሰባጥረው ይቀርቡበት በነበረው የራስ ሆቴል መድረክ ነበር። “ቧለቲካ” በጦቢያ ፖኢቲክ ጃዝ መድረክ ላይ የተጀመረው የእያዩ ፈንገስ ጉዞ ሦስተኛ ምዕራፍ ነው። ከዚህ ቀደም “ፌስታሌን” እና “አጀንዳዬን” የሚል ርዕስ የተሰጣቸው ሁለት ምዕራፎች ለዕይታ በቅተዋል።

ፈንድቃ በዓለም ሃገራት መድረክ

በሦስቱም ተውኔቶች በኃይል የሚናገረው፣ የሚተቸው እና የሚሳለቀው እያዩ ፈንገስ መምህር የነበረ ነው። ምሬት እና ስላቁ ከገጣሚ ነፍሱ ጭምር የሚቀዳ ነው። መገፋቱ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታዘበው መቋሰል ኃይለኛ ተናጋሪ አድርጎታል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለሙያ “ራስ ሆቴል ሲያዘጋጁ እንደዚህ አይነት የመንግሥት ሰዎች ነን እያሉ የሚመጡ ነበሩ እና ማስፈራራት የሚያሳዩ ሰዎች ነበሩ። መንግሥትን ይወክሉ አይወክሉ አናውቅም። አሁንም ያለው ነገር ያ ነው” ሲሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጫና እንደነበር አስረድተዋል።

እያዩ ፈንገስ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአሜሪካ እና በካናዳ መድረኮች ለአንድ ዓመት ገደማ ታይቷል። የተውኔቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት የአዘጋጆቹ የቅርብ ሰው ውሳኔው “የተዋናይ እና የጸሐፊው” እንደሚሆን ተናግረዋል።

ተውኔቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተዘወተረ በመጣው ማኅበራዊ ድረ ገፆች ብቅ ሊል እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። ከዚህ ቀደምም ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረው  እና ተመልካቾችን ያፈራው “ምን ልታዘዝ” የተባለ ድራማ በቴሌቭዥን መተላለፍ ሲቆም በዩቲዩብ በኩል ብቅ ብሎ ነበር።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ