1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ምዕራብ ክልል የትምህርት ማስረጃን ያጭበረበሩ ላይ ርምጃ ተወሰደ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 17 2015

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ያላቸውን ስምንት የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ 218 ሰዎችን ከሥራ አባረረ።

https://p.dw.com/p/4LQrA
Symbolbild gekaufter Doktortitel
ምስል dpa

የሀሰት ትምህርት ማስረጃ መዘዝ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ያላቸውን ስምንት የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ 218 ሰዎችን ከሥራ አባረረ። በክልሉ በሐሰተኛ የትምህርት ሰነድ መገልገል በስፋት እየተለመደ መምጣቱን የተናገሩት የዶቼ ቬለ DW ምንጮች በአሁኑወቅት ከ10ኛ ክፍል ሐሰተኛ ዲግሪ አሠርተው የተቀጠሩ በርካታ ሠራተኞች መኖራቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። የክልሉ አመራሮች ከችግሩ የጸዱ ሆነው አለመገኘታቸው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጥራት ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑንም ምንጮቹ ተናግረዋል።

የትምህርት ማስረጃ ማጭበርበር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚገኙ መንግሥታዊ መዋቅሮች ሐሰተኛ የትምህርት ሰነዶች መበራከት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዶቼ ቬለ ምንጮች ገልጸዋል ፡፡ ምንጮቹ እንደሚሉት በክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ደጃፍ ረግጠው የማያውቁ ግለሰቦች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን በማቅረብ በዲግሪ ሲቀጠሩም ሆነ ለከፍተኛ ሹመት ሲታጩ ማየት አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል ፡፡ በዎላይታ ዩኒቨርሲቲ ተርጫ ካምፓስ በመምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ አባተ ኡቃ ለአጭር ጊዜ በክልሉ ዳውሮ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በኃላፊነት መሥራታቸውን ይናገራሉ ፡፡ አቶ አባተ በቆይታቸው በክልሉ «አስደንጋጭ» ያሉትን የትምህርት ማስረጃዎች ማጭበርበር መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ከፍተኛ የተጭበርበሩ ወይም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ይገኛሉ ያሉት አቶ አባተ «ከ10ኛ ክፍል ሐሰተኛ ዲግሪ አሠርተው የተቀጠሩ በርካታ ሠራተኞች እንደሚገኙ አውቃለሁ ፡፡ ሕጋዊ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ሠራተኞች የሥራ መደቦቻቸው በሐሰተኖቹ እየተያዙ ይገኛሉ ፡፡ በተለያዩ ጊዚያት ጥቆማዎች ቢቀርቡም ነካክቶ ከመተው ባለፈ ችግሩን ከመሠረቱ ሊፈታ የሚችል እርምጃ ሲወሰድ አይታይም ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አመራሮች ጭምር የችግሩ አካል ሆነው በመገኘታቸው ነው» ብለዋል፡፡

የሀሰተኛ ትምህርት ሰነድ መነኻሪያዋ የቶጫ ወረዳ 

South West Ethiopia People Region Emblem
ምስል South West Ethiopia People Region government Communication Affairs Bureau

የዶቼ ቬለ ምንጮች እንደሚጠቁሙት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትምህርት ማስረጃዎች ማጭበርበር ደረጃው ቢለያይም በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች የሚስተዋል እውነት ነው ፡፡ በክልሉ በችግሩ ስፋት ረገድ ግን የዳውሮ ዞን ቶጫ ወረዳን የሚስተካከል የለም ነው የሚባለው ፡፡ በወረዳው ሰሞኑን ብቻ በተመረጡ ውስን መሥሪያቤቶች የመጀመሪ ዙር ነው የተባለ የትምህርት ማስረጃዎች የማጣራት ሥራ መከናወኑ ይነገራል፡፡  በወረዳው የማጣራት ሥራ ከተካሄደባቸው 565 የትምህርት ማስረጃዎች ውስጥ 218ቱ ሀሰተኛ ሆነው መገኘታቸውን የቶጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ታዬ ለዶቼ ቬለ በሥልክ ገልጸዋል፡፡ በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ሲሠሩ ከተገኙት መካከል ስምንቱ የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን የተጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው «ተመርቀናል በሚል ማስረጃዎችን ወደ አመጡባቸው  ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ድረስ በመሄድ በተደረገ ማጣራት ተቋማቱ በጭራሽ እንደማያውቋቸው በማህተብ በተደገፈ ደብዳቤ አረጋግጠውልናል፡፡ አሁን ላይ ስምንቱን አመራሮች ጨምሮ ሁሉም ሠራተኞች ከሥራና ከኃላፊነት እንዲነሱ አድርገናል፡፡ ይህ አስተዳደራዊ እርምጃ ነው ፡፡ በቀጣይ በወንጀል በመጠየቅ አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ ማስረጃዎችን ለአቃቢ ሕግ አቅርበናል፡፡ አሁን ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ ይገኛል» ብለዋል ፡፡ 

ቢሮው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት ለምን ዳተኛ ሆነ?   

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተንሠራፍቷል የተባለውን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ለማጥራት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ፡፡ በተለይም በታእታይ የአስተዳደር እርከን የሚገኙት የወረዳ መስተዳድሮች በተጭበረበረ ሰነዶችን ለመመርመር ጥረት እያደርጉ እንደሚገኙ የዶቼ ቬለ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የወረዳ አመራር ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመከላከል በክልል መዋቅር በኩል ተገቢውን ድጋፍ አየተደረገ አይደለም ይላሉ ፡፡ በተለይ ችግሩ በቀጥታ በሚመለከተው የክልሉ የሰው ሀብት ልማትና የመንግሥት አገልግሎት ቢሮ በኩል ዳተኝነት እንደሚስተዋል እኝሁ አመራር ተናግረዋል፡፡ ዶቼ ቬለ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ዙሪያ የክልሉን የሰው ሀብት ልማትና የመንግሥት አገልግሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሥራት ሀዳሮን በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡ ኃላፊው ግን «በግብረ ኃይል እያጣራን ነው» ከሚል አጭር ምላሽ ባለፈ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፤ ፡፡ የቀድሞው አመራርና የአሁኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህር የሆኑት አቶ አባተ ኡቃ ግን በክልሉ አሁንም በርካታ ሠራተኞችና አመራሮች በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየሠሩ እንደሚገኙ መረጃዎች መኖራቸውን ይናገራሉ ፡፡ መረጃዎች ካሉ ክልሉ ለምን እርምጃ መውሰድ ተሳነው በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት አቶ አባተ «ለዚህ ምክንያቱ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው አመራሮቹ እርምጃ ከወሰድን ሥልጣናችንን እንጣለን የሚል ሥጋት አላቸው ፡፡ ምክንያቱም በዙሪያቸው የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች የችግሩ አካል በመሆናቸው ምን አነካካኝ የሚል ሥጋት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ሁለተኛው በይፋ ባይነገረም አሁን በለውጥና በሽግግር ውስጥ የምንገኝ ሥለሆነ ለጊዜው ጉዳዩን አታንሱ ይቆይ የሚል አዝማሚያ በመኖሩ ነው » ብለዋል ፡፡ ዶቼ ቬለ የክልሉ መንግሥት በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ክትትል ላይ ዳተኝነት እያሳየ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ አሁንም የክልሉን የሰው ሀብት ልማትና የመንግሥት አገልግሎት ቢሮ ሃላፊን ጨምሮ ይመለከታቸዋል የተባሉ የክልሉ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ የሚሰጠው አካል አላገኘም ፡፡ 

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ