1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብዙ ሊነገርለት የሚገባው የጡት ካንሰር

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 8 2015

የጡት ካንሰር በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት በሰዎች ላይ የሚገኝ የካንሰር አይነት የሆነ መምጣቱን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ታማሚዎቹ ለህክምና እርዳታ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱት ግን በአብዛኛው ህመሙ ስር ከሰደደ በኋላ መሆኑ ሀኪሞቹን እያሳሰበ ነው።

https://p.dw.com/p/4IIPs
Äthiopien Krebs psychosoziale Selbsthilfegruppe
ምስል Biruck Habtamu

በጥቅምት ወር ስለጡት ካንሰር

በየዓመቱ በጥቅምት ወር ስለጡት ካንሰር በቂ ግንዛቤ እንዲኖር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይካሄዳሉ። ካንሰር ሲባል ብዙዎች በቶሎ የሚያስቡት የማይድን ህመም ነው የሚለውን ነው። ሆኖም ግን በቂ የህክምና አማራጮች ባሉባቸው ሃገራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የጡት ካንሰር ህመም አጋጥሟቸው ታክመው የዳኑት ቁጥር ጥቂት አይደለም። የጡት ካንሰር በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት በሰዎች ላይ የሚገኝ የካንሰር አይነት የሆነ መምጣቱን የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ታማሚዎቹ ለህክምና እርዳታ ወደ ሀኪም ቤት የሚሄዱት ግን በአብዛኛው ህመሙ ስር ከሰደደ በኋላ መሆኑ ሀኪሞቹን እያሳሰበ ነው።

Äthiopien Haramaya University krebszentrum
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ስር ወደሚገኘው የሕይወት ፋና ሆስፒታል የካንሰር ማዕከልምስል Biruck Habtamu

ዶክተር ብሩክ ሀብታሙ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘው ሕይወት ፋና ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ባለሙያ ናቸው። በዚህ ሀኪም ቤት የካንሰር ማዕከል ተከፍቶ ህክምናው በስፋት መሰጠት ከጀመረ ሦስት ዓመት አስቆጥሯል። ሆኖም በሚያክሙበት ስፍራ ኬሞቴራፒ የሚባለው በመድኃኒት የሚሰጠው ህክምና እንጂ የጨረር ህክምና ግን ገና አልተጀመረም። ሌሎች በካንሰር ህክምና ላይ አትኩረው የሚሠሩ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የጡት ካንሰር ብዙዎች ላይ ከሚገኙ የካንሰር አይነቶች ቀዳሚው መሆኑን ዶክተር ብሩክም አስተውለዋል።

Äthiopien Krebs psychosoziale Selbsthilfegruppe
በአዳማ ሆስፒታል ስለካንሰር ህመም እና ህክምና በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ቡና እየጠጡ ውይይት ይካሄዳልምስል Biruck Habtamu/Adama University Hospital

በአካል ላይ ለውጥን መከታተል እንደሚገባ የሚመክሩት የህክምና ባለሙያዎች በተለይ የጡት ካንሰር በሚያሳያቸው አንዳንድ ምልክቶች ፈጥኖ ሊደረስበት እና ታክሞም ሊድን እንደሚችል ይናገራሉ። አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ግን በቂ መረጃ ባለማግኘት ሊሆን ይችላል ይኽን የተገነዘበ አይመስልም። ዶክተር ብሩክም ይህንኑ ያረጋግጣሉ። ለዚህ ደግሞ ሰዎች በቂ መረጃ አለማግኘታቸው ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ። ዶክተር ብሩክ የገለጿቸው ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይበሉ እንጂ ይኽም ብቻ አይደለም ሰዎች በጊዜ ወደ ህክምና እንዳይሄዱ እንቅፋት የሚሆኑት። አለማወቅም በራሱ ሌላቸው ችግር ነው።

Äthiopien Adama University Hospital
የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልምስል Biruck Habtamu/Adama University Hospital

የካንሰር ህክምና ከፍተኛ ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ተፈራ በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። ዶክተር ብሩክ እንደገለጹልን እሳቸው የሚያገለግሉበት ሆስፒታል የካንሰር ማዕከል ዶክተር ቢንያም በአዳማ ሆስፒታል ኅብረተሰቡ ስለካንሰር ህመም እና ህክምና በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ያመቻቹ የመማማሪያ መድረክ ያስገኘው አበረታች ውጤት ለእነሱ ማዕከል አርአያ ሆኗል።  እነ ዶክተር ቢንያም አዳማ ላይ በሁለት ዓመታት ጉዞ የተሻለ ውጤት ያገኙበትን ተሞክሮ መነሻ በማድረግም በሕይወት ፋና ሆስፒታል የካንተር ማዕከልም ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት የካንሰር ታማሚዎች መረጃ የሚለዋወጡበት መድረክ ተቋቁሟል። ዶክተር ቢኒያም ከህክምናው ጎን ለጎን ሰዎች ስለካንሰር ህመም ምንነት ማወቅ እንዲችሉ ሁኔታዎች መመቻቸት ይኖርባቸዋል ባይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ታክመው የዳኑት ወገኖች ትልቅ ሚና አላቸው። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ቀደም ብለው እንዲህ ያለውን ስለካንሰር መረጃ የመለዋወጫ መድረክ ያዘጋጁት ወይዘሮ ሜሮን ከበደ በዚህ ዝግጅት ቀርበው ልምዳቸውን ማካፈላቸው ይታወስ ይሆናል። ወይዘሮ ሜሮን ደጋግመው በራሳቸው ጥረት እና ባካሄዱት ምርመራ የጤና ችግሩ እንደገጠማቸው በማወቃቸው በህክምና ድነው ዛሬ ሌሎችን በማንቃቱ በኩል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ዶክተር ቢንያምም ወይዘሮ ሜሮን ካቋቋሙት ፒንክ ሎተስ ኢትዮጵያ ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸውልናል።

Äthiopien Krebs psychosoziale Selbsthilfegruppe
በአዳማ ሆስፒታል ኅብረተሰቡ ስለካንሰር ህመም እና ህክምና በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ የተመቻቸው የመማማሪያ መድረክምስል Biruck Habtamu/Adama University Hospital

ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ