1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተስፋና ሙግት የሚነሳበት ብሔራዊ ምክክር

ማክሰኞ፣ ግንቦት 29 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚታየው አለመግባባት እየተባባሰ መጥቷል ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ አለመግባባትን የፈጠሩ ጉዳዮችን በመለየት ላይ መሆኑን ያስረዳል ። ኮሚሽኑ ገለልተኛ እና አካታች ነው መባሉን የሚጠራጠሩ የፖለቲካ ፖርቲዎች ግን አሉ።

https://p.dw.com/p/4SGMk
Äthiopien Kommission für den nationalen Dialog
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ትችት ሰንዝረዋል

የተለያዩ የሚገፋፉ ሃሳቦች በተንሰራፉባት ኢትዮጵያ ለዓመታት ታሪክን ጨምሮ በበርካታ ሀገራዊ እሴቶች ላይ ከመግባባት መድረስ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ምስረታ እና ቀጣይ አቅጣጫ ላይም በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሳሰል አቋምና ሃሳብ የላቸውም፡ በነዚህ እና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመፍጠር ብሎም በዜጎች መሃል መስማማት እንዲሰፍን የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም አለመግባባትን የፈጠሩ ጉዳዮችን በመለየት ላይ መሆኑን ያስረዳል፡፡ 

ይሁንና ይህ በአገሪቱ ዜጎችና ወኪሎች ነን ባሉት መካከል መግባባት እንዲፈጠር የተቋቋመው ኮሚሽን ገለልተኛ እና አካታች ነው መባሉን እንጠርጥራለን ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁንም ድረስ በዚህ ተቋም ስር ታቅፈው በምክክሩ የመሳተፉን ጉዳይ የማይመስል እያሉ ያጣጥላሉ፡፡ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ ተጠቃሽ ነው፡፡ የፓርቲው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይህንን አስመልክተው ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ “ምክከር ካልተደረገ የትም መድረስ እንደማይቻል ከኢህአዴግ ዘመን ጀምሮ ስንጠይቅ ነበር፡፡ በመሃል ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በረራሱ መንገድ ኮሚሽን ፈጥሮ ወደ ስራ አስገባ፡፡ እኛ ህን ሂደት ነው የተቃወምነው፡፡ አሁንም ብሆን ሰፊ ተደማጭነት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ተካተቱበት ብሔራዊ ምክክር አስፈላጊነቱ ላይ ጥርጣሬ ባይኖረንም አሁን በሚገፋበት መንገድ ግን ውጤት ይመጣል የሚለውን አናምንም፡፡”

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጽ/ቤት
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጽ/ቤትምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ራሔል ባፌ በፊናቸው በኮሚሽኑ የአመሰራረት ሂደት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ይሁንና “ጉዳዩ የአገር ጉዳይ እንደመሆኑ ከመገለል መፍትሄው ተቀራርቦ መነጋገር ነው” የሚለውን አስተያየታቸውን ያክላሉ፡፡ የምክክር ኮሚሽኑን አመሰራረት ሂደት በመቃወም የገለልተኝነትና አካታችነት ሁኔታውም ላይ ጥያቄ አለን ያሉ ቁጥራቸው ከ10 በላይ እንደሆነ የሚገለጸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከፓርቲዎቹ ምክር ቤት ያስወጣቸውም ይህ ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ፕሮፌሰር መረራም ይህንን አልሸሸጉም፡፡ “በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ላይ የተቋቋመው ኮሚሽን አስፈላጊነት እና ገለልተኝነት ላይ የተለያዩ አቋም ስለተያዘ እና ወጥተን የሃቀና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ መስርተናል፡፡” 

ሊደረግ የታቀደው ብሔራዊ ምክክር ገለልተኝነቱና አካታችነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባት እንደሌለበት የሚያነሱት ዶ/ር ራሔር ባፌ ግን የምክክር ሂደቱን ተቃውመው ኮከስ የፈጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶችንም ወደ ምክክሩ ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ባይ ናቸው፡፡ “መሰረታዊ ጉዳይ መሆን ያለበት ይህ ብሔራዊ ምክክር የመንግስት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይሆን የህዝብ መሆኑን ህዝቡ እንዲቀበል በዚያ ላይ መተማመንም እንዲኖር መሰራት አለበት፡፡”

በአገራዊ ምክር ጉዳዩ ላይ ሰሞኑን ለሳምንት ያክል በአውሮፓ በተለያዩ አገራት የልምድ ልውውጦች ሲደረግ ተሳትፈው እንደነበር ያወሱት ፕሮፌሰር መረራ ግን፤ በምክክር ኮሚሽኑ የሚመራው ውይይት ቢያንስ ገለልተኝነቱ እና አካታችነቱ ሲረጋገጥ ብቻ ዓለማቀፍ መስፈርቱን ያሟላል ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቅርቡ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሲዳማ ክልሎች ውስጥ የውይይት ሂደቱን መጀመሩን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ፓርቲዎች በሚያነሱት ቅሬታን በተመለከተ ለኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ዶ/ር ዮናስ አዳዬ በተደጋጋሚ ደውለን አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ