1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ መመለሳቸው

ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2016

በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ አላማጣ እና ሌሎች አካባቢዎች መመለስ መጀመራቸው ተገለፀ። ትናንት ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ ከተማ መመለሳቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል። ተመላሾቹ ደህንነታቸውን ከማስጠበቅ በተጨማሪ ሰብአዊ ድጋፍም እንዲቀርብላቸው ጥሪ ያቀርባሉ።

https://p.dw.com/p/4iTg9
የመጠለያ ጣቢያ ሽሬ
ሽሬ የተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ፎቶ ከማኅደርምስል Million Haileselasie/DW

ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ አላማጣ መመለሳቸው

በጦርነቱ ምክንያት በተለይም ከትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከፌደራል መንግሥት ጋር በተደረሰ መግባት መሠረት ወደ ትግበራ መሸጋገሩን የሚገልፀው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፥ ባለፉት ሳምንታት ወደ ፀለምቲ፣ ከትናንት ጀምሮ ደግሞ ወደ አላማጣ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቃዮች መመለስ መጀመራቸውን ይገልፃል። በመኾኒ፣ ማይጨው እና ሌሎች መጠለያዎች የነበሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከትናንት ጀምሮ ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው አላማጣ መመለስ እንደጀመሩ የገለፁልን በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ፥ ትናንት ብቻ ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወደ ቀዬው መመለሱን፥ ዛሬና በቀጣይ ቀናትም የቀሩትን ተፈናቃዮች ለመመለስ ሂደት ላይ መሆናቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ።

ትናንት ከመኾኒ መጠለያ ጣብያ ወደ ቀዬአቸው አላማጣ ከተማ ከተመለሱት መካከል ያነጋገርናቸው አቶ አለባቸው ስዩም፥ ከረዥም ጊዜ አስቸጋሪ የመጠለያ ስፍራ ኑሮ በኋላ ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ደስታ ፈጥሮባቸዋል።

በተመሳሳይም ከሰሜን ምዕራብ ዞን ተፈናቅለው በእንዳባ ጉና መጠለያ የነበሩ እና አሁን ላይ ወደ ቀዬአቸው ፀለምቲ ወረዳ ማይዓይኒ አካባቢ የተመለሱት አቶ መልካሙ ዘውደ፥ በአካባቢያቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፀጥታ ማስከበር ሥራ እየከወነ መሆኑ ይገልፃሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተፈናቃዮች የመመለስ ሂደቱ «ፅንፈኛ» ያሉት ኃይል ለማስተጓጐል ጥረት እያደረገ ነው በማለት ለዶቼቬለ የገለጹት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ ፤ አክለውም ሁኔታው ለፌደራል የፀጥታ አካላት መገለፁንም አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ያሉት ዜጎች የሚያነሱት ጥያቄ የሰብአዊ እርዳታ እና የማቋቋሚያ ድጋፍ ነው። ተመላሾቹ ባዶ እጃቸውን ወደ የቤታቸው መግባታቸውን በመግለፅ አስፈላጊ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጥሪ ያቀርባሉ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ከራያና ፀለምቲ በተጨማሪ ሁሉንም የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተሠራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ