1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮችና አዲስ ዓመት በመቐለ

ማክሰኞ፣ መስከረም 1 2016

ተሰናባቹ 2015 ዓመት በትግራይ ክልል ካለፉት ዓመታት የቀጠለ ጦርነት የነበረበት፣ በዚያው በአሮጌው ዓመት ደም አፋሳሹ ጦርነት ያስቆመ ስምምነት የተደረሰበት እና የሰላም ተስፋ የተፈጠረበት ነበረ። ለረዥም ግዜ ተዘግተው የነበሩ የስልክ እና ኢንተርኔት ጨምሮ የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎቶች ዳግም የተጀመሩበት ነበር።

https://p.dw.com/p/4WFnG
የአዲስ ዓመት መገለጫ አደይ አበባ
የአዲስ ዓመት መገለጫ አደይ አበባ መስተዋቱ ላይ ይታያል ምስል Million Hailesilassie/DW

ተፈናቃዮችና አዲስ ዓመት በመቐለ

የተገባደደው 2015 ዓመተ ምህረት በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ያበቃበት እና ተስፋ ሰጪ የሰላም ዕድል የተፈጠረበት ነበር። በሌላ በኩል መፍትሔ ያልተሰጠው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው አለመመለሳቸው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። ይህም የነበረውን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተባብሶ እንዲቀጥል እና ወደ ሌላ ዓመት እንዲሻገር አድርጎታል። በትግራይ ክልል ያሉ ተፈናቃዮች አዲሱን ዓመት ከዘላቂ ሰላም ተስፋ ጋር ተቀብለውታል። 

ተሰናባቹ 2015 በትግራይ ካለፉት ዓመታት የቀጠለ ጦርነት የነበረበት፣ በዚያው በአሮጌው ዓመት ደም አፋሳሹ ጦርነት ያስቆመ ስምምነት የተደረሰበት እና የሰላም ተስፋ የተፈጠረበትነበረ። ለረዥም ግዜ ተዘግተው የነበሩ የስልክ እና ኢንተርኔት ጨምሮ የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶች ዳግም የተጀመሩበት እንዲሁም በርካታ አወንታዊ ክስተቶች የተስተዋሉበት ተደርጎ በብዙዎች የሚታወስ ቢሆንም፤ በአንፃሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ያልተመለሱበት፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ተባብሶ የቀጠለበት ሁኔታም የዓመቱ ሌላኛው ገፅታ ተደርጎ ይታያል። በአዲሱ ዓመት 2016 ዓመተምህረት መግብያ ያነጋገርናቸው በትግራይ ያሉ ተፈናቃዮች፣ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች እና ሌሎች በአዲሱ ዓመት የተጀመረው የሰላም ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። በመቐለ ከተማ 70 ካሬ ተብሎ በሚታወቅ የተፈናቃዮች መጠልያ ጣቢያ ያገኘናቸው ተፈናቃይ ዜጎች የአዲሱ ዓመት ምኞታቸው ገልጸዋል። አስመረት ታፈረ ከሰቲት ሑመራ የተፈናቀሉ እና አሁን ላይ በመቐለ መጠልያ ያሉ እናት ናቸው። ያሉበት ሁኔታ ሲያስረዱ "መኖር ከባድ ነው፣ ከሞቱት በላይ በሕይወት ካሉ በታች ሆነን እየኖርን ነው። ረድኤት የለ፣ ምን ልበልህ፣ ተናግረህ የማትጨርሰው ችግር ላይ ነን። ሰው ቤት እንኳን እንዳንገባ ህዝቡ ራሱ ምንም የለውም። የመቐለ ህዝብ ነበር የሚረዳን፤ ልብስ የሚሰጠን፣ አሁን ህዝቡ ራሱ ችግር ላይ ነው። ምን ያድርግ። የምንለብሰው የለንም፣ የምንበላው የለንም፣ የምንጠጣው የለንም፣ ረድኤት ከተሰጠን ሰባት ስምንት ወራት አልፏል" ይላሉ። 

ተፈናቃይ ሕጻናት በመቐለ መጠለያ ጣብያ
ተፈናቃዮቹ በአዲስ አመት ወደየቀያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ኑሮአቸውን ለመቀጠል ተስፋን ሰንቀዋልምስል Million Hailesilassie/DW
የመቐለ የተፈናቃዮች ጣቢያ በከፊል
የመቐለ የተፈናቃዮች ጣቢያ በከፊል፤ ከረዥሙ የመጠለያ አዳራሽ ፊት ለፊት በሰማያዊ ፕላስቲክ የተጠጋገነ መጠለያ ይታያል ።ምስል Million Hailesilassie/DW

ሌላዋ ተፈናቃይ ደግሞ "2016 ሰላም ሆኖ ወደ ሀገራችን ተመልሰን ሰርተን የምንበላበት እንዲሆን ነው ምኞታችን። እኛ ድሮውንም ሰርተን ነበር የምንኖረው፣ እርዳታ እንጠብቅም። ሰርተን ነበር የምንኖረው አሁንም ሰርተን መኖር ነው ፍላጎታችን። ይህ እንዲሆን ፈጣርያችንን እንለምናለን" ሲሉ ገልጸዋል። በመቐለ ያነጋገርናቸው ሌሎች ተፈናቃዮችና ነዋሪዎችም በበኩላቸው በአዲሱ ዓመት ተስፋ መሰነቃቸውን ነግረውናል።

ሚልዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ