የታኅሣስ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2016ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከስዊትዘርላንድ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ከቱርክ እስከ ቻይና በትናንትናው ዕለት በርካታ ድሎችን ተቀዳጅተዋል ። በአንጻሩ፦ «የኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን» ከፓሪስ ኦሎምፒክ በፊት ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮች ላይ ጥብቅ ምርመራ እና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ዐስታውቋል ። የአበረታች ንጥረ ነገር ጣጣው አንድን ሀገር ከዓለም አቀፍ እና ከኦሎምፒክ ውድድሮች ሊያሳግድም የሚችል ነው ። ጉዳዩ ኢትዮጵያንምን ያህል ያሰጋል? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ያልተጠበቀ ክስተት ተስተውሏል ። የቡንደስሊጋውን ዋንጫ በተደጋጋሚ በማንሳት የሚኃወቀው ባየር ሙይንሽን በአይንትራኅት ፍራንክፉርት ሜዳ የግብ ጎተራ ሆኗል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የመሪነቱን ሥፍራ ተረክቧል ። በአራት ጨዋታዎች ድል ርቆት የቆየው ማንቸስተር ሲቲ ወደ ማሸነፉ ተመልሷል ። ቸልሲ ሽንፈት ገጥሞታል ።
አትሌቲክስ፦
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ትናንት በተከናወኑ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል ። ሜክሲኮ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የሞንቴሪ ማራቶን፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት በርሃነ ጸጋዬ (2:11:24)ኬንያውያንን እስከ አራተኛ ደረጃ አስከትሎ አሸናፊ ሆኗል ። በዩናይትድ ስቴትስ የሆኖሉሉ ማራቶን ደግሞ፦ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ስንታየሁ ጌታሁን (2:35:16) እና ካሱ ቢተው (2:36:04)የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።
ትናንት በተከናወነው የቻይና የጉዋንጁ ማራቶን በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ድል ተቀዳጅተዋል ። ጉተኒ ሾኔ (2:28:30)፣ ጫልቱ ጪምዴሳ (2:33:13)እና የኔነሽ ጥላሁን (2:37:16)ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አሸንፈዋል ። እዛው ቻይና ውስጥ ትናንት በተካሄደው የኒንግዴ ግማሽ ማራቶን ፉክክር በወንድም በሴትም ኢትዮጵያውያኑ ይስማው ዐየነው (1:06:29)እና መንገሻ አዳነ (1:13:32) አሸናፊ ሆነዋል።
የኅዳር 24 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ቱርክ ውስጥ በተካሄደው እና የብሪታንያዋ ሯጭ ሩት ጄቤት ባሸነፈችበት የመርሲን ማራቶን ደግሞ፦ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች የኔአበባ እጅጉ (2:28:24)፣ እና ፈይኔ ገመዳ (2:28:25)፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። የአራተኛ ደረጃውም የተያዘው በኢትዮጵያዊቷ ሯጭ ከበቡሽ ይስማ (2:28:35) ነው ። በሣዑዲ ዓረቢያ የአል ኮባር የ5 ኪሎ ሜትር ፉክክር ቢኒያም መሐሪ (13:05) እና ብርሃኑ በለው (13:04)1ኛ እና ሁለተኛ ወጥተዋል ። በዚህ ውድድ አትሌት ሐጎስ ገ/ሕይወት እና ይስማው ድሉ የ4ኛ እና 5ኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሁለቱም የገቡበት ሰት (13:09) ነው ።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ መድረኮች ድል ማስመዝገባቸው የማስደሰቱን ያህል የአበረታች ንጥረ ነገር ጉዳይ በኢትዮጵያ እጅግ አሳስቧል ። «የኢትዮጵያ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን» ከጥር ወር ጀምሮ የአበረታች ንጥረ ነገሮች ምርመራና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ዐሳውቋል ። በኢትዮጵያ ቢያንስ ዐሥር አትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገር በመጠቀም ተጠርጥረው እገዳ እና ቅጣት ተላልፎባቸዋል ። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ኤፍ ኤም ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ጉዳዩ እጅግ አስደንጋጭ ነው ይላል ።
ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ የ2023 የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አሸናፊ መሆኗን ዓለማቀፉ የአትሌቲክ ማኅበር ቅዳሜ ዕለት ይፋ አድርጓል ። አትሌት ለተሰንበት ለሽልማት የበቃችው በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10ሺ ሜትር ውድድር ላይ አንደኛ ከወጣች በኋላ ለፈጸመችው ተግባር ነው። በወቅቱ ትውልደ ኢትዮጵያ ኔዘርላንዳዊት አትሌት ሲፈን ሀሰን ውድድሯን ልታጠናቅቅ ጥቂት ሜትሮች ሲቀራት ተደነቃቅፋ ትወድቃለች ። ለተሰንበት እንዳሸነፈች አትሌቷን አቅፋ በማጽናናት ስፖርታዊ ጨዋነት ዐሳይታለች ። ያም ለሽልማት አብቅቷታል ።
እግር ኳስ
«አይንትራኅት ፍራንክፉርት የባየርን ሙይንሽንን አምድ ነቀነቀው» የጀርመን የስፖርት ጋዜጦች ከዘገቡት መካከል አንዱ ነው ። በእርግጥም የባየርን ሙይንሽን አምድ እጅግ ተነቅንቋል ። ቅዳሜ ዕለት በዶይቸ ባንክ ፓርክ ስታዲየም የታደመው ባየርን ሙይንሽን የ5 ለ1 ብርቱ ሽንፈትን አስተናግዶ ተመልሷል ። ጀርመን ውስጥ የስፖርት ዜና፦ «አይንትራኅት ባዬርንን ጉድ አደረገው»፣ «ባዬርን ድባቅ ተመታ»፣ በሚሉ መሰል አስተያየቶች ተጨናንቋል ። በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ለገና እና አዲስ ዓመት ስጦታ የሚገዛበት ጊዜ የመሆኑን አጋጣሚ በመጠቀም፦ «ፍራንክፉርት ለባዬርን አምስት ግቦችን ስጦታ ላከለት» ሲልም ጽፎ ያስነበበ አለ ። ባየርን ሙይንሽን ዮሹዋ ኪሚሽ 44ኛው ደቂቃ ላይ ለማስተዛዘኛ ባገባት አንዲት ግብ መጽናናት የሚችል አይስልም ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከ12ኛው ደቂቃ ጀምሮ እስከ 60ኛው ድረስ አምስት ግቦችን አከታትሎ በማግባት ግዙፉን ባዬርን ጉድ አድርጎታል ።
አሁን የባየርን ሙይንሽን ኃላፊዎች የሚጠብቁት አንድ ነገር ነው ። ከእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ጋ ነገ ለሚኖራቸው የሻምፒዮንስ ሊግ ስድስተኛ ዙር ጨዋታ የእንግሊዙ አጥቂ ሔሪ ኬን ከገቡበት የብርቱ ሽንፈት ሐፍረት እንዲታደጋቸው ። በነገው ዕለት ሌላኛው የጀርመን ቡድን ዑኒዮን ቤርሊንም ሪያል ማድሪድን በሜዳው ያስተናግዳል ። በአንጻሩ ዑኒዮን ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ1 ድል አድርጓል ። ሌን ከሴቪያ፣ ናፖሊ ከብራጋ፤ ኢንተር ሚላን ከሪያል ሶሴዳድ፣ ኤርቢ ዛልስቡርግ ከቤኔፊካ፣ ኤፍሲኬ ከጋላታሳራይ ነገ ይጋጠማሉ ። ውድድሮቹ ረቡዕም ይቀጥላሉ ።
የኅዳር 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከትናንት በስትያ በአስቶን ቪላ የ1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ነገ ፒኤስቪ አይንድሆቨንን ይገጥማል ። ሉቶን ታውንን ትናንት እንደምንም 2 ለ1 ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ ረቡዕ ዕለት በሻምፒዮንስ ሊጉ ሮተር ሽቴርንን ይገጥማል ። ግብ አዳኙ ኧርሊንግ ኦላንድ፣ ጄሬሚ ዶኩ እና ኬቪን ደ ብሩይነ በጉዳት ከጨዋታ ውጪ የሆኑ የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች ናቸው ።
በሻምፒዮንስ ሊግ ሌላ ግጥሚያዎች፦ ኒውካስል ከሚላን፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋ ይፋለማሉ ። ኒውካስል ትናንት በቶትንሀም የ4 ለ1 ብርቱ ሽንፈት አስተናግዷል ። ዶርትሙንድ በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት በላይፕትሲሽ የ3 ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በ37 ነጥብ የመሪነቱን ስፍራ የተረከበው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 አሸንፏል ። በሳምንቱ እሁድ ደግሞ በአውሮጳ ሊግ የደረጃ ፍልሚያ ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ