ደቡብ አፍሪቃ እስራኤልን በዘር ማጥፋት መከሰስ እና በናይጄሪያ የተስፋፋው የሀሰት ዲግሪ
ቅዳሜ፣ ጥር 4 2016
አፍሪቃውያንን የከፋፈለው የደቡብ አፍሪቃ የእስራኤል ክስ
ደቡብ አፍሪቃ እስራኤልን በዘር ማጥፋት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መክሰሷ በዚህ ሳምንት ትኩረት ከሳቡ የአፍሪቃ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
ያለፈው ሀሙስ ዘሄግ በሚገኘው የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (ICJ) በእስራኤል ላይ የተመሰረተውን ክስ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች የአፍቃ ሀገራት በቅርበት እየተከታተሉት ነው።
ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ በ/ ICJ /ላይ ያቀረበችው ክስ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በቅርብ ከቀረርቡት ሦስት ክሶች አንዱ ነው።
አንደኛው ክስ ከሩሲያ ወረራ በኋላ በዩክሬን የቀረበ ሲሆን፤ ሞስኮ ወታደራዊ ዘመቻውን የከፈተችውን በተጨባጭ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈፀም ነው።በማለት ክስ መስርታለች።
ሌላኛው የዘር ማጥፋት ክስ ፣ በጎርጎሪያኑ ህዳር 2019 ዓ/ም ጋምቢያ የሙስሊም ሀገራትን በመወከል ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት /ICJ/ ያቀረበችው ክስ ነው።
ጋምቢያ ምያንማርን በአናሳዎቹ የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች በማለት ከሳለች። ጋምቢያ ህዝቧ በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን፤ በእስራኤል ላይ ክስ የመሰረተችውን ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ 30 የአፍሪካ ሀገራት አባል የሆኑበት የእስልምና ትብብር ድርጅት (OIC) አባልም ነች።
በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም ፣ የሂደቱ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ፍርድ ቤቱ ለጋምቢያ ወስኗል።
በክሱ የተፈረደባት ምያንማርም የተገለጹትን ድርጊቶች ለመከላከል «በእሷ ስልጣን ውስጥ ያሉትን ሁሉንም እርምጃዎች እንድትወስድ» አዟል። ወታደራዊ እና መደበኛ ያልሆኑ ታጣቂዎችን ጨምሮ እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ሀገሪቱ ማረጋገጥ እንዳለባትም ፍርድ ቤቱ አዟል። .
በጋምቢያ ዋና ከተማ ባንጁል ነዋሪ የሆኑት ሞዱ ጃዎ ለDW እንደገለፁት በደቡብ አፍሪቃ ከሳሽነት የተጀመረውን ይህንን ክስ የአፍሪቃ ሀገራት ሊደግፉት ይገባል ይላሉ። «በዚህ እርምጃ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ደቡብ አፍሪካን መደገፍ አለባቸው። እስራኤል ንጹሐን ዜጎችን እየገደለች ነው።»
የደቡብ አፍሪካ እና የጋምቢያ ጉዳዮች ይለያያሉ?
በአምስተርዳም በሚገኘው ኒዮድ /NIOD/ በተሰኘ የጦርነት እና የዘር ማጥፋት ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ቲጅስ ቡውኝት «የደቡብ አፍሪካ ተነሳሽነት ከጋምቢያ በጣም የተለየ ሊሆን ይችላል» ይላሉ።
በደቡብ አፍሪካ ለ46 ዓመታት በህግ የተደነገገው አፓርታይድ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ደቡብ አፍሪካ በ84 ገፅ ማመልከቻዋ ከፍልስጤም ግዛቶች ጋር አንዳንድ መመሳሰሎች እንዳሉት አበክራ መግለጿን ያስረዳሉ። ነገር ግን እስራኤል ከአፓርታይድ ጋር የሚመሳሰሉ ሀሳቦችን አትቀበልም፣ እናም የክሱ ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አከራካሪ ነው ይላሉ።
ጋምቢያዊቷ ጦማሪ ዲጃ ጃዎ ግን የደቡብ አፍሪቃን እርምጃ ታደንቃለች።
«እጅግ በጣም ጥሩ እርምጃ ነው ምክንያቱም ይህ ስለ ሰብአዊ መብቶች ለመሟገት እና በግጭት የተጎዱትን ለመደገፍ ደቡብ አፍሪካ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ነው።»
ጃዎ ጉዳዩን በአፓርታይድ ስርዓት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚኖሩ ዜጎች ከነበረው የመብት ጥሰት ጋር ታያይዘዋለች።
«አንዳንዶቹ ተገድለዋል አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ታስረዋል። ስለዚህ ጋዛውያን ምን እየደረሰባቸው እንደሆነ ያውቃሉ።»
ብዙ የደቡብ አፍሪቃ አይሁዶች ግን ቅር ተሰኝተዋል
በደቡብ አፍሪቃ የአይሁድ ተወካዮች ምክር ቤት ሀላፊ (SAJBD)ካረን ሚልነር ግን ይህንን አይቀበሉትም።ሚልነር እስራኤልን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዱ የደቡብ አፍሪካን መንግስትን ይተቻሉ።
«እስካሁን በደቡብ አፍሪቃ ምንም ሲደረግ አላየንም።ከሩሲያ እና ዩክሬን ግጭት ጋር በተያያዘ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በኮንጎ እና በሱዳን ጨምሮ በመላው አፍሪካ እየተከሰቱ ካሉት አሰቃቂ ግጭቶችም ምንም ሲደረግ አላየንም።»
የደቡብ አፍሪካ ክስ የመጣው እስራኤል በጋዛ ጥቃትን ከጀመረች በኋላ ነው። ጥቃቱን የጀመረችው በአውሮፓ ህብረት ፣ በአሜሪካ ፣ በጀርመን እና በሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃማስ በደቡባዊ እስራኤል ከጥቅምት 7 ቀን 2022 ዓ።ም ጀምሮ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶችን ከፈጸመ ዓ/ም በኋላ ነው። ሀማስ በወቅቱ 1,200 ሰዎችን ገድሎ ከ200 በላይ ማገቱን የእስራኤል መንግስት ገልጿል።
በተቃራኒው በጋዛ ውስጥ ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በጦርነቱ ተገድለዋል ሲል በጋዛ በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን አስጠንቅቋል።
ያም ሆኖ ደቡብ አፍሪቃ ከክስ ይልቅ የማስታረቅን እና ሰላም የማምጣትን ስራ ልትሰራ ይገባት ነበር ይላሉ።ሚልነር።
«ደቡብ አፍሪካ ወደ ሰላም የሚያመራውን መንገድ መምረጥ ትችል ነበር። ደቡብ አፍሪካ በተለይ ሃማስ ታጋቾቹን እንዲለቅ መጠየቅ እና ጫና ማድረግም ትችል ነበር ። ይልቁንም እጅግ ውድ እና ሰፊ የሆነ የህግ ሂደት ውስጥ ገብተዋል ፣ ይህ እውን ሊሆን የማይችል ነው።በዚህ ጦርነት መጨረሻ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።»
የ1948ቱ የተባበሩት መንግስታት የዘር ማጥፋት ስምምነት
ደቡብ አፍሪካ ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባቀረበችው ክስ የ1948ቱን የተባበሩት መንግስታት የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል እና ቅጣት ስምምነትን ጠቅሳለች።ቦውኝት የህጉን ይዘት እንዲህ ያብራራታል።
«በአለም አቀፍ ህግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማለት የአንድን ብሄር፣ ዘር፣ ጎሳ ወይም የሀይማኖት ቡድን አባላት በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የተለዩ ድርጊቶችን ማድረግ ማለት ነው።»
እስራኤል የዘር ማጥፋት ውንጀላውን በፅኑ ውድቅ አድርጋ በችሎቱ ለመከራከር ቃል ገብታለች። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ እና ሌሎች ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣናት ደቡብ አፍሪካን ፀረ-ሴማዊነት እና የአይሁዶች ጭፍን ጥላቻ የሚለውን ቃል ጠንከር ያለ በመጠቀም የአደባባይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ባለፈው ሐሙስ በችሎቱ መክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ደቡብ አፍሪካዊ ተሟጋች ቴምቤካ ንግኩካይቶቢ «እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ዓላማ አላት» ብለዋል።
DW ስለ «የዘር ማጥፋት» ክስ በደብሊን የትሪኒቲ ኮሌጅ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሚካኤል ቤከር የዘር ማጥፋት ወንጄልን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
«የዘር ማጥፋት ዓላማ ተብሎ የሚጠራውን ነገር ማረጋገጥ በጣም ከባድ ነው።ያ የሚባለው የፍላጎት ደረጃ አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ በፍርድ ቤት ለማሳየት አስቸጋሪ ነው።»ብለዋል።
ቤከር እና ቡውግኔት እስራኤል ፈጸመች ወይም አልፈጸመችም የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማረጋገጥ ከባድ ጥያቄ እንደሆነና መልስ ለማግኘት ብዙ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ይስማማሉ። «በህግ በፍርድ ቤት ማረጋገጥ በጣም ፈታኝ ከሆኑ ወንጀሎች አንዱ ነው» ብለዋል ቡውግኔት።
እየተስፋፋ የመጣው የሀሰት ዲግሪ በናይጄሪያ
በናይጄሪያ እየተስፋፋ የመጣው የሀሰት ዲግሪ በዚህ ሳምንት ሌላው ትኩረት የሳበ የአፍሪቃ ጉዳይ ነው።
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኒዩ አስተዳደር ባለፉት 15 አመታት ስራ የጀመሩ 107 የሀገር ውስጥ የግል ዩኒቨርስቲዎች ላይ ምርመራ ሊጀምር መሆኑን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል አስታወቋል።
የናይጄሪያ መንግስት ከዓመታት በፊት በሀገሪቱ እንዲሰሩ እውቅና የተሰጣቸውን ከዩኤስኤ አሜሪካ እና ከብሪታንያ የመጡትን ጨምሮ 18 የውጪ ዩኒቨርስቲዎችንም አግዷል። እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የውሸት ዲግሪዎችን ሲሰጡ ዓመታትን ያሳለፉ ናቸው።
ርምጃው በምርመራ ዘገባ ቅሌቱ መጋለጡን ተከትሎ ሲሆን፤ የናይጄሪያን የትምህርት ተቋማት ያናወጠውን የውሸት ዲግሪ መስፋፋት ለመታገል ያለመ ነው።
በስውር የምርመራ ዘገባ የሚሰራው ናይጄሪያዊው ጋዜጠኛ ኡመር አዉዱ በ6 ሳምንታት ውስጥ ምንም ሳይማር ከአንድ ዩንቨርሲቲ ዲግሪ አግኝቷል። ይህን ቅሌት በማጋለጡ ፤አሁን ከሀሰተኛ ሰርተፍኬት ባለቤቶች የማስፈራሪያ መልዕክት እየደረሰው ነው።
ናይጄሪያ ውስጥ ፤ የዩኒቨርሲቲ ትምህርትን ክብር ለመመለስ የተማሪዎች እና የትምህርት ባለሙያዎች ማህበራት እየተንቀሳቀሱ ነው.።ያም ሆኖ በሀገሪቱ የውሸት የዲግሪ ሰርተፍኬት ማግኘት በጣም እየተስፋፋ መጥቷል።በዚህ ቅሌት ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ ጉዳዩን አባብሶታል።የውሸት ዲግሪውን ሴራ ያጋለጠው ናይጄሪያዊው ጋዜጠኛ ኡመር አውዱ ችግሩ የደረሰበትን ደረጃ ያስረዳል።
«ስለዚህ ይህ ችግር በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ አሁን ብዙ ወጣት ናይጄሪያውያን ተስፋ ቆርጠው ሰርተፍኬት እየፈለጉ እና በትምህርት ዘርፉ ላይ ከባድ ችግር እየፈጠሩ ማየት ትችላላችሁ። ስለዚህ በሁለቱ ሀገሮች ውስጥ በሚከናውኑት በእነዚህ ተግባራት የመንግስትን እና ናይጄሪያውያንን ትኩረት መሳብ አለብን ብለን አሰብን።»
ከሀገራቸው በተጨማሪ ብዙ ናይጄሪያውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ቤኒን እና ቶጎ በመሄድ የአራት አመት ዲግሪውን በሳምንታት ውስጥ ወስደዋል። የምስክር ወረቀቶቹ እንደማንኛውም ሸቀጥ ቤት ውስጥ ይሸጣሉ። ናይጄሪያዊው የዩኒቨርስቲ መምህር ኢብራሂም ሻታምባያ እንዳሉት ይህ የሀገሪቱን የትምህርት ስርዓት እና ምርታማነት ያዳክማል።
«ባለፉት ዓመታት የተከሰተው ነገር፣ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ናይጄሪያን እንዴት እየተጠቀሙበት እንደሆነ በግልጽ ያሳያል።ዩኒቨርስቲዎች በትክክክል ያልተማሩ እና የሙያ ብቃት የሌላቸው ተመራቂዎችን በማፍራት አስተዋፅዖ አድርገዋል።»
ኢብራሂም አያይዘውም ከእነዚህ ተቋማት በአቋራጭ የውሸት ዲግሪ የገዙ ተመራቂዎች ወደ ስራ ሲገቡ የሚፈለገውን ተግባር ለመፈፀም ብቃትና ችሎታ ስሌለቸው ችግር እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
የናይጄሪያ መንግስት አንዳንድ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ይህንን ችግር ለመቆጣጠር ጊዜው አሁን እንደሆነ አምኖበታል። ዑመርም በሀገሪቱ ይህ መሰሉ ቅሌት እንዲከናወን መፈቀድ የለበትም ይላሉ።
«እነዚህ ነገሮች እንዲከናወኑ መፍቀድ ለኛ ትክክል አይሆንም፣ አንዳንድ ሰዎች አእምሮአቸውን አስጨንቀው ጠንክረው እየሰሩ፣ ጥሩ የትምህርት ውጤት ለማግኘት እንቅልፍ አልቫ ምሽቶችን ያሳልፋሉ። አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው በምቾት ተቀምጠው በማዘዝ ያልተገባ የምስክር ወረቀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይረከባሉ።ይህ እንደ ሀገር ስለእኛ ጥሩ ነገር አይነግርም።»
ከናይጄሪያ በተጨማሪ ቶጎ እና ቤኒንም በሀሰተኛ ዲግሪ ንግድ ይታወቃሉ።የናይጄሪያ ባለስልጣናት ከእነዚያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ የምስክር ወረቀቶችን እያገዱ ነው። የኡጋንዳ፣ የኬንያ እና የጋና ዩኒቨርሲቲዎችም በጥቁር መዝገብ ውስጥ ይገኛሉ።
ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ