1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን አልበሽርን ለአይ.ሲሲ. ልትሰጥ ነው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 8 2013

በሽር በዳርፉር ተፈጽሟል በተባለ የዘር ማጥፋት ወንጀል በጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ሲፈለጉ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል።መቀመጫውን ዘ ሄግ ያደረገው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክሱን የሚያጠናክር ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲችል ሱዳን ውስጥ ቢሮ የመክፈት እቅድ አለው ።የሱዳን ባለሥልጣናትም እቅድን ተቀብለውታል።

https://p.dw.com/p/3yyiu
Sudan Khartum | Omar Al-Baschir vor Gericht
ምስል AP/dpa/picture alliance

ሱዳን አልበሽርን ለአይ.ሲሲ. ልትሰጥ ነው


ሱዳንን ለ30 ዓመታት የገዙት የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦመር አልበሽር ለዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በእንግሊዘኛው ምህጻር ICC   ተላልፈው የሚሰጡበት ሂደት በዚህ ሳምንት ተጀምሯል።በሳምንቱ አጋማሽ የሃገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፣በሱዳን ምዕራባዊ ግዛት ዳርፉር፣ከጎርጎሮሳዊው 2003 ዓም አንስቶ በተካሄደው የርስ በርስ ግጭት ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀሎች የሄጉ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ የቆረጠባቸው አል በሽር ተላልፈው እንዲሰጡ መስማማቱን አስታውቋል። የሱዳን ካቢኔ ውሳኔ በተሰማ በማግስቱ ሐሙስ፣ ሱዳን ከICC ጋር የትብብር ውል ፈረመች።ውሉን የፈረሙት የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ካሪም ካንና ጉዳዩ  የሚመለከተው የፍትህ ሚኒስትር መሆናቸውን  ካን ከትናንት በስተያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
«የዘገየሁበት ምክንያት ከሱዳን መንግሥት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስፈራረም መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።የተፈረመውም በእኔ በአቃቤ ሕጉና በፍትህ ሚኒስትሩ ነው።»
በሳምንቱ መጀመሪያ ካርቱም የገቡት ካን የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል አብደል ፋታህ ቡርሃንን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላህ ሃምዶክን  እንዲሁም የሃገሪቱን የፍትህ ባለሥልጣናትና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም አነጋግረዋል ። ስምምነቱም የእስር ማዘዣ ከተቆረጠባቸው ሰዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ትብብር ለመመስረት የሚያስችል መሆኑን ካን ተናግረዋል።የICC ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንዳሉት ውሉ የቀድሞ አምባገነን በሽር፣በዳርፉር ግጭት ተፈጽመዋል በተባሉ ወንጀሎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የማድረግ አንድ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።መቀመጫውን ዘ ሄግ ያደረገው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክሱን የሚያጠናክር ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እንዲችል ሱዳን ውስጥ ቢሮ የመክፈት እቅድ እንዳለው ካን ካርቱም ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። 
«ከውሳኔዬና ከፍላጎቴ ጎን ለጎን ኢንሻላህ መቀመጫውን እዚህ አድርጎ ሙሉ ጊዜ የሚሰራ አንድ ቡድን ንዲኖረን ለማድረግ ማቀዴን ህዳር ላይ ተመልሼ እንደምመጣ እና ዳርፉርንም እንደምጎበኝ ጠቁሜያለሁ።» 
የሱዳን ባለሥልጣናትም የICC ጠበቆች ቡድን በርቀት ከመስራት ካርቱም ውስጥ በመሆን የሙሉ ጊዜ ሥራ እንዲያካሂዱ የቀረበውን እቅድ በደስታ መቀበላቸውን ነው  ካን የተናገሩት።ይሁንና በዚህ ሳምንት ካርቱም ውስጥ ከመንግሥት ጋር የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙት የሄጉ ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ካን እንደሚሉት በሽር ተላልፈው ከመሰጠታቸው በፊት ሌሎች ቁልፍ የሚባሉ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል።አል በሽርን አሳልፎ የመስጠቱ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን፣የወታደሩንና የሲቪሉን ተወካዮች ባካተተው በገዥው የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት መጽደቅ ይኖርበታል። ካን እንደሚሉት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤትና የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ የጋራ ምክር ቤቱ በመጪው ሳምንት በጉዳዩ ላይ ይወያያል።
«ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት አካሂጃለሁ።ሃላፊነታቸውን ያውቃሉ፤ይፋ የሚሆኑ ውሳኔዎች ሲተላለፉ መግለጫ ይሰጣል።የጋራ ምክር ቤቱ  በሚቀጥለው ሳምንት ስብሰባ እንደሚያደርግ ተነግሮኛል።ስብሰባው ምን እንደሚያመጣ እናያለን።በስተመጨረሻ ለመተባበርም ሆነ እንዴት እንደሚተባበሩ መወሰኑ የኔ ሳይሆን የሱዳን ነው።»
ከሱዳን ባለሥልጣናት ጋር በሽርን መቼ እንደሚያስረክቧቸው አለመነጋገራቸውን ነው ካን የገለጹት ።የሱዳን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሱዳን የዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ምስረታ ውል የሮሙን ህገ ደንብ መቀላቀል የሚያስችላትን ረቂቅ ሕግ ማጽደቁን በደስታ ተቀብሎታል።ውሳኔው በአይሲሲ የእስር ማዘዣ ለተቆረጠባቸው ለበሽርና የቀድሞ ረዳቶቻቸውን የፍርድ ሂደት አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ ነው።   ረቂቅ ሕጉን ማጽደቅን በሚመለከት በሽግግሩ ወቅት እንደ ፓርላማ ሆነው የሚያገለግሉት  ገዥው ሉዓላዊ ምክር ቤት እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጋራ በመጪው ሳምንት በሚያካሂዱት ስብሰባ ይነጋራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሱዳንና የICC ስምምነት በሽር በሄጉ ፍርድ ቤት የመዳኘታቸውን እድል ከፍ ያደርገዋል። ይህ  ግን በሱዳን አወጣጋቢ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው።
የ77 ዓመቱ በሽር በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በዳርፉር ተፈጽሟል በተባለ የዘር ማጥፋት ወንጀል በጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ሲፈለጉ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል።ሁለት የቀድሞ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ከርሳቸው ጋር በጦር ወንጀሎች ተከሰዋል። በሽር በ2009 ዓም በዳርፉር  በጦርና በሰብዓዊነት ላይ በተፈሙ ወንጀሎች ነበር የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው።በኋላ ግን  የዘር ማጥፋት ወንጀልም ታከለባቸው።በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2019 ታስረው  ታህሳስ 2019 ዓም በሙስና የተከሰሱት በሽር ከሐምሌ 2020 አንስቶ ደግሞ በጎርጎሮሳዊው 1989 በአክራሪ ሙስሊም ተዋጊዎች ድጋፍ  ሥልጣን በያዙበት መፈንቅለ መንግሥት  በፍርድ ሂደት ላይ ናቸው። ጥፋተኛ ከተባሉም የሞት ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል ተብሏል።  

በተከታታይ ከተካሄደ ህዝባዊ አመጽ በኋላ በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2019 ከስልጣናቸው የወረዱት አልበሽር አሁን ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ኮቦር እሥር ቤት ነው ያሉት።ሁለቱ የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የቀድሞ የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጦር ወንጀሎች የተከሰሱት በዳርፉሩ ግጭት ወቅት የሀገር ውስጥና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አብደልራሂም ሞሀመድ ሁሴን እንዲሁም የቀድሞው የደቡብ ኮርዶፋን ሀገረ ገዥ የደኅነት ሃላፊ በኋላም የበሽር ፓርቲ መሪ የነበሩት አህመድ ሃሩንም አል በሽር ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ በእስራ ላይ ናቸው።ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከዚህ ሌላ ያለበት የማይታወቀውን የአማጽያኑን መሪ አብዱላ ባንዳንና የጃንጃዊድ መሪ አሊ ኩሻይብን በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ከሷል።ሱዳን ከነሐሴ 2019 ዓም አንስቶ በጊዜያዊ የሲቪልና የጦር ኃይል አስተዳድር ነው የምትመራው።ጊዜያዊ አስተዳደሩም በበሽር ዘመን ለተፈጸሙ ወንጀሎች ሰለባዎች ፍትህ ለማምጣት ቃል ገብቷል።የሱዳን ካቢኔ በሽርን አሳልፎ ለመስጠት መወሰኑን  ዩናይትድ ስቴትስን በደስታ ተቀብላለች፤ውሳኔውን በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ትልቅ እርምጃ ስትልም አወድሳለች ።የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሱዳን ለፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ከዓለም አቀፉ ፍርድቤት ጋር መተባበሯን እንድትቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። 
«የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ካቢኔው ባሳለፈው ውሳኔ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በዳርፉር በተፈጸሙ ወንጀሎች የሚፈለጉትን  የቀድሞውን ፕሬዝዳንት በሽርንና ሌሎች የቀድሞ ባለሥልጣናትን አሳልፎ ለመስጠት ዳግም ማረጋገጡን በደስታ ተቀብለነዋል።ውሳኔውን ለማስፈጸም ካቢኔውና ሉዓላዊው ምክር ቤት በጋራ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየተጠባበቅን ነው።ሱዳን የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸውን አሳልፋ በመስጠትና የተጠየቁትን ማስረጃዎችም በማቅረብ ከICC ጋር መተባበሯን እንድትቀጥል እንጠይቃለን።ይህን ማድረግ ሱዳን ለአስርት ዓመታት ያጠፉ ፣አለመቀጣታቸውን ለመዋጋት ዋነኛ እርምጃ ነው የሚሆነው።»
በሽር በስልጣን ላይ እያሉ በ2009 ዓም የእስር ማዘዣ ከተቆረጠባቸው በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ በዳርፉር ተፈጽሟል ባለችውየዘር ማጥፋት ወንጀል ሰበብ፣ ሃገራት በሽርን እንዳያስተናግዱ ለዓመታት ግፊት ስታደርግ ቆይታለች።
የዳርፉሩ ጦርነት የተጀመረው በጎርጎሮሳዊው 2003 ዓም ነው።ያኔ ስልታዊ አድልዎ ተፈጽሞብናል አረቦች በሚያመዝኑበት የካርቱም መንግሥት ተጨቁነናል ሲሉ ያማርሩ የነበሩት አረብ ያልሆኑ አማጽያን ነፍጥ አንግበው ተነሱ ።የካርቱም መንግሥት በአጸፋው የአየር ድደባ እያካሄደ ፣ በአካባቢው ከሚገኙ አርብቶ አደሮች በተመለመሉት በጃንጃዊድ ሚሊሽያዎች በማስወረር  አመጹን በኃይል መጨፍለቅ ጀመረ።የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የበሽርን መንግሥት እና የቀድሞ ረዳቶቻቸውን በመሬት ፖሊሲ በአስገድዶ መድፈር፣ በግድያ፣በዝርፊያ እና መንደሮችን በማቃጠል ለረዥም ጊዜ ሲከሱ ቆይተዋል።ሚሊሽያዎቹም ጅምላ ግድያ በማካሄድ እና አስገድዶ በመድፈር ይወነጀላሉ።በዚህ ግጭት የተመድ በምዕራብ ሱዳንዋ ግዛት በዳርፉር ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከዛሬ 18 ዓመት አንስቶ 300 ሺህ ሰዎች መሞታቸውንና ከ2.5ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ይናገራል።በሽር አገዛዝ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶባቸዋል ከሚባሉት የዳርፉር አማጽያን ዋና ዋናዎቹ ከአዲሱ የሱዳን መንግሥት ጋር በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል።ከመሪዎቻቸው መካከልም አንዳንዶቹ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ይዘዋል,። ከጎርጎሮሳዊው 2007 አንስቶ እስከ ዘንድሮ ታህሳስ ድረስ  የተመድና የአፍሪቃ ኅብረት  የጋራ ሰላም አስከባሪ ኃይ በምህጻሩ UNAMID በዳርፉ በሰላም ማስከበር ተሰማርቶ ቆይቷል። ከዚያ ቀደም ሲልም ከ2004 ዓም አንስቶ የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ዳርፉ ነበር። ይሁንና በግዛቲቱ አሁንም ግጭት አልቆመም።    
ኂሩት መለሰ 

Sudan | El Geneina | Haupstadt West-Darfur
ምስል AFP
Sudan | UNAMID Mission
ምስል AFP
Sudan Ministerpräsident Abdullah Hamduk
ምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance
Karim Kahn wird Chefanklaeger des Weltstrafgerichts
ምስል Sabah Arar/AFP/Getty Images
Libyen Sirte | Früherer sudanesischer Präsident | Omar Hassan al-Baschir
ምስል Photoshot/picture alliance

ማንተጋፍቶት ስለሺ