1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ እየተባለም በአማራ ክልል የቀጠለው ውጊያ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 11 2016

ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት የተሰጠውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ከአምስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች ወደ መንግሥት መግባታቸውን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ። በሌላ በኩል በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማና ምዕራብ ጎጃም ዞን ፈረስ ቤት ከተማ ውጊያዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4aRzi
በአማራ ክልል የጎንደር ከተማ
በአማራ ክልል የጎንደር ከተማ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ከአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጣቢያ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመመካከር የሁለት ሳምንታት የሳለም ጥሪ ማድረጉን የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፋንታው ተናግረዋል።

ቢሮ ኃላፊው ትናንት ለመገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ «የሰላም ጥሪውን ተከትሎ ከአምስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች በሰላም ገብተዋል።» ብለዋል። «በአጠቃላይ በሁሉም ቀጣናዎች በአራቱም እዝ ጣቢያ ቀጣናዎች ወደ አምስት ሺህ 216 የሚሆን ታጣቂ ኃይል ወደ ሰላም ሁኔታ የተመለሰበትና ሰላማዊ ሕይወቱን ለመምራት ፈቃደኝነቱን አሳይቶ አቀባበል የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው፣ ... አሁን ወደ ማዕከላት የገቡበት ሁኔታ ነው ያለው።» ብለዋል።

በክልሉ የቀጠለው ውጊያ

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ውጊያውመቀጠሉን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ትናንት በነበረው ውጊያ የመከላከያ ሠራዊት ድሮንን ጨምሮ ከባድ መሳሪያዎችን ተጠቅሟል ነው ያሉት። ትናንት ከሰዓት በኋላ ከ11 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ጠጠር ድንጋይ፣ ድኩል ቃና እና ዝቋላ በሚባለው አካባቢ ውጊያ እንደነበርና ሰዎች መቁሰላቸውንና መሞታቸውን ተናግረዋል። ሌላ የዚሁ ከተማ ነዋሪም በተለይ ጠጠር ድንጋይ በሚባለው የከተማው ክፍል ከባድ ውጊያ እጅግ ከበድ ያለ እንደነበርና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ቀኑ 7 ሰዓት ድረስም እንደቀጠለ ገልጠዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ አማራ ክልል
በአማራ ክልል ታጣቂዎች ለመንግሥት እጃቸውን መስጠታቸው ቢነገርም በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።ፎቶ ከማኅደር፤ አማራ ክልልምስል AP/picture alliance

 በተመሳሳይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል  ከተማና አካባቢው ውጊያ ትናንት ሲካሄድ መዋሉንና ዛሬም መቀጠሉን የአማኑኤል ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። በተለይም ትናንት በተለምዶ «የነጪ» እና «የውሻ ጥረስ» በሚባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ እንደነበር አመልክተዋል። «ትናንትና 12 ሰዓት ጠዋት የነጪ በሚባለው አካባቢ ውጊያ ተጀመረ፣ እስከ ቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ ውጊያው ቀጥሏል። ጥቂት ውጊያው በረድ እንዳለ የፋኖ ታጣቂዎች ከተማ ውስጥ ገቡ፣ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሯት። በተለምዶ ውሻ ጥርስ በሚባለው አካባቢ መከላከያ ከባድ መሳሪያ መተኮስ ጀምሮ ነበር፣ የጉዳት መጠኑን አሁን ማወቅ አይቻልም፣ ተኩስ አሁንም የነጪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አለ፣ በውሻ ጥርስ በኩል ያለው በርዷል። (ቀን 7 ሰዓት)» 

ሌላ የአማኑኤል ከተማ አስተያየት ሰጪም በተመሳሳይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ ውጊያ መቀጠሉ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል። ጉዳዩን አስመልክቶ ከመንግሥትና ከፋኖ በኩል አስተያየቶችን ለማካተት ያደረግሁት ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ከሐምሌ 2015 ዓ ም መጨረሻ ጀምሮ  በአማራ ክልል በተፈጠረው ጦርነት መንገዶች አንደ ልብ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በተሟላ መልኩ እየተከናወኑ አይደለም።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ