1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አምነስቲ የታሰሩ የኢሰመጉ አባላት እንዲለቀቁ ተጠየቀ

ረቡዕ፣ ጥር 3 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በሥራ ላይ ሳሉ በፀጥታ ኃይሎች የታሰሩ አራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አባላትን በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ሲል ዓለም አቀፉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ። መንግሥት የሰብዓዊ ጉዳይ ባለሞያዎቹን ያሰረዉ የሚሰራዉ የመብት ጥሰት አደባባይ እንዳይወጣ ነዉም ሲል ድርጅቱ ከስዋል።

https://p.dw.com/p/4M261
Logo amnesty international

«የኢሰመጉ አባላት ይህ ነዉ የሚባል አንድም ወንጀል አልፈፀሙም»

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በሥራ ላይ ሳሉ በፀጥታ ኃይሎች  የታሰሩ አራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አባላትን በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ሲል  ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «አምነስቲ ኢንተርናሽናል» አሳሰበ። ድርጅቱ ትናንት አመሻሽ ላይ ይፋ ባደረገዉ መግለጫ አራቱ የኢሰመጉ አባላት ታህሳስ 27 እለት በቁጥጥር ስር ዉለዉ ለእስር የተዳረጉት በአዲስ አበባ ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉን ደሃ ነዋሪዎች ጉዳይ ለማጣራት እና መረጃ በመሰብሰብ ላይ ሳሉ ነዉ።  

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «አምነስቲ ኢንተርናሽናል» ይፋ ባደረገዉ መግለጫ መሰረት አራቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) አባላት ባለፈዉ ታህሳስ 27 በፖሊስ ሲያዙ ይህ ነዉ የሚባል አንድም ወንጀል አልፈፀሙም። የሰብዓዊ መብት ጉዳይን የሚከታተለዉ የኢሰመጉ ሰራተኞች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸዉ ያሉ የደሃ ነዋሪዎችን ጉዳይ በመከታተል ላይ ሳሉ ነበር ሲል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል። የኢሰመጉ አባላት የታሰሩት በዓለም ገና የተፈናቀሉ ሰዎችን ጉዳይ በመከታተል ላይ ሳሉ የገና በዓል ሊከበር ሁለት ቀናት ሲቀረዉ  እንደሆነ  በአምነስቲ  ኢንርናሽናል የህግና የፖሊሲ ጉዳይ አማካሪ አቶ ፍሰሃ ተክሌ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።   

አምነስቲ በዓለም ገና አካባቢ በአዲስ አበባ ዙርያ በመንግሥት ትዕዛዝ እየፈረሰ ያለዉን የነዋሪዎች በኖርያ ቤት ጉዳይስ ተመልክቷል? የሰማዉስ ነገርም አለ? ለሚለዉ ጥያቄ አቶ ፍሰሃ ተክሌ በርግጥ ድርጅቱ የቤት መፍረስ እና የሰዎች መፈናቀል ጉዳይን ሰምተናል ይሁንና ይህን ለማጣራት የሄዱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሰራተኞች መታሰራቸዉ አግባብ አይደለም ሲሉ አቶ ፍሰሃ ተክሌ ተናግረዋል። አቶ ዳንኤል ተስፋዬ፤ ብዙአየሁ ወንድሙ፤ በረከት ዳንኤል እና ናሆም ሁሴይን የተባሉ የኢሰመጉ አባላት በዓለም ገና አካባቢ ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉ ደሃ ዜጎችን ጉዳይ ለመከታል ቦታዉ ላይ የተገኙት ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም እንደነበር አምነስቲ ባወጣዉ ዘገባ ጠቅሷል።  

አራቱ፣ የኢሰመጉ አባላት በታሰሩ በነጋታዉ «ያለ ፖሊስ ፈቃድ የሰብአዊ መብት ክትትል በማድረግ» በሚል ታህሳስ 28 ቀን ክስ እንደተመሰረተባቸዉም ታዉቋል። ይሁንና ይህ በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት ወንጀል አለመሆኑን አምነስቲ ባወጣዉ መግለጫ ላይ ጠቅሷል።  የኢሰመጉ አባላት የነበሩበት መኪናን በቁጥጥር ስር ያዋለዉ ፖሊስ በበኩሉ ከድርጅታቸዉ ምንም አይነት የድጋፍ ደብዳቤ ሳይዙ ቤት የፈረሰባቸዉን ሰዎች ሲያነጋግሩ እንደነበር አምነስቲ ዘግቧል። አራቱ የኢሰመጉ አባላት በኦሮምያ ክልል ጌላን ጉዳ ፖሊስ ጣቢያ መያዛቸዉ ተጠቅሷል።  አራቱ ታሳሪዎች ዛሬ ጥር 3 ቀን 2015 ዓም የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንዳለባቸዉ ታዉቋል።

በሌላ በኩል የኢሰመጉ ሠራተኞች በሚደርስባቸዉ በሚደርስባቸዉ ዛቻ እና ማስፈርርያ ምክንያት በጋምቤላ ክልል የኢሰመጉ ጽ/ቤት መዘጋቱን መረጃ እንደደረሰዉ አምነሲቲ ገልጿል። በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «አምነስቲ ኢንተርናሽናል» የህግና ፖሊሲ አማካሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ ለሰጡን ቃለ ምልልስ አመሰግናለሁ። አዜብ ታደሰ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «አምነስቲ ኢንተርናሽናል» የህግና ፖሊሲ አማካሪ አቶ ፍስሃ ተክሌን አነጋግራ ተከታዩን ዘገባ አጠናክራለች።

አዜብ ታደሰ  

ነጋሽ መሐመድ