አሳሳቢዉ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 9 2015ሦስተኛ ቀኑን በያዘው በሱዳን ብሔራዊ ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ በተባለው ሕጋዊ ታጣቂ ቡድን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት የፈጠረው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ሲሉ በካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ተናገሩ። ሱዳን ውስጥ የተጀመረው ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት የአገሪቱ የፖለቲካ ሂደት እጅግ በጣም ጥሩ በሚባል ሁኔታ እየቀጠለ ነበር ያለው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት ( ኢጋድ ) ሲቪል መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለው የመጨረሻ ፊርማ ይፈረማል ብሎ ሲጠብቅ ይህ ክስተት መምጣቱ እንዳሳዘነው ገልጿል።
ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ፣ ችግሩ በውይይትና በንግግር እንዲፈታ ለማድረግም የሦስት አገራት ፕሬዝዳንቶች የተካተቱበት ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ካርቱም ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ስምምነትን ማፍረስ የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ነባር ልማድ ነው ያሉ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ተንታኝ ኢጋድ "አንተም ተው አንተም ተው ፣ ተስማሙ፣ ስልጣን ተጋሩ" ከማለት ያለፈ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል በመግለጽ ጦርነቱ በአካባቢው አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ እንደ አመጣጡ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሱዳን ውስጥ በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ በተባለው ታጣቂ የሚሊሽያ ኃይል መካከል የተቀሰቀሰው ሰሞነኛ የለየለት ጦርነት የአፍሪካ ሕብረት ከሕብረቱ አባልነት በወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ ምክንያት ቀድም ሲል ላገዳት ጎረቤት አገር ሱዳን ተጽእኖው ዓለም አቀፍ ውጤት ያለውና የብዙ ተዋናዮችን መራኮትን የሚያባብስ ችግር ወልዷል።
እስካሁን ከ 100 በላይ ሰዎች ተገድለው፣ በርካቶች ቆስለው ክፉኛ የንብረት ውድመት ማስከተሉ የተነገረለት ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን እና ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ጎራ ለይተው እየተፋለሙበት ያለው የከተማ ውስጥ ጦርነት ዋና ከተማ ካርቱምን ጨምሮ ሌሎች ከተሞችንም የጦርነት አውድማ አድርጎ እያበጠ ይገኛል።
አቶ ደርሶ የተባሉ የተባበሩት መንግሥታት በስደተኛነት መዝግቦ የሚያውቃቸው ኢትዮጵያዊ ከሚኖሩበት ካርቱም ከተማ ቃለ መጠይቅ ስናደርግላቸው ከወዲያ ከፍተኛ የጥይት ድምፅ ይሰማ ነበር። በሚኖሩበት ማእከላዊ ካርቱም ኤርትራዊያን ስደተኞች ጭምር በስፋት ይኖራሉ ያሉት እኒሁ የዐይን እማኝ በሱዳን የእለት ምግብ ሱቅ ላይ ከሚሸመት በቀር ለቀናት እና ለወራት የሚሆን ምግብ ቤት ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ የሌለ በመሆኑ ስደተኞችን ጨምሮ ራሳቸው ሱዳናዊያኑም ፈተና ላይ ወድቀዋል ብለዋል።
ሱዳን ውስጥ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ብዙ ወገኖች የግጭት አቁሙ ጥሪ እያደረጉ ነው። ሀገራት በተናጠል ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ድርጅቶችም እንዲሁ ተኩስ እንዲገታ እየወተወቱ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተፋላሚዎቹ ኃይላት ችግራቸውን በሰላም እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የአረብ ሊግ፣ የአፍሪካ ሕብረት ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች አካላት ተመሳሳይ ጥሪ አድርገዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ይህንን ጦርነት ለማስቆም የሕብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበር ወደ ካርቱም እንደሚልክ አስታውቋል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት ( ኢጋድ ) የአባል አገራቱን መሪዎች በአስቸኳይ ሰብስቦ በጉዳዩ ላይ ተወያይቷል። የደቡብ ሰዳን፣ የጅቡቲ እና የኬንያ መሪዎችን ያካተተ አንድ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ካርቱም ለመላክ በዝግጅት ላይ ይገኛል። የኢጋድ ዋና ፀኃፊ ቃል ዐቀባይ ኑር ሞሃመድ ከጅቡቲ ለዶቼ ቬለ በስልክ በሰጡት ማብራሪያ
ኢጋድ ይህንን ችግር ለመፍታት ከአፍሪካ ሕብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በሦስትዮሽ ግንኙነት በቅርበት እየሰራ ይገኛል። ኢጋድ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባቱ ግዴታ መሆኑን ገልጿል። ይህንን የሚያደርገው ግጭት እንዲቀንስ ፣ ተኩስ እንዲቆም ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሆነ አስታውቋል።
የአባል አገራቱ መሪዎች ትናንት ሁሉንም ተፋላሚ ወገኖች ለማነጋገር ተስማምተው ቢለያዩም ዛሬ ሰኞ ጭምር በከባድ መሣሪያ የታገዘው ግጭት መቀጠሉን ከስፍራው ማረጋገጥ ችለናል። ይህ የሱዳን ግጭት ኢትዮጵያ ጨምሮ በሌሎች አገሮች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጫና ቀላል የሚባል እንዳለሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እየገለፁ ነው። በሕዳሴ ግድብ ዘሪያ የሚታየው ልዩነት ፣ በድንበር ረገድ ያለው ውዝግብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ያቋጨችው ችግር አለ።
አምባሳደር ተፈራ ሻውል ሱዳንን አንድም የተፈጥሮ በሌላ በኩል ስምምነት ያለማክበር ነባር ልማድ ለዚህ መሰል ችግር ተጋላጭ እንዳደረጋት ገልፀዋል። ሱዳን ውስጥ አሁን ከተቀሰቀሰው ጦርነት በፊት ሰፋፊ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በየጊዜው ተስተናግደዋል።
"እነዚህ ሦስት ፕሬዝደንቶች በሽምግልና እና ማስታረቅ ረገድ የዳበረ ልምድ ያላቸው እና አንጋፋ መሪዎች ናቸው። በተቻለው ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ካርቱም ይጓዛሉ የሚል እቅድ ተይዟል። ሆኖም ከዚያ በፊት ሁለቱንም ወገኖች ተኩስ ማቆም በሚችሉበት ሁኔታ ያነጋግሯቸዋል። ስለዚህ ኢጋድ በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በሦስትዮሽ የሥራ ግንኙነት በቅርበት እየሰራ ይገኛል። በዚህ ረገድ ትናንት ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ጋር ተኩስ ማቆም በሚችሉበት ሁኔታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ መቅረብ በሚችልበት አማራጭ ዙሪያ እንዲሁም ንፁሃን ዜጎች ጥበቃ ማግኘት እንዲችሉ ሰፊ ግንኙነት ተደርጓል።
ከትናንት በፊት ማለትም ይህ ግጭት ከመፈንዳቱ በፊት የሱዳን የፖለቲካ ሂደት እጅግ በጣም ጥሩ በሚባል ሁኔታ እየቀጠለ ነበር። በአገሪቱ የፖለቲካ ሂደት የሲቪል መንግሥት መመስረቱን የሚያረጋግጠው የመጨረሻ ፊርማ ይፈረማል በሚል ነበር ሁሉም ወገን እየሠራ የነበረው።" በማለት ውጥኑ አለመሳካቱን ገልፀው አሁንም ቢሆን ተፋላሚዎቹ ወደ ሰላማዊ ንግግር ይመለሳሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ