አሳሳቢው የቅርስ ምዝበራና የድረገጽ ላይ ሽያጭ
ዓርብ፣ የካቲት 4 2014በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ሃይማኖታዊ የሆኑ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች ለገበያ መቅረባቸው አሳሳቢ መሆኑ ተገለጠ። ጥንታዊ ቅርሶቹ ከሰሞኑ eBay በተባለ ድረ-ዓለማቀፍ በይነ-መረብ ላይ ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን፤ ቅርሶቹ ያለምንም ጥያቄ የኢትዮጵያ ናቸው ሲል የቱሪዝም ሚኒስቴር ለዶቼ ቬለ ተናገሮዋል። ቅርሶቹ የወጡት ቀድሞ ነው ወይንስ አሁን በጦርነቱ ምክንያት የሚለውን ግን በአሁኑ ወቅት ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሆነ አብራርቶዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ስለሺ ግርማ የዓለም ቅርሶችን የሚጠብቀውና ፓሪስ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) ቅርሶቹ የኢትዮጵያ ስለሆኑ ለሽያጭ እንዳይውሉ እና ወደ አገር ቤት መመለስ እንዲችሉ አዲስ አበባ ከሚገኘው የድርጅቱ ኃላፊ ጋር ዛሬ ጥዋት መነጋገራቸውን ገልፀዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት በጦርነት ወቅት በርካታ ቅርሶች ለውድመት፣ ለስርቆት፣ ለዝርፊያ እንደሚጋለጡ አስታውሰው ቅርሶች በጎብኝዎችና ሌሎች እንዳይወጡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ጠንካራ ቁጥጥር ይደረጋል። ይሁንና በእንዲህ ያለው የጦርነት ጊዜ ሰዎች በድንበር በኩል መውጣታቸው ስለማይቀር ይዘዋቸው የሚወጡ ቅርሶች እንደሚኖሩም ለዶይቸ ቬለ (DW) ገልጸዋል። አጠቃላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ውድመት የደረሰባቸው ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ምን ያህል እንደሆኑ ጥናት ሲደረግ እንደቆየ እና የጥናቱ ውጤት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
በተለይ eBay እና አማዞን በተባሉ የበይነ-መረብ ግብይት አከናዋኝ ድረ ገጾች ላይ ከተለያየ አገር የተዘረፉ ልዩ ልዩ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ማሳያ ቅርሶች ለግብይት ይቀርባሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አገር ወዳድ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የቅርስ ተቆርቋሪ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቅርሶችን እየገዙ ለተዘረፉባቸው አገሮች ስለሚያስረክቡ በዚሁ መንገድ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በተነሳው ጦርነት ምክንያት ልዩ ልዩ ቅርሶች የሚገኙባቸው ሙዚየሞች፣ አብያተክርስትያናት እና ገዳማት እንዲሁም መስጊዶች ለውድመት፣ ለዘረፋ እና ስርቆት መዳረጋቸው ይታወቃል።
ሰሞኑን eBay በተባለው ድረ ገጽ ለሽያጭ ከቀረቡት ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ቅርሶች መካከል በግዕዝ ቋንቋ ቀይ እና ጥቁር ቀለም በሚተፋ መቃ - ብዕር የተጻፉ አነስተኛ መጠን ያላቸው የብራና መጽሐፍት፣ ልዩ ልዩ ይዘትና ቅርጽ ያላቸው መስቀሎች ይገኙበታል። በድረ ገጽ ግብይቱ ላይ ለቅርሶቹ ሽያጭ የተቀመጠው ዋጋ አነስተኛ መሆን ብሎም የቅርሶቹን ውድነት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን በስፋት ሽፋን መስጠታቸው ብዙዎች ከጀርባ ምን አለ? እንዲሉ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በዚሁ በ2014 ዓ. ም ከእንግሊዝ ፣ ከስዊዘርላንድ እና ከሆላንድ አክሊል፣ የብራና መጽሐፍት፣ መስቀሎችንና ጎራዴን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችንም አስምልሷል። ይሁንና አሁንም ከመቅደላው ጦርነት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የወጡ ጽላቶች እና ሌሎች ውድ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶች የአገር ከአገርን ብርቱ የዲፕሎሚሲ ሥራዎችን የሚጠይቁ በመሆናቸው ሳይመለሱ በየአገራቱ ሙዚየሞች ውስጥ እንደሚገኙ መንግሥት ደጋግሞ ገልጿል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ