በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ድንጋጌው ተራዘመ
ዓርብ፣ ጥር 24 2016
በአማራ ክልል ለስድስት ወራት ተደንግጎ ሥራ ላይ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዘመ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ልዩ ስብሰባ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለመንፈቅ ያህል ጊዜ በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲራዘም በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት፣ ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነትን በአግባቡ ማጤን ይኖርባቸዋል ሲሉ አዋጁ ከመራዘሙ አስቀድመው ዛሬ ጠዋት ጽፈው ነበር። ከአዲስ አበባ ሰሎሞን ሙጬ ዘገባ አለው።
በአማራ ክልል በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የዘለቀውን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ ክልሉ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ በቀድሞው የክልሉ ርዕሠ መስተዳር ጥያቄ ቀርቦ በፌዴራል መንግሥቱ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ለ ስድስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲፀና ዛሬ ምክር ቤት ወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ «በክልሉ የተደቀነውን አደጋ ለመቆጣጠት እና በክልሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመታደግ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል» ያለው መንግሥት ያም ሆኖ ግን ቀሪ ያላቸው ሥታዎችን ለማጠናቀቅ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ሥጋት አዝማሚያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለማራዘም ውሳኔ ላይ መደረሱን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞቲዮስ አብራርተዋል።
ለአዋጁ መራዘም የቀረቡ አወንታዊ የድጋፍ ድምጾች
«አዋጁ በመታወጁ የአማራ ክልል ሕዝብ እና በየደረጃው ያለ አመራር ከባሰ እልቂት የዳነበት እና ክልሉን ከመበተን የታደገ ነው» የሚሉ የድጋፍ አስተያየቶች በዛሬው ጉባኤ ላይ መነሳቱ ታውቋል። ቀላል ቁጥር ያልሆነ ወረዳ እና ቀበሌ ችግር ውስጥ መሆኑ፣ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ገደብ መኖሩ እና ገበሬው ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ያልቻለበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩ እንዲሁም በሽምቅ ውጊያ የታች መዋቅር አመራሮች እና ሰላማዊ ዜጎች እየሞቱ መሆኑ ተጠቅሶ የድንጋጌው መራዘም ላይ ከምክር ቤቱ አባላት አወንታዊ ድጋፍ ተሰጥቷል። አዋጁን መነሻ አድርጎ ዜጎችን ያለአግባብ የማሰር ፣ የማንገላታት ችግር መኖሩን ያስታወሱ የምክር ቤት አባላት እርምት ጠይቀዋል፣ አዋጁ አላማውን እንዳይስትም ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።
የተቃውሞ ድምጾችም ተደምጠዋል
በሌላ በኩል መነጋገር፣ መደራደር፣ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስፈልገንም ብለን ነበር። ሆኖም በወቅቱ ሰሚ አልነበረንም ያሉ የምክር ቤት አባል በአዋጁ ምክንያት «ንፁሃን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፣ የምክር ቤት አባላት ላልተገባ እሥር እና እንግልት ተዳርገዋል» በማለት የድንጋጌውን መራዘም ተቃውመዋል። «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም በጎ ተጽዕኖ አላመጣም። እውነተኛ ድርድር እና ውይይት እየተደረገ አይደለም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አጠቃላይ የሀገሪቱን ልማት ወደኋላ ነው የመለሰው» የሚሉ የተቃውሞ ሀሳቦች ተስተናግደዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ የበላይ ኃላፊ ዶክተር ዳንኤል በቀለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚራዘም ከሆነ ለረዥም ጊዜያት በእስር ላይ በሚቆዩ ሰዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽእኖ አሳሳቢ መሆኑን ዛሬ ጥዋት በ X የማኅበራዊ መገናኛ ጽፈው ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት፣ ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነት በአግባቡ መጤን ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበው ነበር። ኮሚሽኑ ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ የአዋጁን መደንገግ ተከትሎ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን፣ በማሳያነትም ግድያ እና አስገድፎ መድፈር፣ በከባድ መሣሪያ አልፎ አልፎ በድሮን ድብደባ እየተፈፀመ ነው ሲል አስታውቆ ነበር። ምንም እንኳን መንግሥት የኮሚሽኑን ዘገባ ቢያጣጥለውም።
የመርማሪ ቦርዱ ሥልጣን ስለመራዘሙ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ የሥራ ዘመን ከአዋጁ ጋር ተራዝሟል። መርማሪ ቦርዱ ባለፉት ስድስት ወራት 7,196 ተጠርጣሪዎች ተይዘው እንደነበር እና «ከ 5000 በላይ» ያህሉ በተሃድሶ እና ሥልጠና እንዲለቀቁ ተደርጓልም ብሏል። የዛሬው የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይም ይሁን ትናንት ፍትሕ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የተቋሙ የስድስት ወራት የሥራ ዘገባው ላይ የግል እና የውጭ ብዙኃን መገናኛዎች ገብተው እንዳይዘግቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ