1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንድ ለአንድ፦ የኢትዮጵያን የተዘረፉ ቅርሶች የማስመለስ ፈተና ከዶክተር አሉላ ፓንክረስት ጋር

Eshete Bekele
ዓርብ፣ ኅዳር 27 2017

ኢትዮጵያ በመቅደላ ጦርነት እና በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶችን ለማስመለስ ግፊት እያደረገች ነው። ከዚህ ቀደም የአክሱም ሐውልት፣ የአጼ ቴውድሮስ ጸጉር፣ ታቦቶች እና ጸሀይ አውሮፕላንን የመሳሰሉ ቅርሶች ተመልሰዋል። በሙዚየሞች እና በግለሰብ አሰባሳቢዎች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/4npBi
Äthiopien Mekedela  Alula Pankhurst
ምስል Alula Pankhurst

አንድ ለአንድ፦ የኢትዮጵያን የተዘረፉ ቅርሶች የማስመለስ ፈተና ከዶክተር አሉላ ፓንክረስት ጋር

በመቅደላ ጦርነት እና በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች ተዘርፈው ተወስደዋል። በእንግሊዝ ጦር ከተወሰዱት መካከል በ27 ሙዚየሞች ምን አይነት ቅርሶች የት እንደሚገኙ በአግባቡ ተመዝግቧል። አልባሳት፣ ዘውዶች፣ ከሐይማኖት ጋር ቁርኝት ያላቸው መስቀሎች፣ ታቦቶች እና የብራና መጻህፍት ይገኙበታል። በሙዚየሞች የሚገኙ ቅርሶችን ማስመለስ ግን እንዲህ ቀላል አይደለም። 

“በእንግሊዝ ሀገር አንድ ቅርስ ብሔራዊ ሙዚየም ከገባ በፓርላማ አዋጅ ካልሆነ በስተቀር መመለስ አይቻልም የሚል ሕግ ስላለ በውሰት ካልሆነ በስተቀር በቀላሉ ለማስመለስ አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በእንግሊዝ ወታደሮች ቤተሰቦች እጅ የሚገኙ ቅርሶች በአንጻሩ አልፎ አልፎ ለጨረታ እንደሚቀርቡ ዶክተር አሉላ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት የተዘረፉት ቅርሶች “በጣም በርካታ” ቢሆኑም ዶክተር አሉላ እንደሚሉት የት እና በማን እጅ እንደሚገኙ የሚጠቁም የተደራጀ መረጃ የለም። ቅርሶቹን ለማስመለስ የት እንደሚገኙ መለየት እና ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን በባለቤትነት የያዟቸውን ወገኖች ማሳመን ይጠይቃል። 

ኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶች ለማስመለስ ያደረገችው ግፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የአክሱም ሐውልት ነው። በፋሺስት ጣልያን ወደ ሮም ከተጋዘ በኋላ በፒያዛ ዲ ፖርታ ካፔና አደባባይ ቆሞ የነበረው እና 24 ሜትር የሚረዝመው ሐውልት ከኃይለኛ ውትወታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው በሚያዝያ 2005 ነበር። ሐውልቱን ለማስመለስ የተደረገውን ጥረት በግምባር ቀደምትነት ካስተባበሩ መካከል የዶክተር አሉላ አባት እና ኢትዮጵያን ከፋሺስት ጣልያን ነጻ ለማውጣት የታገሉት የሲልቪያ ፓንክረስት ልጅ ሪቻርድ ፓንክረስት አንዱ ነበሩ ነበሩ። 

በኢትዮጵያ በመገጣጠም ቀዳሚ የሆነችው ጸሀይ የተባለች አውሮፕላን ከጣልያን የተመለሰችው በቅርቡ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት አመታት ታቦቶች፣ የብራና መጻህፍት፣ መስቀሎች ጭምር ቢመለሱም አሁንም በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንግሊዝ እና ጣሊያንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይገኛሉ።

አንድም በሙዚየሞች አንድም በግለሰብ አሰባሳቢዎች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል? ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ከዶክተር አሉላ ፓንክረስት ጋር ቃለ-መጠይቅ አድርጓል። ዶክተር አሉላ በሙያቸው የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ (Anthropologist) ናቸው።

በቅርቡ ከመቅደላ የተዘረፈ ጋሻ በልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ እና እርሳቸው ባቋቋሙት የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ድርጅት አማካኝነት ሲመለስ ተሳትፎ አድርገዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሉላ ፓንክረስት በስዊትዘርላንድ በጨረታ ለሽያጭ ቀርቦ የነበረ የራስ ደስታ ዳምጠው የወርቅ ሜዳይን ለማስመለስ በሚደረገው ግፊት ውስጥም ተሳትፎ አላቸው። 

ከዶክተር አሉላ ፓንክረስት ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ