1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዉሮጳ ለሩስያዉያን የጉብኝዎች ቪዛ ጉዳይ

ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2014

የአዉሮጳ ህብረት የዉጭ ጉዳይ ተጠሪ ጆሴፕ ቦሬል፣ ሩሲያውያን በቱሪስት ቪዛ ወደ አውሮጳ ህብረት እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ ማገድ የሚለዉን ሃሳብ "ጥሩ ነዉ ብለዉ እንደማያምኑ" ተናገሩ። የህብረቱ ከፍተኛ የዉጭ ጉዳይ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል በሰጡት ቃለ ምልልስ ህብረቱ ከሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳያቋርጥ ሲሉ ነዉ ያስጠነቀቁት።

https://p.dw.com/p/4GBwH
Estland | Eine Frau hält einen Russischen Pass
ምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

የአዉሮጳ ህብረት የዉጭ ጉዳይ ተጠሪ ጆሴፕ ቦሬል፣ ሩሲያውያን በቱሪስት ቪዛ ወደ አውሮጳ ህብረት እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ ማገድ የሚለዉን ሃሳብ  "ጥሩ ነዉ ብለዉ እንደማያምኑ" ተናገሩ። የህብረቱ ከፍተኛ የዉጭ ጉዳይ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል ለኦስትሪያ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ህብረቱ ከሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብ ጋር  ያለውን ግንኙነት እንዳያቋርጥ ሲሉ ነዉ ያስጠነቀቁት። እንዲህ ያለው መጠነ ሰፊ እርምጃ ምንም ዓይነት በጎ ውጤት አያመጣም፤ ወደ አዉሮጳ ተጓዥ ሩስያዉያን የጉዞ ፈቃድ «ቪዛ» ይዘጋ በሚለዉም አልስማማም ብለዋል። ህብረቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የአንድነት ውሳኔ ያስፈልገዋል ብለው እንደማያምኑም ቦሬል ተናግረዋል። ቦሬል ይህን የተናገሩት ዩክሬይን የሩሲያ ቱሪስቶች አውሮጳን እንዳይጎበኙ ስትል ያቀረበችዉን ጥያቄ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች በዚህ ሳምንት ለመወያየት በተዘጋጁበት ጊዜ ነዉ። የህብረቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነገ ማክሰኞ በፕራግ በሚጀምረው የሁለት ቀን ስብሰባ ላይ በዚህ ሐሳብ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ይህ ሩስያዉያንን የቱሪስት ቪዛ ለመከልከል የቀረበ ሃሳብ የህብረቱን አገሮች መከፋፈሉ ተነግሯል። አንዳንድ የህብረቱ አባል ሃገራት በሙሉ ልባቸው በሃሳቡ ሲስማሙ ሌሎች ግን  ተቃዋሚ ሩሲያውያን ትውልድ አገራቸውን ለቅቀው እንዳይሸሹ በር ይዘጋባቸዋል የሚል ስጋትን እንደፈጠረባቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። አንዳንድ ሩሲያ አጎራባች የህብረቱ ሃገራት ለሩሲያውያን የጉዞ ፈቃድ «ቪዛ» ላለመስጠት ወይም ለመገደብ ወስነዋል፤ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ በመላው የህብረቱ አባል ሃገራት ውስጥ እገዳዉ አልተጣለም። ከሩሲያ ጋር ረጅም የአውሮጳን ድንበር የምትካፈለዉ ፊንላንድ ከፊታችን ሐሙስ ጀምሮ ከሩሲያዉያን በቀን ከምትቀበላቸዉ 1,000 ሰዎች የቱሪስት ቪዛ ማመልከቻ ዉስጥ 10 በመቶ የሚሆኑትን ብቻ ለመቀበል ያወጣችዉን ህግ ተግባራዊ ታደርጋለች። የአዉሮጳ ህብረት አባል ሃገሮች የሆኑት ላትቪያ፣ ሊትዌኒያ እና ፖላንድ ከስድት ወር በፊት የካቲት ወር መጨረሻ ላይ የፑቲን መንግሥት ዩክሬንን መዉረር ሲጀምር ለሩስያ ዜጎች የቱሪስት የጉዞ ፈቃድ «ቪዛ» መስጠት ማቆማቸዉ ይታወቃል።

 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ