ዐይነ ሥውሩ የስፖርት ዘጋቢ በሀዋሳ ኤፍ ኤም 97.7
ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2016ዐይነ ሥውሩ የስፖርት ዘጋቢ
መሉቀን ደሣለኝ ይባላል ፡፡ አይነ ሥውርና የ25 ዓመት ወጣት ነው ፡፡ መሉቀን ዐይነ ሥውር ቢሆንም በሀዋሳ ኤፍ ኤም 97.7 ራዲዮ ላይ በተባባሪ የስፖርት ጋዜጠኝነት እያገለገለ ይገኛል ፡፡አሁን ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የጋዜጠኝነት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ወጣቱ አይነሥውር መሆኑ የስፖርት ዘገባ ከመሥራት እንዳላገደው ይናገራል ፡፡ ጋዜጠኛ መረጃዎችን አሰባስቦ እና ተንትኖ ለአድማጮቹ የሚያደርስ መሆኑን የጠቀሰው ሙሉቀን “ እኔ ይህንኑ የዘገባ ሥራ ለዛውም በስፖርት ዘርፍ እየሠራሁ እገኛለሁ ፡፡ እይታን ከሚፈልጉ ከኮሜንታተርነት እና ከዳኝነት ሥራዎች በስተቀር አንድ ዐይነ ሥውር ስፖርትን መዘገብ ይችላል “ ብሏል ፡፡አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
የጋዜጠኝነት ጅማሮ
ሙሉቀን በትምህርት ቤት ሳለሁ በሚኒ ሚዲያ አደርግ ነበር ያለው ተሳትፎ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ እንዲያዘነብል ምክንያት እንደሆነው ይናገራል ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመማር ሳለሁ ዘገባ ማቅረብ እንደምፈልግ የጠየኩት መምህሬ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ ነበረው ይላል ፡፡ ነገር ግን ከመጀመሪያ ሙከራ በኋላ በእኔ ላይ እምነት በመጣሉ በዕረፍት ሰዓት ለተማሪዎች የስፖርትና የመዝናኛ ዘገባዎች ማቅረብ መቀጠሉን የተናገረው ሙሉቀን “ ለእኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለወደፊት ሙያዬ መሠረት የጣልኩበት ነው ፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ የጋዜጠኝነት ሙያን ለመማር ዕድል ፈጥሮልኛል ፡፡ አሁን ላይ በዚሁ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የኤፍ ኤም ማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ በሳምንት ለሦስት ቀናት ሰፖርታዊና የመዝናኛ ዘገባዎችን እያቀረብኩ እገኛለሁ “ ብሏል ፡፡
ሰዎች ሥለ ሙሉቀን ምን ይላሉ ?
ወጣት ሙሉቀንን በቅርበት ከሚያውቁት መካከል በሀዋሳ ኤፍ ኤም 97.7 ራዲዮ አዘጋጅ ኤፍሬም ዱባለ አንዱ ነው ፡፡ ሙሉቀንን ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ እንደሚያውቀው የሚናገረው ጋዜጠኛ ኤፍሬም “ በርካታ አይነሥውራን የተለየ ተሰጥኦ እንዳላቸው ቀደምሲል ከነበረኝ ልምድ ሥለማውቅ ለእኔ ብዙም አልገረመኝም ፡፡ ነገር ግን የጣቢያውን የስፖርት ዘገባዎች የሚከታተሉ አድማጮች ሙሉቀን አይነሥውር መሆኑን በአጋጣሚ ሲሰሙ ለማመን ሲቸገሩ ተመልክቻለሁ ፡፡ አንዳንዶቹም ራዲዮ ጣቢያው ድረስ መጥተው በማየት ይገረማሉ “ ብሏል ፡፡የስፖርት ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ዜና ዕረፍት
ወጣት ሙሉቀን በበኩሉ ዘገባውን የሚከታተሉ በዙሪያው የሚገኙ ሰዎች በጎ አስተያየት እንደሚሰጡት ተናግሯል ፡፡ በተለይም ዐይነሥውርነትን ጨምሮ የተለያዩ የአካል ጉዳቶች ያሉባቸው ሰዎች አይቻልም ብለን የምናስባቸውን ነገሮች እንደሚቻሉ አሳይተኸናል በማለት የሚያመሰግኑት እንዳጋጠሙትም ጠቅሷል፡፡ አሁን ላይ ከራዲዮ ጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ “ ዐይነሥውሩ “ የተሰኘ ቲክ ቶክ በመክፈት የስፖርት ዘገባዎችን በማቅርብ ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ሙሉቀን ወደፊት በስፖርት እና በመዝናኛ ጋዜጠኝነት ዘርፍ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ራዕይ እንዳለው ተናግሯል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ