1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የተገን አሰጣጥ ስምምነት የሚጠበቀውና ተግዳሮቶቹ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 2016

አባል ሀገራት በአንድ ስደተኛ 20 ሺህ ዩሮ ከከፈሉ ስደተኞችን ለመውሰድ አይገደዱም።ገንዘቡም በብራሰልስ በሚተዳደር የባንክ ሂሳብ ውስጥ ይቀመጣል ነው የተባለው። ይህም አባል ሀገራት በስደተኞች ለተጨናነቁት ሀገራት ኅብረታቸውን የሚገልጹበት አማራጭ ነው። በአዲሱ ስምምነት ስደተኞችን ወደ ሌሎች ሀገራት መውሰድም ይኖራል።

https://p.dw.com/p/4g7Li
ስደተኞች በለንቋሳ ጀልባ በኩል የእንግሊዝ ቻናልን ሲቋርጡ
ስደተኞች በለንቋሳ ጀልባ በኩል የእንግሊዝ ቻናልን ሲቋርጡ ምስል Dan Kitwood/Getty Images

የአዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የተገን አሰጣጥ ስምምነት ተግዳሮቶች

አዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የተገን አሰጣጥ ስምምነት ወደ ኅብረቱ አባል ሀገራት የሚደረግ ፍልሰትን መቆጣጠር እና የጋራ የተገን አሰጣጥን መዘርጋት የሚያስችሉ የተባሉ አዳዲስ ደንቦችን ያካተተ ነው። ኅብረቱን ለብዙ ዓመታት ሲፈታተኑ ለቆዩት ከፍልሰትና ከተገን አሰጣጥ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የጋራ መፍትሔ ይሆናል የተባለውን ይህን ስምምነት የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ባለፈው ሚያዚያ አጸድቆታል። የኅብረቱ አባል ሀገራት መንግሥታትም ፣ ኅብረቱ ጠንካራና ደኅንነታቸው የተጠበቀ ድንበሮች እንዲኖሩት እና ማንኛውም የኅብረቱ አባል ሀገር የስደተኞች ጫናን ብቻውን እንዲቋቋም እንዳይተው ያደርጋል የተባለውን ይህንኑ ስምምነት ባለፈው ሳምንት አጽድቀውታል።የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና የጥገኝነት አሳጣጥ ፖሊሲ ማሻሻያ ይሁንና ኅብረቱ ሕገ ወጥ በሚለው መንገድ ወደ አባል ሀገራት ለመግባት የሚሞክሩ ፍልሰተኞች ይሰተናገዱበታል የተባሉ ደንቦችን ያካተተውን ይህን ስምምነት ሀንጋሪና ፖላንድ  ሳይቀበሉት ቀርተዋል። አዲሱ ስምምነት አባል ሀገራትን ሲያወዛግብ ለቆየው የስደተኞች ጫና ባመዘነባቸው ሀገራት የሚገኙ ፍልሰተኞችን መከፋፈልን ያካትታል። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሀገራት ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጡ ያስገድዳል። ይሁንና ይህ በተለይ በሀንጋሪና በፖላንድ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ። የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ ስምምነቱ ከጸደቀ በኋላ ምክንያታቸውን ተናግረው ነበር። ቱስክ እንዳሉት በስምምነቱ መሠረት ፖላንድ ሌላ ተጨማሪ ስደተኛ ልትቀበል አትችልም፤ መቀበልም የለባትም ።

የግሪክ የድንበር ፖሊስ በግሪክና ቱርክ የድንበር አጥር አጠገብ
የግሪክ የድንበር ፖሊስ በግሪክና ቱርክ የድንበር አጥር አጠገብ ምስል Alexandros Avramidis/REUTERS


« የፖላንድ መንግሥት የፍልሰተኞች ጉዳይ ስምምነቱን ተቃውሞ ነው ድምፅ የሰጠው። ፖላንድ በፍልሰተኞች ጉዳይ ስምምነት መሠረት ማናቸውንም ፍልሰተኞች አትቀበልም። ፖላንድ በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን አስጠግታለች። ከቤላሩስ የመጡትን ጨምሮ በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች እና ጋ ይገኛሉ። ይህ የኔ ሃላፊነት ነው። ፖላንድ ከስምምነቱ ተጠቃሚ ናት። ሆኖም ለምንም ጉዳይ ቢሆን አንከፍልም። ከሌላ አቅጣጫ የሚመጡ ስደተኞችን መቀበልም የለብንም ። ምክንያቱም ፖላንድ ከኅብረቱ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት እንድትችል ኅብረቱ ገንዘብ እንዲከፍላት ማስገደድ እየቻለት ኅብረቱ የስደተኞች ኮታ በግዳጅ አይጥልብንም። በዚህ የተነሳ ሀገሪቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በዋነኛነት የዩክሬን ስደተኞች አስተናጋጅ ሆናለች።»ጀርመንና የአውሮጳ ህብረት የጋራ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ

በአዲሱ ስምምነት መሠረት አባል ሀገራት በአንድ ስደተኛ 20 ሺህ ዩሮ ወይም 21 ሺህ 553 ዶላር ከከፈሉ ስደተኞችን ለመውሰድ አይገደዱም።ገንዘቡም በብራሰልስ በሚተዳደር የባንክ ሂሳብ ውስጥ ይቀመጣል ነው የተባለው። ይህም አባል ሀገራት በስደተኞች ለተጨናነቁት ሀገራት ኅብረታቸውን ለመግለጽ የተቀመጠላቸው  አማራጭ ነው። በአንድ በኩል ከጎርጎሮሳዊው 2015ና 2016 በኋላ እንደነበረው ስደተኞችን ወደ ሌላ ሀገር መውሰድ ይኖራል። በሌላ በኩል ደግሞ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሁም የቁሳቁስ እርዳታ የስጠት አማራጭም እንዳለ ሄሌና ሀን የተባሉ የፍልሰት ጉዳዮች አዋቂ በአንድ ወቅት ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር። አውራ የሚባሉት የአውሮጳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ስምምነቱ ፍልሰተኞች አውሮጳ ሲደርሱ ማን ሃላፊነቱን ይወስዳል በሚል ከዚህ ቀደም ይነሳ የነበረውን ውዝግብ ያስቆማል የሚል ተስፋ ጥለውበታል። ሁሉም በሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋቱንም ያወድሳሉ። ይሁንና ከፖላንድና ከሀንጋሪ በኩል የተነሳው ተቃውሞ ችግር ሊያስከትል የመቻሉ ስጋት መኖሩ አልቀረም። የብራሰልሱ ዘገባያችን ገበያው ንጉሴ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ተንታኞች ጠቅሶ እንደተናገረው እነዚህ ሀገራት ፍልሰተኞችን በመጋራቱ አሰራር ውስጥ አንሳተፍም ካሉ ችግሩን ይበልጥ ሊያወሳሰበው ይችላል የሚል ፍርሀትም አለ። ገበያው ይህን ከማንሳቱ በፊት በአዲሱ ሕግ የተካተቱ ማሻሻያዎችን ያስታውሳል።

የፖላንድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ
የፖላንድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክምስል Lukasz Gagulski/EPA


በአዲሱ ስምምነት ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎችን  ማባረሩ እንዲፋጠን ይደረጋል። በእቅዱ መሠረት የተሻለ ደኅንነት አላቸው ከሚባሉ ሀገራት የመጡ ስደተኞች ማመልከቻዎችን ድንበር ላይ በፍጥነት ለማየትም ታስቧል። የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ማሻሻያው በተለያዩ ምክንያቶች ስደተኞችን የሚገፋ ነው በማለት ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።ከዚህ ቀደም  የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራትን ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሲሉ እንደ ኦክስፋም የመሳሰሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች  ኮንነዋቸው ነበር።  የስደተኞች መብት ተሟጋቾም ውሳኔው ሃላፊነትን ወደ ጎን የተወ ፣ለሌላው ዓለም መጥፎ ምሳሌ ሲሉ ገና ማሻሻያው በኅብረቱ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች በእቅድ ደረጃ በቀረበበት ወቅት አጣጥለውት ነበር። አደገኛው የባሕር ላይ ስደትና እልቂት
አዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የፍልሰትና ተገን ጠያቂዎች የሚስተናገዱበት ሕግ አሁንም ከብዙ አቅጣጫ ትችቶችን ማስተናገዱ አልቀረም። ገበያው እንደሚለው በተለይም አዲሱ ሕግ ቀኝ ጽንፈኞች የስደተኞችን ጉዳይ የምርጫ ዘመቻ አጀንዳቸው ማድረጋቸውን የሚከላከል የመራጩን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል በሚል የሚቀርበውን መከራከሪያ ተችዎች ውድቅ እያደረጉ ነው።የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መንግሥታት በይፋ ካጸደቁት የኅብረት የፍልሰትና የተገን አሰጣጥ ደንቦች አብዛኛዎቹ ገቢራዊ የሚሆኑት በጎርጎሮሳዊው 2026 ዓም ነው። በዚህ የተነሳም መራጩ ህዝብ በቀኝ ጽንፈኞች አጀንዳዎች እንዳይጠለፍ ማድረግን ጨምሮ የኅብረቱን ከባድ የፖለቲካ ቀውስ ሲያጋግሉ ለነበሩት ሌሎች ጉዳዮች አስቸኳይ መፍትሄ ያመጣሉ ተብሎ አይታሰብም ።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ