አዲስ አበባ፤ የኩፍኝ በሽታ ምልክት በሁሉም ክልል ከተሞች መታየቱ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 13 2015ኢትዮጵያ ውስጥ የኩፍኝ በሽታ ምልክት በሁሉም ክልል ከተሞች መታየት መጀመሩ ተነገረ። ይህንን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ለ 10 ቀናት የሚቆይ የኩፍኝ በሽታ ክትባት ዘመቻ መጀመሩን ዛሬ አስታውቋል። የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በዛሬው ዕለት ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለይ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ኅብረተሰቡ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ችግሩ ተባብሶ አስከፊ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ክትባቱ መስጠት እንደጀመረ አመልክቷል። ለዚህም በሽታው ሊያጠቃ በሚችለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሕጻናት እና አዳጊዎች መክተብ እንዳለባቸው የጤና ቢሮው አስታውቋል። የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የተከተቡም ቢሆኑ በዚህ ዘመቻ ክትባቱን ድጋሚ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
«ከበሽታው ከፍተኛ የመተላለፍ እና በወረርሽኝ መልክ የመከሰት ባህርይ የተነሳ በብዙ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተከሰተ በመሆኑ ጤና ሚኒስቴር ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት የሆኑ ሕጻናትን በሙሉ ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም በዘመቻ መልክ የሚሰጠውን ተጨማሪ ክትባት እንዲወስዱ፤ በዚሁ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ለ520 ሺህ ሕጻናት በጡና ጣቢያዎች እና በጊዜያዊ በተመረጡ የክትባት ጣቢያዎች ለመስጠት ታቅዷል።»
በዛሬው ዕለት የተጀመረው የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ እስከ ታኅሣስ 22 ቀን 2022 እንደሚዘልቅም ተገልጿል። የታሰበውን የክትባት ዘመቻ ስኬታማ ለማድረግም 4,500 የጤና ባለሙያዎች፣ የቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ፈቃደኞች ይሳተፉበታል ተብሏል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ ወረርሽ|ን ምክንያት ተጓዳኝ ተላላፊ በሽታዎች ትኩረት ሳይሰጣቸው መቆየቱን ያመለከቱት የጤና ቢሮ ኃላፊው በክትባት ዘመቻው ከኩፍኝ በሽታ በተጨማሪ ሌሎች የሕጻናት በሽታዎች ምርመራም እንደሚከናወን ገልጸዋል።
አያይዘውም በአዲስ አበባ ልጆቻቸዉን ለማስከተብ ለሚመጡ እና ህክምና ለሚያስፈልጋቸው እናቶች ቢኖሩ ነፃ ህክምና እንዲያገኙ መመቻቸቱንም አስታውቀዋል። ክትባቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ጤና ጣቢያዎች እና በተመረጡ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ሃና ደምሴ ከአዲስ አበባ በላከችው ዜና ጠቅሳለች።