1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ የ2022 ክንዉኗ፣ የ2023 ዕቅዷ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 22 2015

በ2022 በርካታ ሕዝብ ከተገደለ፣ከሞተ፣ከተፈናቀለና ከተሰደደባቸዉ 20 ሐገራት አስራ አንዱ የአፍሪቃ ሐገራት ናቸዉ።ሶማሊያ፣ኢትዮጵያ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ደቡብ ሱዳን፣ቡርኪና ፋሶ፣ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ቻድ፣ማሊ፣ኒጀር፣ ናጄሪያ እና ሱዳን።

https://p.dw.com/p/4LaTC
Africa Cup of Nations 2022 | Kamerun vs. Burkina Faso
ምስል Ulrik Pedersen/NurPhoto/picture alliance

ከኢትዮጵያ እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ከጊኒ እስከ ሶማሊያ፣ከሊቢያ እስከ ደቡብ  አፍሪቃ፣ከማዳጋስካር እስከ ሞሮኮ  ሰላምና ጦርነት፣መፈንቅለ መንግስትና ምርጫ፣ የተፈጥሮ መቅሰፍትና የኳስ ጨዋታ ድል የተፈራረቀበት የግሪጎሪያኑ 2022 ዛሬ እኩለ ሌሊት ያበቃል።2023 ለአፍሪቃ ከተሰናባቹ ዓመት ባንድ ነገር ይሻላል።ተስፋ።በዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን አሮጌዉን ዕዉነት ካዲሱ ተስፋ አሰባጥረን  ባጭሩ እንቃኛለን።አብራችሁኝ ቆዩ።
ዓለም አቀፍ አዳኝ ኮሚቴ (IRC በምሕፃሩ) የተባለዉ ድርጅት እንደዘገበዉ  በልማዱ «ሰዉ ሰራሽና የተፈጥሮ« የሚባሉት አደጋዎች ወይም መቅሰፍቶች በ2022 በርካታ ሕይወት፣ ሐብት ንብረት ያጠፉት፣ ብዙ ሕዝብ ያሰደዱ ያፈናቀሉት በ20 ሐገራት ዉስጥ ነዉ።IRC የተመሰረተዉ በጀርመናዊዉ-የሁዳዊ ሳይቲስ አልበርት አይንሽታይን አሳሳቢነት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1933 ነበር።
የሁዲዎችን የጀርመን ናዚ ስርዓት ከሚያደርስባቸዉ ግፍ ለማሸሽ ወይም የሚሸሹትን ለመርዳት ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የተመሰረተዉ ኮሚቴ በመላዉ ዓለም ቀዉስ ባለባቸዉ አካባቢዎች ለአደጋ የተጋለጡ ችግረኞችን ሁኔታ ያጠናል።ድጋፍ እንዲያገኙ ይጥራልም።

የቀዉሶች መዘዝ
ኮሚቴዉ በቅርቡ እንዳስታወቀዉ በ2022 በርካታ ሕዝብ ከተገደለ፣ከሞተ፣ከተፈናቀለና ከተሰደደባቸዉ 20 ሐገራት 11 የአፍሪቃ ሐገራት ናቸዉ።ሶማሊያ፣ኢትዮጵያ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ደቡብ ሱዳን፣ቡርኪና ፋሶ፣ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ቻድ፣ማሊ፣ኒጀር፣ ናጄሪያ እና ሱዳን።
በእነዚሕ ሐገራት ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በተንከባለለ ይሁን ዘንድሮ በተጫረ ጦርነት፣ግጭት፤ ፖለቲካዊ ቀዉስ ወይም የተፈጥሮ በሚባሉት ድርቅ፣ ረሐብና ጎርፍ ሚሊዮኖች አልቀዋል።ብዙ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።ሌሎች ተርበዋል።
የአስቸኳይ ድጋፍ መዘርዝር የተባለዉን ጥናት ያደረገዉ የIRC የበላይ ጆርጅ ሪዲንግስ እንደሚሉት በጣም አሳሳቢዉ እስካሁን በደረሰዉ ቀዉስና መቅሰፍት ሚሊዮኖች ማለቅ፣ መቸገራቸዉ ብቻ አይደለም።ቀዉሶቹ እየባሱና እየከፉ መምጣታቸዉ እንጂ።
«የዘንድሮዉ የአስቸኳይ ድጋፍ መዘርዝር በጣም አስፈላጊ መልዕክት፣ቀዉሶቹ እየባሱ፣እየበዙ መምጣታቸዉ ነዉ።»
በ2014 አስቸኳይ ርዳታ ፈላጊዉ ሕዝብ 81 ሚሊዮን ነበር።በ2022 ግን ወደ 339 ሚሊዮን አሻቅቧል።ከዚሕ ህዝብ ከ85 ከመቶ የሚበልጠዉ የአፍሪቃ ሐገራት ህዝብ ነዉ።የችግረኛዉን ቁጥር ለመቀነስ በተለይ ሞትና አስከፊ ችግርን ለማቃለል መሰረታዊዉ መፍትሔ ጦርነት፣ግጭትና ፖለቲካዊ ቀዉስን የመሳሰሉ መሰረታዊ ምንጮችን ማድረቅ ነዉ።ካልተቻለስ «ማድረግ የምንችለዉ አለ» ይላሉ ጆርጅ ሪዲንግስ።
 «ልናደርጋቸዉ የምንችላቸዉ ጉዳዮች አሉ።ቀዉሶቹ በማሕበረስቡ ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት የምንከላከል ወይም የምንቀንስበት አጥር ማበጀት እንችላለን።ባሁኑ ጊዜ እነዚያ አጥሮች በጣም ተዳክመዋል።ይሁንና ያላሰለሰ የጋራ ጥረት ካደረግን እጥሮቹን መልሰን መገንባት በዉጤቱም የሚያስፈልገዉን የሰብኣዊ ርዳታ መጠንና በዓለም ላይ ያለዉን የቀዉሱ ደረጃን መቀነስ እንችላለን።»
ሪዲንግስ «አጥር» የሚሉት ቀዉሶቹን የሚጎዱትን ሕዝብ መጠን አጥንቶ፣ ድጋፍ ለመስጠት አስቀድሞ መዘጋጀትና መደራጀትን ነዉ።አስቀድሞ የማጥናት፣ የመዘጋጀቱ አስፈላጊነት በርግጥ አላጠያየቀም።ፍቃደኝነቱ እንጂ ጭንቁ።
አጥኚዉ ኮሚቴ እንደሚለዉ ለሞትና ችግር ከተጋለጠዉ ሕዝብ 80 በመቶዉን የጎዳዉ ጦርነት፣ግጭትና ፖለቲካዊ ቀዉስ ነዉ።ከ11ዱ የአፍሪቃ ሐገራት አብዛኞቹ በጦርነት፣ግጭትና ፖለቲካዊ ቀዉስ የሚወድሙ ናቸዉ።ድርቅ፣ረሐብ፣ጎርፍ በርካታ ሕዝብን በመጉዳት ቅደም ተከተል ሁለተኛ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ቀዉስ ደግሞ ሶስተኛዉን ስፍራ ይይዛሉ።
                                                   

የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ገቢራዊነት
የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት የሰላም ስምምነት ገቢራዊነትምስል Million Hailesilassie/DW

አፍሪቃ ከዛሬ እኩለ-ሌሊት በኋላ አዲስ በምንለዉ በግሪጎሪያኑ 2023 ዓመት በ17 ሐገራት የምክር ቤት ወይም የርዕሳነ-ብሔራት ምርጫ ታስተናግዳለች።ዘ-ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት የተሰኘዉ አጥኚ ተቋም እንደሚለዉ ምርጫዎቹ የአሐጉሪቱን መፃኤ ዕድል በጅጉ የሚበይኑ ናቸዉ።የየምርጫዉ ዝግጅት፣ሒደትና ዉጤት፣የተቋሙ ጥናት እንደሚያመለክተዉ፣የሁከት፣ዉዝግብ፣ግጭት ጊዜ ሊሆንም ይችላል።በብዙ ሐገራት አመፅ፣ተቃዉሞ ሰልፍ፣አድማ ሊከሰት ይችላልም።

ISS በሚል የእንግሊዚኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም የበላይ ኃላፊ ፎንቴሕ አኩም እንደሚሉት ደግሞ በ2022 በየሐገሩ የተደረገዉ መፈንቅለ መንግስት በመጪዉም ዓመት መቀጠል-አለመቀጠሉም በጊዜና በፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ የተንጠለጠለ ነዉ።
«ከሁሉም በፊት፣በ2022 በአሐጉሪቱ ያየነዉ የመፈንቅለ መንግስት ድራማ በ2023ም መቀጠል-አለመቀጠሉ ወይም ወደፊት የሚታይ ነዉ።በተለይ በቅርቡ ሳኦቶሜና ፕሪሲፔ የተደረገዉን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ስናጤን ጉዳዩ ማሳሰቡ አይቀርም።»

የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ሁንታ መሪ ሻምበል ኢብራሒም ትራኦሬ
የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ሁንታ መሪ ሻምበል ኢብራሒም ትራኦሬምስል Kilaye Bationo/AP Photo/picture alliance

የጊኒ ባሕረ ሰላጤይቱ የተጫፋሪ ደሴቶች ሐገር ባለስልጣናት እንዳሉት ባለፈዉ ሕዳር 25 የተቃጣባቸዉን መፈንቅለ መንግስት አክሽፈዋል።የትሺቱ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሐገር የጋምቢያ ባለሥልጣናትም ባለፈዉ ታሕሳስ 26 ከተሞከረባቸዉ መፈንቅለ መንግስት መትረፋቸዉን አስታዉቀዋል።
በዚሕም ምክንያት አፍሪቃ በ2023 ዴሞክራሲዊ ፖለቲካዊ ሒደት ይጠናከርባታል ወይስ ይበልጥ ይገፋባት ይሆን የሚለዉ ጥያቄ የብዙዎች እንደሆነ መቀጠሉ አይቀርም።
«ትኩረት የሚሰጣቸዉ ምርጫዎች ናይጄሪያ፣ደቡብ አፍሪቃ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ዚምባቡዌ ዉስጥ የሚደረጉት ናቸዉ።ከነዚሕ ሐገራት በተወሰኑት ሁከት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል  ስጋት አለ።»
ይላሉ ቻተም ሐዉስ የተባለዉ የብሪታንያ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ ኃላፊ አሌክስ ቪኔስ።
አይኖች ሁሉ ወደናጄሪያ ያማትራሉ
ናይጄሪያ ዉስጥ በመጪዉ የካቲት ማብቂያ ምርጫ ይደረጋል።በርካታ የሲቪክ ማሕበራትና የፖለቲካ አቀንቃኞች በተለይ ወጣቶችን ለማስተማርና ለማሳወቅ እየተጣሩ ነዉ።ይሁንና ከአፍሪቃ በሕዝብ ቁጥር  አቻ የሌላት ናይጄሪያ በፖለቲካ ሁከትና አለመረጋጋት እየተናጠች ነዉ።አኩም እንደሚሉት «የናጄሪያ ምርጫ በጣም አስፈላጊ ነዉ» ምክንያት አላቸዉ።
                             
«የናጄሪያ ፖለቲካዊ ምርጫ በእዉነቱ በጣም አስፈላጊ ነዉ።ምክንያቱም ሐገሪቱ በሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከአሐገሪቱ ሐብታም ሐገራት አንዷ በመሆኗ።ፀጥታ ለማስከበርም እየታገለች ነዉ።»
217 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን ናጄሪያን እስካሁን የመሩት መሐመዱ ቡሐሪ ለሁለት ዘመነ-ሥልጣን በመምራታቸዉ በየካቲቱ ምርጫ አይወዳደሩም።ስለዚሕ ምርጫዉ የፖለቲካ መርሕ ብቻ ሳይሆን የመሪ ለዉጥም የሚደረግበት ነዉ- የፖለቲካ ተንታኝ አኩም እንደሚሉት።
በስልጣን ላይ ያለዉ የመላዉ ተራማጅ ኃይሎች ምክር ቤትና ዋነኛዉ ተቃዋሚ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ  እጩዎች ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ናቸዉ።ይሁንና አኩም እንደሚያምኑት የሶስተኛዉ  የሰራተኛ (ሌበር) ፓርቲ ዕጩ ፉክክሩ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፋቸዉ አይቀርም።የሰራተኛ ፓርቲ ዕጩ ነጋዴዉ ፖለቲከኛ ፒተር ኦቦ በናጄሪያ ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸዉ።
የምዕራብ አፍሪቃ ቀዉስ እንደቀጠለ ነዉ
ምዕራብ አፍሪቃ በፅንፈኞች፣ በወርሮበሎች፣በሽፍቶች ጥቃት፣እገታና ዘረፋ እየታበጠች ነዉ።ማሊና ቡርኪና ፋሶ ደግሞ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ሁለት፣ሁለት ጊዜ፣ ጊኒ አንዴ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎባቸዋል።ወደ ሳሕል ዝቅ ሲል ደግሞ ቻድም፣ሱዳንም የጦር መኮንኖች በመፈንቅለ መንግስት ወይም መፈንቅለ መንግስት በመሰለ እርምጃ ሥልጣን እንደተቆጣጠሩ ናቸዉ።የነዚሕ ሐገራት ሽግግር እንዴት ነት ያዉ በይደር የሚታይ ነዉ።
ቀዉሱ ግን በመጪዉ ዓመት መስከኑን የቻተም ሐዉሱ የፖለቲካ ተንታኝ አሌክስ ቪነስ ይጠራጠራሉ።ናጄሪያና ካሜሩን  ግዛቶች ዉስጥ የሚደረገዉ ግጭትም ወደ መጪዉ ዓመት ላለመሸጋገሩ ምንም ዋስትና የለም።
«እንዳለመታደል የአሐጉሪቱ ቀዉስ በ2023ም ይቀጥላል።በተለይ በሳሕል፣ በጣሙን ደግሞ ማሊ፣ቡርኪና ፋሶ ኒዠርም።ካሜሩንና ናጄሪያ ዉስጥም ያለዉ ከፍተኛ የፀጥታ ቀዉስ በጣም አሳሳቢ ነዉ »
የአፍሪቃ ቀንድን ሰላም ሲበዛ ያሰጋዉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዘንድሮ ቆሟል።ዋነኞቹ ተፋላሚ ኃይላት የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ገቢር ማድረጋቸዉ ለብዙዎች ተስፋ ሰጪ ነዉ።አብዛኛዉ ዓለም ትኩረት ያልሰጠዉ የምዕራብ ኢትዮጵያና የሌሎችም አካባቢዎች የጎሳ ግጭት፣ግድያና ሥርዓተ አልበኝነት ግን በህዝብ ቁጥር ሁለተኛዉን ደረጃ የምትይዘዉ የኢትዮጵያን የሰላም ተስፋን-ከቀቢፀ ተስፋ ጋር አቃርጦታል።

USA I Biden hält ein bilaterales Treffen mit dem südafrikanischen Präsidenten Cyril Ramaphosa
ምስል Pete Marovich/UPI Photo/IMAGO

የሱዳን ወታደራዊ ገዢዎችና የሐገሪቱ የሲቢል ፖለቲከኞች የሲቢል አስተዳደር ለመመስረት ባገባደድነዉ ወር መጀመሪያ ያደረጉት ስምምነት በርግጥ ተስፋ ሰጪ ነዉ።ያሁኑ ስምምነት እንደከዚሕ ቀደሙ ላለመደፍለቁ ግን ምንም ዋስትና የለም።
ደቡብ ሱዳን ጥግን ግን ስምምነት የተደገፈዉ ሰላሟ ዘንድሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ  ከብዙዎቹ ጎረቤቶችዋ የተሻለ ነዉ።ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለ።
ሶማሊያ ዘንድሮ አዲስ ፕሬዝደንት መርጣለች።በአሸባብ የሽብር ጥቃት፣በሶማሊያ መንግስት፣ በአፍሪቃ ሕብረትና በዩናይትድ ስቴትስ ጦር አፀፋ ጥቃት የሚያልቀዉ፣በረሐብና ችጋር የሚሞት፣ የሚሰቃየዉ ህዝብ ቁጥር ግን ማየሉ እንጂ የመቀነስ አዝማሚያ አላሳየም።

120 አማፂ ቡድናት የሚፈኑጩባት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የመንግስት ጦር፣ተባባሪዎቹ ሚሊሺያዎች፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወታደሮችም ሰላም ሊያሰፍኑላት አልቻሉም።ሰፊይቱ፣የማዕድን ሐብታሚቱ ሐገር ዘንድሮ የኬንያ፣የዩጋንዳ፣የብሩንዲ፣የደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮችን አስፍራለች።ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ በ1990ዎቹ ማብቂያ እንደነበረችበት  በመጪዉ ዓመትም ብዙ  የአፍሪቃ ሐገርን ባሳተፈዉ ዉጊያ መሐል ለምርጫም ትዘጋለች።የጦር ኃይሉ ርምጃም ሆነ ታሕሳስ 2023 ይደረጋል የተባለዉ ምርጫ ለሰላምና ዴሞክራሲ መፈየድ-አለመፈየዱ ለግምት አዳጋች ነዉ።
የፖለቲካ ተንታኝ አሌክስ ቪነስ የምስራቅ ኮንጎንም ሆነ የሰሜን ሞዛምቢክ ሰላም አሳሳቢ ከማለት ሌላ ሌላዉን መገመት አልቻሉም።«ምስራቃዊ ኮንጎ የግጭት ማዕከል ነዉ።ሰሜናዊ ሞዛምቢክም አሳሳቢነቱ እንደቀጠለ ነዉ።

ዚምባቡዌ ፖለቲካዊ ቀዉስና ጣራ ዘለሉ ግሽበት

ዚምባቡዌ ከዓመታት በፊት የተጣባት የምጣኔ ሐብት ድቀት በመጪዉ ዓመትም ይቃለላል ተብሎ አይታሰብም።ምርጫ ግን ታደርጋለች።አንጋፋዉ ተቃዋሚ  ፖለቲከኛ ኔልሰን ቻሚሳ አዲስ የመሰረቱት «የዜጎች ሕብረት ለለዉጥ» የተሰኘዉ የፖለቲካ ፓርቲ የበርካታ ዜጎችን በጣሙን የወጣቶችን ልብ እያማለለ ነዉ።አዲሱ የለዉጥ ፓርቲ የሚያመጣዉ ለዉጥ በርግጥ ላሁኑ አይታወቅም።ይሁንና  አንጋፋዉ ገዢ ፓርቲ የዚምባቡዌ የአፍሪቃ ብሔራዊ አንድነት-አርበኞች ግንባር ፓርቲ (ZANU-PF)ን ጫናን ለመቋቋም እየተፍጨረጨረም ነዉ።ኔልሰን ቻሚሳም የፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ተጠንካራ ተፎካካሪ መሆናቸዉ አይቀርም።
 

ደቡብ አፍሪቃን የጥቂት ነጮችን ዘረኛ አገዛዝ ካስወገደች ከ1994 ጀምሮ የሚገዛት የደቡብ አፍሪቃ፣የአፍሪቃዉያን  ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC)  ሲርየል ራማፎዛን ለፓርቲዉ መሪነት በድጋሚ መርጧቸዋል።ፕሬዝደንት ራማፎዛ የፓርቲዉን የመሪነት ስልጣን እንደያዙ እንዲቀጥሉ የተመረጡት በሙስና በተለይም ምንጩን በግልፅ ያልስታወቁት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ደብቀዉ በመገኘታቸዉ ስልጣን እንዲለቁ በሚጠየቁ፣በሚወቀሱበት መሐል ነዉ።
ራማፎዛ ካፓርቲያቸዉ አዲስ ባድጋፍ ተጠናክረዉ የተቃዋሚዎቻቸዉን «አፍ ለማዘጋት» ገና ካሁኑ አንድ-ሁለት እያሉ ነዉ።በሚቀጥሉት 12 ወራት ተቃዋሚዎቻቸዉን አዳክመዉ በ2024 በሚደረገዉ ምርጫ ያሸንፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 
ብቻ አፍሪቃ ሰሜን ጫፍ ላይ የተቀመጠችዉ ሞሮኮ ከስደተኞች መሰቃያ፣መተላለፊያነት፣ ከፖሊስ አርዮ-አልጄሪያ ጋር በገጠመችዉ አሰጥአገባ መሐል በእግር ኳሱ ራስዋን ከፍ፣የተቀረዉን አፍሪቃ ዘና ኮራም አድርጋ አመቱን ተሰናበታች።
በዘመኑ ለምታሰሉ መላካም አዲስ ዓመት።
ነጋሽ መሐመድ 

የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝደንት ሲሪየል ራማፎዛ
የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝደንት ሲሪየል ራማፎዛምስል Denis Farrell/AP Photo/picture alliance

እሸቴ በቀለ