ኢትዮጵያ እና የሽብር ጥቃት ስጋት
እሑድ፣ መስከረም 18 2012ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2001 ዓም በአሸባሪዎች ጥቃት ከደረሰባት ጊዜ አንስቶ ራሷ ዩናይትድ ስቴትስ የምታስተባብረው ዓለም በተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪ በሚባሉ ቡድናት ላይ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ከፍቷል። አፍጋኒስታን የተጀመረው ዓለም አቀፍ ጸረ-ሽብር ዘመቻ ከእስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ አልፎ አፍሪቃ ውስጥም በተለያዩ ሃገራት ውስጥ በሚገኙ ቡድናት ላይ ተከፍቷል። የጎላው ጸረ-ሽብር ዘመቻ ምዕራብ አፍሪቃ ናይጀሪያ ውስጥ የሚገኘው ቦኮሃራም የተባለው አሸባሪ ቡድን ላይ የተከፈተው ነው። ምሥራቅ አፍሪቃ ውስጥ ደግሞ አልሸባብ በተባለው የሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ላይ የተከፈተው ዘመቻ በዋናነት ይጠቀሳል።
ሶማሊያ ውስጥ ለአጭር ጊዜያትም ቢኾን በዋናነት መዲናዪቱ ሞቃዲሾን ይዞ ብቅ ያለው እስላማዊ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ኅብረት (ICU) የተባለውን መንግሥት ለማስወገድ ኢትዮጵያ ጦሯን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ዓም ወደ ሶማሊያ አዝምታለች። በዓመቱ ኅብረቱ ከሶማሊያ ሲወገድ በስሩ የነበሩ በአብዛኛው ወጣቶች ያሉበት አንጃ አልሸባብ የተሰኘውን ደፈጣ ቡድን መስርተዋል። ይህ አልሸባብ የተባለ አሸባሪ ቡድን እስከዛሬ ድረስ ሶማሊያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ አደጋ እየጣለ ነው። ቡድኑ ከሶማሊያም አልፎ ኬንያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ባደረሰው የሽብር ጥቃት በርካቶችን ገድሏል፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል።
የአፍሪቃ ኅብረት ከተባበሩት መንግሥታት እና ከአውሮጳ ኅብረት ጋር በመተባበር ቡድኑን ለማጥፋት የአፍሪቃ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (AMISOM) በሚል ስያሜ ወደ ሶማሊያ ያዘመተው ጦር አልሸባብን ሞቃዲሾን ጨምሮ ከትልልቅ ከተሞች ማስወጣት ቢችልም፤ አሸባሪውን ቡድን ግን እስከዛሬ ድረስ ማጥፋት አልተሳካለትም። እንደውም የአልሸባብ ጥቃት ሶማሊያ ውስጥ ከሰሞኑ ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል።
በአሚሶም ውስጥ በርካታ ጦር ካዘመቱ ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። እስካሁን ድረስ በአንጻራዊ መመዘኛ አልሸባብ ኢትዮጵያን ለመበቀል ኢትዮጵያ ውስጥ የጣለው የጎላ አደጋ ባይኖርም፤ የተለያዩ ሙከራዎችን በተለያየ መንገድ ማክሸፉን የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያየ መንገድ ዐስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት አክሽፌያቸዋለሁ ካላቸው የጥቃት ሙከራዎች የቅርቡ እና ከፍተኛ የሚመስለው ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ነው። መግለጫው የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት አድርገው ነበር የተባሉ በርካታ የአልሸባብ እና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይገልጣል። በቁጥጥር ስር ዋሉ የተባሉት ግለሰቦች ተያዙ የተባሉትም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና በጎረቤት ሃገራት ጭምርም ነው። ጥቃት ሊያደርሱ ነበር ከተባሉት ሰዎች መካከል በሀገር ውስጥ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባልም ይገኝበታል ተብሏል።
ይህ አይነቱ የጥቃት ሙከራ ለኢትዮጵያ ሠላምና ደኅንነት ምን ያኽል ያሰጋል የኢትዮጵያ መንግሥትስ አደጋውን ለመከላከል ምን ያህል ዝግጁ ነው?
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ