1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሬደዋ አስተዳደር የጠራው የድጋፍ ሰልፍ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2016

አንድ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ስምምነቱ "ኢትዮጵያ ላይ አዲስ ነገር የሚቀሰቅስ ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ሀገራት መካከል የነበረውን እየተሻሻለ የመጣውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ቀደመው ሊመልስ የሚችል እና ቀጠናዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል ነው ብለዋል"

https://p.dw.com/p/4aoEz
Äthiopien Dire Dawa | Unterstützung für memorandum of understanding mit Somaliland
ምስል Mesay Tekelu/DW

የድጋፍ ሰልፍ በድሬዳዋ

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ያስችላታል የተባለውን ስምምነት ከሶማሌላንድ ጋር ትናንት መፈራረሟን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እና ስሜቶች በመንፀባረቅ ላይ ናቸው።

መረጃውን ተከትሎ የድሬደዋ አስተዳደር የጠራው የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ ጠዋት ሲካሄድ የሰልፉ ታዳሚዎች የመኪና ጡሩምባ በማሰማት ጭምር ደስታቸውን ገልፀዋል ። 

በድጋፍ ሰልፉ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የከተማይቱ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቢኒያም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘቷ ዜና ደስ የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል አቋም በተንታኞች ዕይታ

በሌላ በኩል ስምምነቱን በተመለከተ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የፖልቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ  ሱራፌል ጌታሁን "ኢትዮጵያ ወደብ አገኘች ተብሎ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ የቀረበበት ሁኔታ አግባብ አይደለም" ብለዋል።

ስምምነቱ "ኢትዮጵያ ላይ አዲስ ነገር የሚቀሰቅስ ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ሀገራት መካከል የነበረውን እየተሻሻለ የመጣውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ቀደመው ሊመልስ የሚችል እና ቀጠናዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል ነው ብለዋል" በአስተያየታቸው።

ሀገሪቱ አሁን ካሉባት የውስጥ እና የውጭ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር ወደብ የማልማት ቁመና አላት ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "በዛ ቁመና ላይ የምንገኝበት አይደለም" ብለዋል።

በኢትዮጵያ እና ሶማሌ ላንድ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ ትናንት አምሻሽ በሀረር ከተማ የድጋፍ ትዕይንት መከናወኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነትን በመደገፍ በድሬዳዋ የተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነትን በመደገፍ በድሬዳዋ የተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ምስል Mesay Tekelu/DW

ስለ ስምምነቱ የባለሞያ አስተያየት

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር የባህር በር እንዲሁም የጦር ሰፈር እንዲኖራት ያስችላል የተባለው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ዝርዝር ጉዳዮች ባይገለጡም ለረዥም አመታት ቀጠናዊም ሆነ አህጉራዊ እውቅና ተነፍጓት ለቆየችው ሶማሌ ላንድ ኢትዮጵያ እውቅና እንደምትሰጥ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው። የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄና የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ አቋም

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና  አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪው ሱራፌል ጌታሁን በተባለው መልኩ ኢትዮጵያ በስምምነቱ ለሀገሪቱ እውቅና የምትሰጥ ከሆነ "ለአካባቢው ቀጠና ከባድ ሌላ አዲስ ውጥረት የሚያነግስና የሚያሰፍን " ሆኖ እንደሚታያቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነትን በመደገፍ በድሬዳዋ የተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነትን በመደገፍ በድሬዳዋ የተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ምስል Mesay Tekelu/DW

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ኢትዮጵያ ለሶማሌ ላንድ እውቅና ሰጠች ማለት ሌላ "የዲፕሎማቲክ ሪፍት" በአካባቢው ላይ እንዲኖር ያደርጋል። ይሄ ደግሞ ለሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ለምን ኢትዮጵያ እውቅና ሰጠች በሚል ከፍተኛ ዘመቻ የሚጀምሩበት እና ኢትዮያን ለጥቃት የሚያጋልጣት ሊሆን እንደሚችል ምክንያታቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትና የወደብ ጥያቄ"ላለፉት ሰላሳ ያህል አመታት እውቅና ተነፍጓት ለቆየችው ሀገር ከሌሎች ተነጥሎ እውቅና መስጠት ዲፕሎማቲክ ቁርሾ ውስጥ የሚከት ስለሆነ በመንግስት በኩል በደምብ መጤን አለበት" ያሉት መምህር ሱራፌል ምክንያቱ ደግሞ የስምምነቱ አካሄድ "ከሰጥቶ መቀበል መርህ ያፈነገጠ እና ዊን ዊን አፕሮች ከሚባለው የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እና የዲፕሎማቲክ ስኬት ይሄኛው መዘዙ የከፋ መሆኑን" ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነትን በመደገፍ በድሬዳዋ የተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነትን በመደገፍ በድሬዳዋ የተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ምስል Mesay Tekelu/DW

መምህር እና ተመራማሪው ሱራፌል በኢትዮጵያ መንግስት እና ሶማሌላንድ አሁን ተደረሰ የተባለው  ስምምነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ስኬት መንገድ ማሳያ ነው የሚለውን የብዙዎች ሀሳብ  አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ስኬት ነው ብዬ የምተረጉምበት ምክንያት የለም ምክንያቱም የሚያመጣው መዘዝም ከፍተኛ ስለሆነ ብለዋል።

ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት መምህር ሱራፌል  "ኢትዮጵያ ወደብ አገኘች" ተብሎ በአንዳንድ ሚዲያ ለህብረተሰቡ መረጃው የቀረበበት መንገድም አግባብ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።

መሳይ ተክሉ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር