1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ስንት ታገኝ ይሆን?

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2011

ከሦስት አመታት በኋላ ኢትዮጵያ ከካሉብ እና ሒላላ የተፈጥሮ ጋዝ ሽያጭ በአመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ልታገኝ አቅዳለች። ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተፈረመው ስምምነት መሠረት ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ በ3.2 ቢሊዮን ዶላር የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ እና ማቀነባበሪያ ይገነባል። ግንባታው በሶስት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል።

https://p.dw.com/p/3DkbV
Äthiopien Abkommen zum Bau einer Pipeline | Yonis Ali Guedi und Samuel Horka
ምስል Ethiopian Ministry of mines and petroleum

የማስተላለፊያና ማቀነባበሪያ ግንባታው 3.2 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል

ከአዲስ አበባ በ1,200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኦጋዴን ሸለቆ ኢትዮጵያ ተስፋ የጣለችበት የተፈጥሮ ጋዝ መገኛ ነው። 350,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሰፋው ኦጋዴን ካሉብ እና ሒላላ በተባሉ ሁለት ቦታዎች ከስምንት እስከ አስር ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የሚደርስ የተፈጥሮ ጋዝ እንደሚገኝ ይገመታል።  የኢትዮጵያ የማዕድን እና የነዳጅ ሚኒስቴር ምኒስትር ድዔታ ዶክተር ኩአንግ ቱትላም «ቀደም ብሎ የተገኘው ክምችት 4.7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ነበር። ፖሊ-ጂሲኤል የተባለው ኩባንያ ባደረገው ፍለጋ መጠኑን ከ8 እስከ 10 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ አድርሶታል» ሲሉ ስለ ክምችቱ ተናግረዋል። 

የ40 አመታት ፍለጋ
ላለፉት አርባ ገደማ አመታት የተለያዩ ኩባንያዎች በኦጋዴን ሸለቆ የተፈጥሮ ነዳጅ ፍለጋ ሲያካሒዱ ቆይተዋል። በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ1955 እስከ 1991 ባሉት አመታት 46 ጉድጓዶች ተቆፍረው በርካታ የሐይድሮካርቦን ምልክቶች እና በካሉብ እና ሒላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቶች ተገኝተዋል። 

የካሉብ እና ሒላላ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቶች የተገኙት በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1973 እና በ1974 ዓ.ም. ቴኔኮ በተባለ ኩባንያ አማካኝነት ነበር። ከ1986 እስከ 1991 ባሉት አመታት የሶቭየት ነዳጅ ፍለጋ ኩባንያ (The Soviet Petroleum Exploration Expedition) በካሉብ ዘጠኝ በሒላላ ደግሞ ሦስት ጉድጓዶች ቆፍሯል። የሩሲያ፣ የዮርዳኖስ፣ የቻይና እና የማሌዥያ ኩባንያዎችም ከፍ ያለ ወጪ አውጥተው በካሉብ እና በሒላላ ዕድላቸውን ሞክረዋል። የተሳካለት ግን ከስድስት አመታት በፊት የፍለጋ ሥራውን ከመንግሥት ጋር በተፈራረመው ስምምነት አንድ ብሎ የጀመረው ፖሊ-ጂሲኤል የተባለ የቻይና ኩባንያ ነው።  

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ላይ በፈረሙት ስምምነት መሠረት ከካሉብ እና ከሒላላ ተነስቶ እስከ ጅቡቲ የ767 ኪሎ ሜትር የተፈጥሮ ማጓጓዣ ይገነባል። ከማስተላለፊያው በተጨማሪ ከካሉብ እና ሒላላ የተጓጓዘው የተፈጥሮ ጋዝ በ-162 ዲግሪ ሴንቲግሬድ (-260° ፋራንሀይት) ቀዝቅዞ ለጭነት የሚዘጋጅበት ማቀነባበሪያ ጅቡቲ ዉስጥ ይገነባል። ዶክተር ኩአንግ ቱትላም ለDW እንደተናገሩት ሥራው 3.2 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል። 

ዶክተር ኩአንግ «ቧምቧው ጅቡቲ ወደብ ከደረሰ በኋላ ጋዙ ተቀነባብሮ ይቀዘቅዛል፤ ከዚያ ደግሞ ታምቆ ወደሚሸጥበት አገር ይላካል ማለት ነው። ስለዚህ ማቀነባበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ ይገነባል ማለት ነው። የተፈጥሮ ጋዝ ከተገኘበት ቦታ የሚሰራ ስራ አለ። ከዚያ ደግሞ ቧምቧ የሚዘረጋበት እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (Liquefied natural gas) ማቀነባበሪያ የሚገነባበትን ጨምሮ አጠቃላይ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል» ሲሉ ተናግረዋል። 

Karte Region rotes Meer DE
ምስል DW

የኢትዮጵያ የማዕድን እና ነዳጅ ሚንስትር ዶክተር ሣሙኤል ኡርቃቶ ሥምምነቱን «ሰፊ ድርድር የተካሔደበት እና የሁለቱን አገሮች የጋራ ጥቅም የሚያስከብር» ብለውታል።  ምኒስትሩ ሥምምነቱን ከፈረሙ በኋላ ይኸው ዕቅድ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ የኢትዮጵያ የግል ኩባንያዎችንም ያሳትፋል የሚል ዕምነታቸውን ገልጸዋል። ምኒስትሩ 
«ይኸ በሁለት መንግሥታት መካከል የተፈረመ ሰነድ ከካሉብ እና ሒላላ እስከ ጅቡቲ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ለመገንባት ዕድል ይሰጠናል። በዚህ ሒደት ኢትዮጵያ፤ ጅቡቲ እና ግንባታውን የሚያካሒደው ኩባንያ ተጠቃሚ ይሆናሉ። በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይችላል። የአገር ውስጥ ኩባንያዎቻችን በግንባታ እና ግብዓቶች በማቅረብ ተሳታፊ ይሆናሉ» ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል። በጅቡቲ የኢነርጂ እና የተፈጥሮ ሐብት ሚኒስትር ዮኒስ አሊ ጎይዲ በበኩላቸው ይኸንኑ ሥምምነት «የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር እና የጋራ ጥቅም የሚያስገኝ» ሲሉ ገልጸውታል። ዮኒስ አሊ ጎይዲ አዲስ አበባ ላይ ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ «በስተመጨረሻ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ለመገንባት ከስምምነት በመድረሳቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። ይኸ የሁለትዮሽ ስምምነት ዛሬ እንዲፈረም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን  የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌሕ እና የኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ምኒስትር እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ። ይህ ሥራ ለሁለቱ አገሮች ዕድገት ቁልፍ ሚና አለው። ይኸ ዕቅድ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ያደርጋል። ይኸ የተፈጥሮ ጋዝ ሥራ እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሎ ይገመታል» ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ስንት ታገኛለች? 

የኢትዮጵያ የማዕድን እና የነዳጅ ሚኒስቴር ምኒስትር ድዔታው ዶክተር ኩአንግ ቱትላም እንደሚሉት ከሦስት አመት በኋላ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ የመላክ ሥራው አንድ ተብሎ ይጀመራል። በመጀመሪያዎቹ አመታት ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ጋዝ ልማት ሥራው ባላት ድርሻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ታገኛለች። ወደ ውጪ የሚላከው የተፈጥሮ ጋዝ መጠን ሲጨምር የአገሪቱ ገቢም ከፍ ይላል። ዮኒስ ዶክተር ኩአንግ «በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ውስጥ ኢትዮጵያ 15 በመቶ ነፃ ድርሻ አላት። ግን ኢትዮጵያ የምታገኘው ይከ ብቻ አይደለም። ከአጠቃላይ ሽያጩ እስከ 8 በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ ታገኛለች፤ ከዚያም ደግሞ ታክስ ታስከፍላለች፤ የመሬት ግብር ታገኛለች፤ ሌሎችም በተጓዳኝ የምታገኛቸው ክፍያዎች አሉ። የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጪ መላክ ሲጀመር በአመት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር፤ የጋዙ መጠን ደግሞ እየጨመረ ሲሔድ በስድስት ሰባት አመት እስከ ስድስት ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ታገኛለች ማለት ነው» ብለዋል። 

Deutschland Ostsee-Erdgaspipeline Nord Stream in Lubmin
ምስል picture-alliance/dpa/S. Sauer

ከካሉብ እና ሒላላ የኢትዮጵያ መንግሥት በ2017 ፖሊ-ጂሲኤል ደግሞ በኋላ በ2018 ዓ.ም. የተፈጥሮ ጋዝ ይመረታል የሚል ውጥን ነበራቸው። በሁለቱም ወገን የተያዘው ዕቅድ ግን በተያዘለት ጊዜ አልተሳካም። ፖሊ-ጂሲኤል የተፈጥሮ ጋዝ ልማቱን ለማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ከጅቡቲ ጋር ከተፈራረመ እንኳ አንድ አመት ገደማ አልፎታል። ስምምነቱ ሲፈረም በስድስት ወራት ውስጥ ድርድር ይጠናቀቃል የሚል ዕቅድ ተይዞ ነበር። ፖሊ-ጂሲኤል የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው ቻይና ፖሊ ግሩፕ ኮርፖሬሽን እና መቀመቻውን በሖንግ ኮንግ ያደረገው ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ በሽርክና ያቋቋሙት ኩባንያ ነው። አሁን አዲስ አበባ ላይ በተፈረመው ስምምነት መሰረት ፖሊ-ጂሲኤል በአመት 12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ማጓጓዣ ይገነባል። 

በጅቡቲ የሚገነባው ማቀነባበሪያ 10 ሚሊዮን ቶን የተፈጥሮ ጋዝ በአመት የማዘጋጀት አቅም ይኖረዋል። ዶክተር ኩአንግ «ገንዘቡን የሚያቀርበው ፖሊ-ጂሲኤል የተባለው የቻይና ኩባንያ ነው። ግንባታን በተመለከተ የዝግጅት ምዕራፉ እዚህ ከደረሰ ሌሎች በተጓዳኝ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ። እነሱ ካለቁ በኋላ ጨረታ ይወጣል ማለት ነው። የሚገነባው ኩባንያ ያን ተመስርቶ ግንባታ ይጀምራል» ሲሉ ለDW አስረድተዋል።  

በሶማሌ ክልል የነበረው የጸጥታ ኹኔታ በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋው ላይ የራሱን ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ቆይቷል። በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብሎ የነበረ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ወደ ሰላማዊ ፖለቲካ መመለስ ለተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋውም ሆነ አሁን ይጀመራሉ ለተባሉት የግንባታ ሥራዎች ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ