ኢትዮጵያ የ2 ዓመት ለዉጥ፣ የሶማሌ ክልል ጣጣ
ሰኞ፣ መጋቢት 28 2012ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት የገዛዉ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) መራሹ መንግሥት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ በሚመሩት ከተተካ ባለፈዉ ሳምንት ሁለተኛ ዓመቱን ደፈነ።የኢትዮጵያን ፖለቲካ ባዲስ ሐዲድ ለመዘወር ባለፉት ሁለት ዓመታት የተደረጉት ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ ለዉጦች ብዙ ጥያቄ ቢያስነሱም አብዛኛዉን ሕዝብ ያረኩ፣የሩቅም ቢሆን በጎ ተስፋ የፈነጠቁ ናቸዉ።የዚያኑ ያሕል ከለዉጡ ማግስት ጀምሮ በየአካባቢዉ የፈነዳዉ ግጭት የብዙ ሺሕ ዜጎችን ሕይወትና አካል አጥፍቷል። ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል።ብዙ ሚሊዮኖችን ዛሬም ድረስ እንዳሰጋ ነዉ።የሕወሓት ፖለቲከኞች እንዳኮረፉ ነዉ።የለዉጡ መሪዎች የነበሩት የኦሮሞ ፖለቲከኞች መከፋፈላቸዉ፣ የአማራ መሪዎች መገዳደላቸዉ፣ የህግና-ሥርዓት መድከም ሥጋቱን ወደ ፍርሐት እንሮ ተስፋዉን በጭንቀት ለዉጦታል።ኮሮና ታከለበት።የለዉጡ ሁለተኛ ዓመት በሚዘከርበት ዕለት ከወደ ጂጂጋ የሰማነዉ ደግሞ ለዉጥ አራማጆች ገና በሁለተኛ ዓመታቸዉ አንድ ለመሆን አዲስ የጋራ ጠላት የሚሹ አስመስሏቸዋል።የለዉጡ ሁለተኛ ዓመት መነሻ፣ የሶማሌ ክልል ፖለቲካዊ ቀዉስ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሥልጣን የያዙበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባለፈዉ ሐሙስ ባስተላለፉት መልዕክት ከመንግሥታቸዉ የሁለት ዓመት ገድል-ድል በአንደኝነት የጠቀሱት በሶማሌ መስተዳድር የወሰዱትን እርምጃ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ «አስካፍንጫዉ የታጠቀ» ያሉት የቀድሞዉ ሶማሌ መስተዳድር ልዩ ፖሊስ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት «እስካፍንጫዉ» መታጠቅ አለመታጠቁ በርግጥ ያነጋግራል።
ይሁንና ያ ታጣቂ ሐይል የሚደርሰዉን ግፍ አስቁሞ የበላይ-ኃላፊና አዛዦቹንን ወሕኒ የመዶሉ ትግል ትዕግሥት፣ብልሐትና መስዋዕትነት የጠየቀ እንደነበር አያጠያይቅም።የቀድሞዉ የሶማሌ ክልል ርዕሠ-መስተዳድር አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)ና ባለስልጣኖቻቸዉ ከስልጣን ከተወገዱ የፊታችን ኃምሌ ማብቂያ ሁለት ዓመት ይደፍናሉ።የፖለቲካ ተንታኝ ሙሳ አደም እንደሚሉት ከአብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳደር በኋላ የክልሉን የመሪነት ሥልጣን የያዙት አዳዲሶቹ ፖለቲከኞች የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የወሰዱት እርምጃ አስደሳች፤ ያደረጉት ጥረትና የገቡት ቃልም ተስፋ ሰጪ ነበር።
ነበር መሆኑ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የሁለተኛ ዓመት ገድል ድላቸዉን ከመግለፃቸዉ ከአንድ ወር ግድም በፊት የጂጂጋ ሕዝብ ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ የመሰረቱትን የብልፅግና ፓርቲን በመደገፍ የአደባባይ ሰልፍ ማድረጉ ተዘግቦ ነበር።የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት አዲሱን ገዢ ፓርቲ፣ በዘጋቢዎቹ አገላለፅ «እዉነተኛ ፌደራሊዝምን ለመተግበር እየሰራ ያለ» በማለት 20ሺሕ ሰልፈኛ አወድሶታል።የፋና ብሮድካስት ዘገባ እንደሚለዉ በሰልፉ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።ሰልፈኛዉን ሕዝብ ከትልቁ አደባባይ ሰገነት ወይም መድረክ ላይ ፊትለፊት ተደርድረዉ ይመለከቱ የነበሩት ባለስልጣናት እርስበርስ የሚሻኮቱ፣አንዱ ሌላዉን ለመጣል የሚያሴሩ፣ ምናልባትም ባሕርዳር ላይ አምና ሰኔ እንደሆነዉ ለመገዳደል የሚደባቡ መሆናቸዉን የዋሑ ሰልፈኛ የሚያቅበት ምንም ፍንጭ አልነበረዉም።የፖለቲካ ተንታኝ ሙሳ አደም እንደሚሉት ግን ለፎቶ ግራፍ አንድ መስለዉ አንድ ላይ የተደረደሩት ፖለቲከኞች ከወራት በፊት ጀምረዉ ሲሻኮቱ ነበር።
በስደት የነበሩ ኢትዮጵያዉያን ፖለቲከኞች ሥለሚሉ ስለሚያደርጉት እንዲዘገብላቸዉ ጋዜጠኞችን ሌት ተቀን ይወተዉታሉ።ቦሌ አለም አቀፍ አዉሮፕላን ከደረሱ በኋላ ግን ከጋዜጠኛ ይሸሻሉ።ለአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ቀረብ ያሉ ከሆኑማ እነሱ ወይም አለቆቻቸዉ በሚቆጣጠሩት መገናኛ ዘዴ ለመወደስ-መሞገስ ካልሆነ በስተቀር ዕዉነትን ወይም ጠጠር ያሉ ጥያቄዎችን ከሚያቀርቡ መገናኛ ዘዴዎች ጨርሶ ይሰወራሉ።
ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ያልሰከነዉን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከ40 ዓመት በላይ ሲያተራምሱ የነበሩ አንዱ ፖለቲከኛ በቅርቡ ለመገናኛ ዘዴ መግለጫ መስጠት አቁሜያለሁ ብለዉ በይፋ ማወጃቸዉን ሰምተናል።መብታቸዉ ነዉ።መብታቸዉ የማይሆነዉ በሕዝብ ስምና ስለ ሕዝብ ብለዉ የሰሩትን መጥፎ-ይሁን በጎ መደብቅ አለመቻላቸዉ ነዉ።አዳዲሶቹ የሶማሌ ክልል ባለስልጣናትም እንዲያ ናቸዉ።በስደት እያሉ መዐልት ወሌት ሲነዘንዙን የነበሩት ፖለቲከኞች አሁን ለፅሁፍ መልዕክታችን እንኳን መልስ ለመስጠት ሸሽተዋል።ወይም ስልጣን የቀሟቸዉ የቀዳሚዎቻቸዉ ትክክለኛ ወራሽ መስለዋል።
የሆነዉ ግን ያዩ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የመንግሥታቸዉን የሁለት ዓመት ገድል ድል በሚዘዘሩበት ዕለት የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ለመጠፋፋት ይዛዛቱ ነበር።በሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሠ-መስተዳድር በአቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና በክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ በአቶ አብዱልአዲል ሐሰን መካከል የተፈጠረዉ ጠብ በጣም ተካርሮ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ፣ ጂጂጋ የሰኔ 15ቷን ባሕርዳር ከመሆን ለጥቂት ነዉ ያመለጠችዉ።የጠቡ ትክክለኛ ምክንያት በርግጥ አለየም።ባለስልጣናቱም ያልነዉን ለመድገም እስካሁን በግልፅ ለመናገር አልፈቀዱም። ሽኩቻዉ ግን ዉስጥ ዉስጡን ሲብላላ ነበር።እንዳገና ሙሳ አደም።
የአማራ መስተዳድር ባለስልጣናትን ያጋደለዉ ጠብ በክልሉ የበላይ አስተዳዳሪዎችና በፀጥታ ዘርፍ ሹማምንት መካከል የነበረዉ ልዩነት ነበር።የሶማሌ ባለስልጣናት ልዩነትም የአሰራር፣የአስዳደር፣የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጃት፣ የርዕዮተ ዓለም ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፤ ጠቡ ግን ልክ እንደ አማራ ክልል ምክትል ርዕሠ-መስተዳድሩ እና የፀጥታ ኃላፊዉ በሚመሯቸዉ ቡድናት መካከል መሆኑ እርግጥ ነዉ።
እስካሁን ባለን መረጃ መሰረት ባለፈዉ ሐሙስ ጠቡ ከመፍረጥረጡ በፊት ሥልጣን የለቀቁት የምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ አቶ መሐመድ ዑሉድ በጠቡ ሰበብ ተከሰዉ ለፖሊስ ቃላቸዉን ሰጥተዋል።የምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ የፕሮቶኮል ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ቢስሌ ታስረዋል።የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት አቶ አብዱልአድል ሐሰንን እንዲያስር ባለፈዉ ሐሙስ ወደ ቤታቸዉ የተላከዉ ኃይል፣ ተፈላጊዉን ከሚጠብቁት ታጣቂዎች ጋር ለግጭት ሲጋበዝ አምሽቶ ለማፈግፈግ ተገድዷል።ኃላፊዉ ግን ከስልጣን ተወግደዉ በቁም እስረኝነት እየተጠበቁ ነዉ።
የአማራ ባለስልጣናት እርስበርስ የተገዳደሉት፣ ለዉጥ አራማጅ የሚባሉት የኦሮሞ ፖለቲከኞች መቃቃራቸዉ የተሰማዉ ከቅማት-እስከ ባሌ፣ ከሞያሌ እስከ ደምቢዶሎ አብዛኛዉ አካባቢ በጎሳ፣በኃይማኖትና በፖለቲካ ቀዉስ በሚታመስበት ወቅት ነዉ።የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግጭት፣ግድያ ምስቅልቅሉ ሳያገግም፣ አንደ አብዛኛዉ ዓለም የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ስጋቶቹን ሁሉ በልጦ በሚያስጨንቀዉ መሐል አሁን፣ የጂጂጋዉ ሽኩቻና ጠብ መሰማቱ የማይታየዉን ጠላት ለመዋጋት መደረግ የሚገባዉን የጋራ ጥረት ክፉኛ መሸርሸሩ አያጠያይቅም።
ጅጅጋ ባለፈዉ ሐሙስ የሰኔ 15ቷን ባሕርዳርን በርግጥ አልሆነችም።አለመሆኗ ለሰላም ወዳዶች ሁሉ አስደሳች ነዉ። አንዳቸዉ ባንዳቸዉ ላይ እያሴሩ፣ ሕዝብን ባደባባይ ለድጋፍ የሚያሰልፉ፣ የዓመት ከመንፈቅ በጎ ዉጤታቸዉን እየተናገሩ እርስበርስ የሚሻኮቱ ፖለቲከኞች ሐሙስ ያለፉትን ሌላ ጊዜ ላለመድገማቸዉ ዋስትና አለመኖሩ ግን በርግጥ ሊያስቆዝም ይገባል።የፖለቲካ ተንታኝ ሙሳ አደም ይመክራሉ።ካለፈዉ ተማሩ-እያሉ።
ዶክተር ዐብይ ባለፈዉ ሐሙስ ባስተላለፉት መልዕክት «ሞት በሕይወት ይሸነፋል» ብለዋል።ድፍን ዓለም ከዚሕ የተለየ ምኞች በርግጥ ሊኖረዉ አይችልም።በስንት ሞት ስንት ሕይወት ያሸንፋል እንጂ-ጥያቄዉ።ደግሞም ሰሜኖች አኩርፈዉ፣ ሰሜን ምዕራቦች እየተሽመደመዱ ማሐሎች ተቃቅረዉ፣ ምስራቆች እየተሻኮቱ፣ አስገባሪዎችን ካስገበረዉ ከማይታይ መቅሰፍት መቶ ሚሊዮኖችን መከላከል እንዴትና መቼ ይቻል ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ