1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር የዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ዕቅድ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 7 2013

ኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ለማድረግ በድርድር ላይ እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።ይኸ ለኢትዮጵያ እስከ ስድስት አመታት የመክፈያ ጊዜ እፎይታ ይሰጣል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም ጠይቋል።ኢትዮጵያ ለ2014 ዓ.ም 31. 8 ቢሊዮን ብር ለውጭ ዕዳ ክፍያ አዘጋጅታለች

https://p.dw.com/p/3wUAN
Äthiopien | Straßenszene in Addis Abeba
ምስል Eshete Bekele/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ዕቅድ

ኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ለማድረግ በድርድር ላይ እንደምትገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታውቋል። ሪፖርቱ እንደሚለው ይኸ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ እስከ ስድስት አመታት የሚደርስ የመክፈያ ጊዜ እፎይታ ይሰጣታል። የወለድ የመክፈያ ጊዜውንም ወደ አስር አመታት ያራዝማል።

ከዚህ በተጨማሪ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል ኢትዮጵያ ካለባት ዕዳ 125 ሚሊዮን ዶላር የአከፋፈል ማስተካከያ ለማድረግ በሒደት ላይ መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል። በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓ.ም. ከግንቦት እስከ ታኅሳስ ባሉት ወራት ኢትዮጵያ መክፈል ለነበረባት ዕዳ ማስተካከያ ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ከፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ተፈራርማለች። ለዚህም ከአበዳሪ አገሮች ጋር በተናጠል ድርድር እየተካሔደ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ በአፋጣኝ እንዲቋቋም ጠይቋል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጌሪ ራይስ ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ (Common Framework) ተጠቃሚ ለመሆን ባለፈው የካቲት ለቡድን 20 አገራት እና የፓሪስ ክለብ አበዳሪዎች ጥያቄ ማቅረቧን አስታውሰዋል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አገሪቱ የመክፈል ግዴታ ያለባት ዕዳ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ለልማት ወጪዎች የበጀት ቦታ መፍጠር እና የብድር ጫና ሥጋት ምዘናን ወደ መካከለኛ የመቀነስ ዓላማ እንዳላቸው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ አስታውቀዋል። ቃል አቀባዩ ጌሪ ራይስ እንዳሉት "የኮሚቴው መዋቀር በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን ያግዛል።"

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት (Extended Fund Facility) በተባሉ ማዕቀፎች በኩል ለኢትዮጵያ 2.1 ቢሊዮን ዶላር በታኅሳስ 2012 ዓ.ም. አጽድቋል። ይኸ የገንዘብ መጠን ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ቃል ከገባው 2.9 ቢሊዮን ዶላር 70 ከመቶ ገደማ መሆኑ ነው።  አይኤችኤስ ማርኪት (IHS Markit) በተባለው የመረጃ እና ትንተና ተቋም ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አሊሳ ስትሮበል "ሥምምነቱ መደበኛ ግምገማዎችን ያካተተ ሲሆን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የብድር ዘላቂነት ትንተና ጋር የተያያዘ ነው" በማለት ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ መሠረት መክፈል ያለባትን ዕዳ ለማስተካከል እና የዕዳ ጫናዋን ለመቀነስ ያሳለፈችውን ውሳኔ በይኹንታ መቀበሉን የሚያስታውሱት የምጣኔ ሐብት ባለሙያዋ "ነገር ግን ውሳኔው ይፋ ከሆነ በኋላ በየካቲት መጀመሪያ ገደማ ከወጡ ጥቂት የመንግሥት መግለጫዎች በቀር መንግሥት የዕዳ አከፋፈሉን ለማስተካከል የያዘውን ዕቅድ በማቅረብ ረገድ ዝምታን መርጧል። አንዳንዶች በቡድን 20 ማዕቀፍ መሠረት የዕዳ አከፋፈልን እንደገና ማዋቀር ኢትዮጵያ ከግሉ ዘርፍ የተበደረችው ገንዘብ ወለድ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋት ይመለከታሉ። በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሠረት የዕዳ አከፋፈልን ማዋቀር የተጠያቂነት አስተዳደርን (liability management) በማስፈን ለረዥም ጊዜ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ገበያ ገንዘብ ማግኘት ይቻላል ብሎ መጠበቅ ይችላል። ነገር ግን በእንደዚህ አይነት የዕዳ ማስተካከያ የግል አበዳሪዎች እንዴት ይስናገዳሉ የሚለውን የሚመልስ ተጨባጭ መግለጫ የለም።" ሲሉ ተናግረዋል።

IWF Report Logo
ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ በአፋጣኝ እንዲቋቋም ጠይቋል።ምስል Yuri Gripas/REUTERS

የኢትዮጵያ አብዛኛው የውጭ ዕዳ ከዘርፈ-ብዙ (መልቲ ላተራል) እና የሁለትዮሽ (ባይላተራል) ምንጮች የተበደረችው ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንዲዋቀር የጠቆመው ኮሚቴ ኢትዮጵያ እና አበዳሪዎቿን በማገናኘት መረጃ እንዲለዋወጡ ሥርዓት ያበጃል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ይኸው ኮሚቴ አበዳሪ እና ተበዳሪ በስምምነት የሚያዘጋጁት የብድር አከፋፈል ሥርዓት እንዲዘረጋ እና መተማመን እንዲፈጠርም ያግዛል።

አሊሳ ስትሮበል "የኮሚቴው መቋቋም የምዘና ተቋማት የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዲገመግሙ ይረዳቸዋል። ይኸ በመጨረሻ በዕድገት ረገድ ከፍተኛ ቅነሳ ያሳያል ተብሎ የሚጠበቀውን ኤኮኖሚ መልሶ ለማነቃቃት፤ የውጪ ፋይናንስ የምትፈልገው የኢትዮጵያን በጀት ለመደገፍ እና ለሰብዓዊ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ጠቃሚ ነው። ስለዚህ ይኸ ሒደት ይፋጠናል ብዬ እጠብቃለሁ" ብለዋል።

የኮሚቴው አባላት ማንነት የሚወሰነው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች እነ ማናቸው በሚለው ይሆናል። የገንዘብ ምኒስትር ድኤታው እዮብ ተካልኝ ለብሎምበርግ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ የብድር አከፋፈል ማስተካከያ ከሶስት አመታት በኋላ ወለድ የሚከፈለበትን የአንድ ቢሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ አይመለከትም። አሊሳ ስትሮበል ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውሳኔዋን ይፋ ካደረገች በኋላ የሒደቱ ዘገምተኝነት በኢትዮጵያ አበዳሪዎች እና የምዘና ተቋማት ዘንድ በዝምታ አልታለፈም።

"በየካቲት መጀመሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣን በዕዳ አከፋፈል ማስተካከያው የግል አበዳሪዎች የሚካተቱበት ዕድል አነስተኛ እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል።  ይሁንና ኢትዮጵያ የብድር አከፋፈሏን እንደገና ለማዋቀር መዘጋጀቷን በየካቲት ይፋ ካደረገች በኋላ ሒደቱ ዘገምተኛ መሆኑ በግል አበዳሪዎች እና የምዘና ተቋማት ዘንድ ሥጋት የፈጠረ ሲሆን በዚህ ምክንያት በግንቦት ወር የኢትዮጵያ ምዘና ዝቅ ብሏል" ይላሉ አሊሳ ስትሮበል

Infografik Ratingagenturen Startbild DEU
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካ፣ የኤኮኖሚውን እንቅስቃሴ እና የአገሪቱን የመክፈል አቅም እየተከታተሉ በመገምገም ለአገሪቱ የዕዳ ምዘና ደረጃ የሚያወጡ እንደ ሞዲ እና ፊች የመሳሰሉ ተቋማት ከሚሰማቸው ሥጋት አንዱ የቻይና ብድር መጠን በግልጽ አለመታወቅ እንደሆነ የኤኮኖሚ ባለሙያዋ አሊሳ ስትሮበል ያስረዳሉ።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዋ "ተጨማሪ እርግጠኝነት ማጣት እና ጉዳዩን ወደ አንዳች አቅጣጫ የሚመራ የአበዳሪዎች ኮሚቴ አለመቋቋም የግል አበዳሪዎች በጉዳዩ ላይ ባላቸው ዝቅተኛ ስሜት ላይ የሚታከል ይሆናል። ይኸ ብዙውን ጊዜ የዩሮ ቦንድ ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል። በግንቦት ወር አንድ የምዘና ተቋም የኢትዮጵያን ደረጃ ዝቅ ማድረጉን ይፋ ሲያደርግ በሶስት አመታት ውስጥ ወለድ የሚከፈልበት የኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ዋጋ ሲቀንስ ተመልክተናል። የኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ወለድ በ18 ነጥቦች የቀነሰ ሲሆን፤ ይኸ ኢትዮጵያ የብድር አከፋፈሏን እንደገና ለማዋቀር መወሰኗን በየካቲት ካሳወቀች ወዲህ ከፍተኛው ነው።  ስለዚህ ጉዳዩ ረዘም ያለ ጊዜ መውሰዱ፤ ሥጋት ላለባቸው የግሉ ዘርፍ አበዳሪዎች፤ ውጤቱ ምን ይሆናል በሚለው ረገድ በአንፃራዊነት ውስብስብ ውሳኔ እንደሚኖር ይጠቁማል" ብለዋል።

የቡድን 20 አገራት የዕዳ ማስተካከያ ማዕቀፍ በዋናነት የሚመለከተው የመንግሥት ብድሮችን ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም የፋይናንስ ገበያ እና ከምዕራባውያን አገሮች ከተበደረችው ገንዘብ በተጨማሪ ምን ያክል የቻይና ዕዳ አለባት? የሚለው ጉዳይ በግልጽ አለመታወቁ ለሒደቱ ፈተና ከሚጋርጡ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል። ለደሐ አገሮች የዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ የተበጀው የቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ ቢያንስ አሁን የቻይና ብድሮችን አይጨምርም። ከመንገድ እስከ ባቡር፤ ከእግር ኳስ ሜዳ እስከ ስኳር ፋብሪካ ለግንባታ ከቻይና ከፍ ያለ ገንዘብ ለተበደረችው ኢትዮጵያ አጠቃላይ የዕዳ አከፋፈል ማስተካከያ ለመስራት ከወደ ቤጂንግ ይሁንታ ምግኘት እንደሚያሻት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካ፣ የኤኮኖሚውን እንቅስቃሴ እና የአገሪቱን የመክፈል አቅም እየተከታተሉ በመገምገም ለአገሪቱ የዕዳ ምዘና ደረጃ የሚያወጡ እንደ ሞዲ እና ፊች የመሳሰሉ ተቋማት ከሚሰማቸው ሥጋት አንዱ ይኸው የቻይና ብድር መጠን እንደሆነ አሊሳ ያስረዳሉ።

አሊሳ ስትሮበል "ከምዘና ተቋማት ጋር ስትነጋገር ብዙ ጊዜ የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያ ምን ያክል የቻይና ብድር እንዳለባት የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ ነው። በዚህ ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ ምክንያት ይኸ ውይይት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ በጉዳዩ ላይ ጫና ማሳደሩን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዋ ጠቅሰዋል። "በትግራይ ጦርነት የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል" የሚሉ ሪፖርቶች ከቀረቡ በኋላ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ ሊሰጡ የመደቡትን ዕገዛ እንዲያቆሙ መጠየቋን በአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ምኒስትሩ ሮበርት ጎዴክ ተናግረዋል። እርምጃው ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ሊሰጡ ያቀዱትን ገንዘብ እንዲያቆሙ የሚያደርግ ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ስምምነት ከተፈራረመ 18 ወራት አልፈዋል።

የትግራይ ጦርነት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ካሳደረው ጫና ባሻገር በአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይም የከፋ ዳፋ አስከትሏል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ መውጣቱ እንደተገለጸ መንግሥታቸው ከወታደራዊ ወጪዎች ውጪ "ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ትግራይ ውስጥ" ማውጣቱን ተናግረዋል።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed Parlament
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2014 ዓ.ም. በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ዕለት እንዳሉት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት 37 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ባለፉት ሶስት አመታት ወደ 26 በመቶ ዝቅ ብሏል።ምስል Yohannes Gebireegziabher/DW

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አገሪቱ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አኳያ ያለው ምጣኔ መቀነሱን እየጠቀሱ የተሰሩ ማሻሻያዎች ውጤት ማምጣታቸውን ያስረዳሉ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ2014 ዓ.ም. በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ዕለት እንዳሉት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት 37 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ባለፉት ሶስት አመታት ወደ 26 በመቶ ዝቅ ብሏል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ዕዳው ከሚከፈልበት ጊዜ አንፃር ሲሰላ በብዙ የመቀነስ አዝማሚያ አለው። የዕዳ አከፋፈልን ለማስተካከል ከወዳጅ አገራት ጋር የተሠሩ ሥራዎች አሉ። ባለፉት ሶስት አመታት ኮሜርሺያል ብድር አንድም ዶላር ቢሆን አቁመናል። ዋናው የኢትዮጵያን ዕዳ ያገዘፈው ኮሜርሺያል ብድር ነው። እሱን ሙሉ በሙሉ ማቆም ተችሏል" በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2014 የበጀት አመት 45 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ ያዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 31. 8 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው ለውጭ ዕዳ ክፍያ የታቀደ ነው። ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት የጸደቀው የኢትዮጵያ መንግሥት የ2014 ዓ.ም. በጀት እንደሚያሳየው ለውጪ አበዳሪዎች ከሚከፈለው 31. 8 ቢሊዮን ብር 18.9 ቢሊዮን ብር ገደማ ለዋና የዕዳ ክፍያ፤ 12.8 ቢሊዮን ብር ገደማ ደግሞ ለወለድ ክፍያ ተመድቧል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ