ኢትዮጵያ «ያለመረጋጋት ምንጮችን ማድረቅ በሚቻልበት ሂደት ቁልፍ ሚና ትጫወታለች »
ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሚኖራት ሚና
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢው ከቀጣናው ተሻጋሪ የሆኑ የሰላም መደፍረስ እና አለመረጋጋት ምንጮችን ማድረቅ በሚቻልበት ሂደት ቁልፍ ሚና መወጣት ላይ እንደምታተኩር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ በማያባራ መልኩ መግለጫዎችን፣ ዛቻዎችን እና ማስፈራሪያዎች እያስተጋባች መሆኑን ገልፀው በኢትዮጵያ በኩል ግን ውጥረቶችን የማለዘብ እና የማርገብ ሂደት ስለመመረጡ ጠቅሰዋል።
ቃል ዐቀባዩ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ የተናገሩትን፣ ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የብሪክስ ስብስብ በአሜሪካ ዶላር ላይ ስለያዘው ውጥን ያስተላለፉትን ማስጠንቀቂያ በሚመለከት የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም ቢጠየቁም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ኢትዮጵያ አከባቢያዊ ውጥረቱን ለማርገብ የያዘችው የቀጣይ እቅድ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢው ያለውን "ውጥረት" ለማርገብ በኃላፊነት ስሜት ላይ ያተኮረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስታካሂድ መቆየቷን የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ከሶማሊያ የሚቃጡ አባባሽ መግለጫዎችን የማለዘብ እና የማርገብ ሂደት ስትከተል መቆየቷን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ጋር የተካረረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ውስጥ የገባቸው ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የፈረመችውን የባሕር በር የሚያስገኝላት የመግባቢያ ስምምነት አሁንም ውድቅ እንድታደርገው በመጠየቅ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ወቅታዊ ግንኙነት "ሰላማዊ" ነው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ይህ የማይሆን ከሆነ ሶማሊያ ውስጥ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ የጦር ሠራዊት በዚያ እንደማይቀጥል እና ቦታ እንደማይኖረው፣ ቀጣይ በሀገሪቱ በሚሰማራው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ጥምር ኃይል ውስጥም ሊካተት እንደማይችል ሲትገልጽ ቆይታልች።ይህ ሁኔታ ባለበት የአካባቢው የፀጥታ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ በኃላፊነት ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ከመሥራት ወደኋላ እንደማትል ቃል ዐቀባዩ ገልፀዋል።
"ከቀጣናው ተሻጋሪ የሆኑ የሰላም እና አለመረጋጋት ምንጮችን ማድረቅ የሚቻልበት ሂደት ላይ ከሌሎች አጋሮች ጋር ሆና ቁልፍ ሚና መጫወቷን የምትቀጥል ነው የሚሆነው"
ተጀምረው የነበሩ የማሸማገል ጥረቶች የት ደረሱ?
ራስ ገዝ ሶማሊላንድ ባለፈው ወር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አድርጋ ከረጅም ዓመታት በኋላ የተቃዋሚ ተወዳዳሪው ምርጫውን ያሸነፉ ሲሆን የዛሬ ሳምንት ሐሙስ የስልጣን ርክክቡ ይደረጋል። ሶማሊላንድ አዲስ ፕሬዝዳንት መምረጧ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው የመግባቢያ ስምምነት ትምምን ላይ ሊያሳድረው የሚችለው ተጽዕኖ ይኖር እንደሆን የተጠየቁት ቃል ዐቀባዩ ምላሽ አልሰጡበትም።
የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ውዝግብ ለማርገብ በቱርክ ተጀምሮ የነበረው የማሸማገል ጥረት ምን ላይ ደረሰ? የሚለውን እና የኬንያ እና ዩጋንዳ መሪዎች ይህንን ውጥረት ለመቀነስ የማሸማገል ሚና ለመወጣት ውጥን እንደያዙ ስለመሰማቱ ተጠቅሶ ለቀረበላቸው ጥያቄም "ኢትዮጵያ ከሰላም መድረክች የሸሸችበት አጋጣሚ የለም" ሲሉ በመንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ በጎ ምልከታ ስለመያዙ ፍንጭ ሰጥተዋል።
"ዘላቂ የሆነ ሁለቱንም ሀገራት ሊያስማማ ወደሚችል አቅጣጫ ለመሄድ አጋዥ ሚና ስትጫወት ቆይታለች"
ምላሽ ያልተሰጠባቸው ጥያቄዎች
በሌላ በኩል ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በሀገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ማብራሪያ የሰጡት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ "የፕሪቶርያው የግጭት ማቆም ስምምነት ቢተገበር በራሱ ይህ ሁሉ ችግር ባልመጣ ነበር። ይሁንና የፕሪቶርያውን ውል ያዘጋጁ አካላት ውሉ እንዲጣል አድርገው የአማራን ጦር መሳርያ ማውረድ ከሁሉ አስቀድሞ መርጠው ሌላ አዲስ ጦርነት ማወጅ ስለምን አስፈለገ?" ሲሉ ተደምጠዋል። ከሳምንታት በፊት በሶማልያ፣ በግብፅ እና በኤርትራ መካከል የተደረገው ግንኙነት ኢትዮጵያን ለመጉዳት አስመስሎ በተለያዩ አካላት መገለፁን ግን "የተለመድ መረጃ የማዛባት እና የማደናገር ሥራ" መሆኑንም ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ገልፀው ነበር።
ስለዚህ እና ኢትዮጵያ የቀድሞ ታጣቂዎችን የመበተን ሥራ መጀመሯ በተነገረበት ወቅት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተስፋለም ይህደጎ የኤርትራ ሠራዊት አሁንም በትግራይ ክልል ውስጥ መሆሩን መጥቀሳቸው ተገልጾ እውነታው ምን ላይ ነው የሚለውን የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ምንም ከመናገር ተቆጥበዋል። ቃል ዐቀባዩ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ ግን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነቱ በመልካም ሁኔታ ላይ ያለ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በቅርቡ የተቀላቀለችው ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ አባላትን ያቀፈው የብሪክስ ስብስብ ከአሜሪካው ዶላር ጋር ተፎካካሪ መገበያያ ገንዘብ የመጠቀም ውጥን መያዙን መነሻ አድርገው ያንን የሚያደርጉ ከሆነ መቶ በመቶ የቀረጥ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለማስጠንቀቃቸው የኢትዮጵያን አቋም ተጠይቀውም ምላሽ አልሰጡበትም።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ