1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2015

አስተያየት ሰጭዎች ተመላሾቹ ሀገራቸው መግባታቸው ቢያስደስታቸውም ሲሰቃዩ ወደነበሩበት ወደ ሳዑዲ አረብያና ሌሎች የአረብ ሀገራት መመለሳቸው ሊቆም ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሽሬ፣ አላማጣና ኮረም ከተሞች በሚገኙት ቅርንጫፎቹ ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን የመቀበልና የማስቀመጥ አገልግሎት ነው የተጀመረው።

https://p.dw.com/p/4LNgm
Saudi Arabien I  Äthiopien
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያውያን ተመላሾች፤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሽሬ፣ አላማጣና ኮረም አገልግሎት መጀመሩ

በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ የተባሉ ከ1ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ በሳዑዲ አረብያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ አንድ ሺህ 18 ኢትዮጵያውያን ባለፈው ረቡዕ ሀገራቸው መመለሳቸውን አስታውቋል። በመስሪያ ቤቱ መረጃ መሠረት  ከተመላሾች ውስጥ 919ኙ ወንዶች  99ኙ ደግሞ ሴቶች ናቸው። ለሀገራቸው የበቁትን እነዚህን ኢትዮጵያንን ፣ካሚል መሐመድ ፣ማርቆስ ማቲውስ ፣እና ዳን ግሬስፉል በፌስ ቡክ በአጭሩ«እንኳን ደኅን መጣችሁ ብለዋቸዋል። ጽጌ ተክለማርያም እንኳን በሰላም ተመለሳቹ ሲሉ ፣ አብዱ አያሌው ወሎ «እንኳን ለሀገራችሁ አበቃችሁ የሰው ሀገር የሰው ነው ምንም ቢሆን ሀገራችሁ ይሻላችኋል »በማለት የበኩላቸውን ሀሳብ ሰንዝረዋል።ቴዎድሮስ ተካ ኢትዮጵያውያኑ መመለሳቸውን «መልካም ተግባር» ብለውታል። እንኳን ለቤተሰባቸዉ አበቃችሁ ያሉትደግሞ መስፍን ወርቁ ናቸው ።
 «ተመልሰው መሄዳቸው የማይቀር ቢሆንም» ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት መሸሻ ንጉሴ ኢትዮ «ተመልሰው መሄዳቸው የማይቀር ቢሆንም ለጊዜው ካሉበት ችግር መውጣታቸው መልካም ነው በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል። መሸሻ ብቻ ሳይሆኑ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ተመላሾቹ ሀገራቸው መግባታቸው ቢያስደስታቸውም ሲሰቃዩ ወደነበሩበት ወደ ሳዑዲ አረብያም ሆነ ሌሎች የአረብ ሀገራት መመለሳቸው ሊቆም ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ። ከመካከላቸው አንዷ ሉባባ መሐመድ ናቸው።« አልሀምዱሊላህ እንኳን በሰላም ወደአገራቸው ተመለሱ በማለት ሉባባ መልካም ምኞታቸው ከገለጹ በኋላ «ነገር ግን አሁንም ወደዛው ተመልሶ የሚሄደው በጣም ብዙ ነው ማሰቆም ይሄንን ነው።» ሲሉ መፍትሄውንም ጠቁመዋል።  «ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የት ደረሱ? የሚለው ደግሞ ፣አማራ ምን አለ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ ጥያቄ ነው።በላይ ፋሲል መሲም አገር ውስጥ ያሉትስ የት ደርሰው ይሆን የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል። የሁለቱም ጥያቄ ከዚህ ቀደም ከሳዑዲና ከተለያዩ የአረብ ሀገራት የተመለሱት የት ናቸው ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ለማለት ይመስላል።ታዬ ተፈሪ ለሁለቱም የሚሆን የሚመስል መልስ ጽፈዋል።«ተመልሰው እየተሰደዱ ነው ካሉ በኋላ «ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ» ብለውታል።ምን ዋጋ አለው እጥፍ የሚሆኑት ደግሞ ተመልሰው እየሄዱ ነው ብለዋል። ወሎዬው አህመድ በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት «ተመለሱ እየተባለ ሁልጊዜ በሚድያ ይነገራል ግን ሳዑዲ የታሰሩ ዘመዶቻችን 2 አመት እና ከዚያ በላይ  የሆናቸው አሉ» በማለት በተሰደዱበት በሳዑዲ አረብያ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ችላ እንዳይባል አሳስበባዋል። ቶይባ መሐመድ፣ «ማሽ አሏ የቀሩትን አላህ ይድረስላችሁ ብለው በዚህ አጋጣሚ በፈጠራችሁ እዚያ ያሉት መውጫ አጥተው እባካችሁ ዳግም ስደትን አትሞክሩ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ መሆኑን አስታውቋል። ድርጅቱ ይፋ ባደረገው ዘገባ መሠረት በአሁኑ ጊዜ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን፣በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ኢ-ሰብዓዊና አስከፊ በሆነ መንገድ ታስረዋል። አምነስቲ ፣ሳዑዲ አረቢያ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በዘፈቀደ እያሰረች እና በግዳጅ ወደ አገራቸው እየመለሰች መሆኑንም ገልጿል።በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪቃ ቀጠና ሃላፊ ሔባ ሞራዬፍ ስደተኞቹ በእስር ቤቶች የተያዙበት ሁኔታ “የረዥም ጊዜ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት”ሊያስከትል የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል። 
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፌደራሉ መንግሥት ቁጥጥር ስር በሚገኙት በሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነበር። ባንኩ በሰሜን ኢትዮጵያው አለመረጋጋት ምክንያት በነዚህ ከተሞች ሲሰጥ የነበረውን የባንክ አገልግሎት ለረዥም ጊዜ ለማቋረጥ መገደዱን  በዚህ ሳምንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውሶ ነበር። ባንኩ እንዳለው በሦስቱ ከተሞች በሚገኙት ቅርንጫፎቹ ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን የመቀበል አንዲሁም ገንዘብ የማስቀመጥ አገልግሎት መስጠት ነው የተጀመረው። በዚህ መረጃ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አገልግሎቱ መጀመሩ ያስደሰታቸው እንዳሉ ሁሉ ግን አገልግሎቱ በከፊል መጀመሩ ቅር ያሰኛቸው ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ከአስተያየቶቹ ጥላቻን የሚሰብኩ ዘለፋም ያካተቱe ይበዛሉ። እነዚህን ወደ ጎን ትተን የተሻሉ ያልናቸውን ሃሳቦች መርጠናል። 
ዮርዲ አበሻ በፌስቡክ ጥሩ በርቱ ሲሉ በቀለ ተሾመም ጥሩ ነው ብለዋል። ኤፍሬም ገብርኤል ደግሞ ለጅምሩ እግዚአብሔር ይመስገን ካሉ» በኋላ ግን «በእናታችሁ ለህዝቡ ብቻ ብላችሁ በሁሉም ኣከባቢዎች በተቻለ ፍጥነት አስጀመሩት።» በማለት ተማጽነዋል «። ብሌን በርሄ ደግሞ «ከሆነ ጥሩ ነው የመንግስት ስራ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ቅድሚያ አገልግሎት እንዲያገኙ ቢደረግ ደግሞ መልካም ነው።» በማለት የበኩላቸውን ሃሳብ ሰጥተዋል። መሐመድ ሰይድ «የምር በጣም ደስ ይላል።እንኳን ደስ ያላችሁ»ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።ፋንታዬ አሰፋ ግን ቅሬታ አላቸው «ብር ማስገባት እንጂ ማስወጣት አይቻልም ሰው ብር አውጥቶ ካልተጠቀመ ምንኑ ተከፈተ »የሚል። መሐመድ ካሳሁን ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት «ህዝቡ ያስቀመጠውን ገንዘብ አውጥቶ መጠቀም ካልቻለ የባንኩ መከፈት ምንም ጥቅም የለውም» ሲሉ በድሉ በቀለ ጉተማ በፌስቡክ ጥያቄዎች አቅርበዋል። «የነበሩ የባንክ ሂሳቦች ተከፍተው ሰው ገንዘቡ ማውጣት ካልቻለ ምኑ ነው የተከፈተው? ወይስ ለሌላ አካል ነው የተከፈተው? የሚሉ ናቸው ጥያቄዎቹ።ሙሱ ሙሴ  ደግሞ« ነገረን እኮ። ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር የሚላክ ገንዘብ ለማውጣት ነው የሚለው ዜናውን አንብቡ ብለዋቸዋል። መላኩ አየለ አለሙ  «በፓትሮል የተደገፈ ዘረፋ አለ ተብሎ እየተነገረ ባንክ ስራ ጀመረ ማለት ምንድነው? የሚል ጥያቄ በፌስቡክ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ «ወደፊት ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን አገልግሎቱን በማስፋት እና በየደረጃው በሁሉም ቅርንጫፎች አገልግሎት በማስጀመር ደንበኞቹን ለማስደሠት ጥረቱን አንደሚቀጥል አስታውቋል።ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ አንበሳ ባንክ  የተሰኘው የግል ባንክ በሽረ እንዳሥላሴ እና አካባቢው አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ቅርንጫፍ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ቅርንጫፍ ምስል Million Hailesillasie/DW
ከሳዑዲ አረብያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለምዝገባ ተሰልፈው
ከሳዑዲ አረብያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለምዝገባ ተሰልፈው ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ