ኤርትራዊዉ ተጠርጣሪ ስደተኛ አሸጋጋሪ ፍርድ ቤት ቀረበ
ማክሰኞ፣ ጥር 2 2015
ስደተኞችን በማሸጋገር፣ ማሰቃየትና ገንዘብ በመቀበል ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘዉ ኤርትራዊ ተወልደ ጎይቶም ዛሬ ስቮላ-ኔዘላንድስ ፍርድ ቤት ቀረበ።ተወልደ በርካታ የምስራቅ አፍሪቃ ዜጎችን በሰሜን አፍሪቃ በኩል ወደ አዉሮጳ በማስገባት፣ከስደተኞች ገንዘብ በመቀበልና ስደተኞች ላይ ግፍ በማድረስ ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነበር።ኢትዮጵያ ለኔዘርላንድስ አሳልፋ ስጥታዋለች። ተወልደ ጎይቶም በቅርቡ ሱዳን ዉስጥ ከተያዘዉ የሕገ-ወጥ ስደተኞች አሸጋጋሪዎች መሪ ተብሎ ከሚታመነዉ ከሌላዉ ኤርትራዊ ተጠርጣሪ ኪዳኔ ዘካሪያስ ሐብተማሪያም ጋር ግንኙነት እንዳለዉ የዓለም ፖሊስ ድርጅት (ኢንተር ፖል) እና የኔዘርላንድስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታዉቀዋል።ከዘጠኝ ቀናት በፊት የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ስዉር ተከታታዮች ሱዳን ዉስጥ የያዙት ኪዳኔ ዘካርያስ ሐብተማርያም የምስራቅ አፍሪቃ ዜጎችን በማገት፣በመዝረፍ፣ በማሰቃየት፤በመግደልና ወደ ሌላ ሐገር በማሸጋገር ወንጀል እንደሚጠረጠር ኢንተር ፖል አስታዉቋል።የኔዘርላንድስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዋና ጠበቃ ፔትራ ሆክስትራ የተወልደ ጎይቶምን ጉዳይ ከኪዳኔ ዘካሪያስ ሐብተማሪያም ጋር አገናኝተዉ ለመክሰስ ይፈልጋሉ።ተወልደ ጎይቶም ዛሬ ላስቻለዉ የኔዘርላንድስ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአስተርጓሚ በሰጠዉ የእምነት ክሕደት ቃል ግን የተያዘዉ በመልክ ወይም በስም ተመሳሳይነት እንጂ ጥፋተኛ «አይደለሁም» ብሏል።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ