ኤኮዋስ በማሊና ቡርኪናፋሶ ላይ የጣለዉን ማዕቀብ አነሳ
ሰኞ፣ ሰኔ 27 2014ማስታወቂያ
የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ኤኮዋስ) በማሊ እና በቡርኪናፋሶ ላይ ያሳረፈዉን የኤኮኖሚ እና የገንዘብ ማዕቀብ አነሳ። የወቅቱ የኤኮዋስ ኮሚሽነር ታዋቂዉ የአይቮሪኮስት የምጣኔ ሐብት ምሁር ዦንክሎድ ካሲ ቦዉ እንደተናገሩት ኤኮዋስ እዚህ ዉሳኔ ላይ የደረሰዉ ሁለቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ወታደራዊ መሪዎች በየሃገራቸዉ በ 24 ወራት ጊዜ ዉስጥ ምርጫ አካሄደዉ የዴሞክራሲ ሽግግር እንደሚያደርጉ ካሳወቁ እና አዲስ የምርጫ ሕግ በጽሑፍ ለማኅበሩ ካቀረቡ በኋላ ነዉ። የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ኤኮዋስ) ጋና መዲና አክራ ውስጥ ባካሄደዉ ጉባዔ፤ በዙር የሚደርሰዉን የወቅቱን የድርጅቱን የመሪነት ስልጣን ከጋናዉ ፕሬዚደንት ናና አኩፎ-አዶ ተቀብሎም፤ ለኒጀሩ ፕሬዚዳንት ማማዱ ኢሳፉ አስረክቦአል። የምዕራብ አፍሪቃዉ የኢኮኖሚ ባኅበረሰብ በጋናዉ ፕሬዚደንት በአኩፎ-አዶ አመራር ወቅት ሦስት መፈንቅለ መንግስቶችን በመጋፈጡ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ኤኮዋስ ደካማ ሆኗል ብለው ይከራከራሉ።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ