በጋዛ ተኩስ የሚቆመው መቼ ነው?
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20 2016በዩናይትድ ስቴትስ በአውሮጳ ኅህብረት እና በሌሎችም በአሸባሪነት የተፈረጀው ሐማስ እሥራኤል ውስጥ ድንገተኛ የሽብር ጥቃት ሰንዝሮ ከ1400 በላይ ሰዎችን በመግደል 240 ሰዎችን ከጠለፈ በኋላ የእሥራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ ሐማስ ላይ ብርቱ የመልስሶ ማጥቃት ዘመቻ ከፍቶ ቆይቷል ። እንደ ፍልስጥኤም የጤና ምንጮች ከሆነ፦ በእሥራኤል ሐማስ ጦርነት የሟቾች ቁጥር ከ8 ሺህ 5 መቶ መብለጡ ታውቋል ። ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ሕጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ፍልስጥኤማውያን እንደሚገኙበት ተዘግቧል። በጋዛ የተኩስ አቁም የሚደረገው መቼ ነው የሚሉ ጥያቄዎች ከእየ አቅጣጫው እየተነሱ ነው ።
ሦስት ሳምንታት የዘለለው የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነትበዚህ ሳምንት በምድር ጭምር ተጠናክሮ ቀጥሏል። ዩናይትድ ስቴትስ የአውሮጳ ኅህብረት እና ሌሎችም በአሸባሪነት የፈርጁት ሀማስ መስከረም 26 በሰላማዊ እሥራኤላውያን ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ ከ1400 በላይ ሰዎችን ገድሎና በርካቶችን አቁስሎ፤ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑትን ጠልፎ መውሰዱ ይታወቃል ።
እስራኤል በአጸፋው በወሰደችው የአየርና የከባድ ጦር መሣሪያ ጥቃት ደግሞ ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች በአብዛኛው ሕጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ፍልስጥኤማውያን እንድተገደሉ ከስፋራው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ ።
እስራኤል የአጸፋ ርምጃውን ከጀመረች ጀምሮ ወደ ጋዛ ሰርጥ ምግብ ውኃና መድኃኒትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች እንዳይገቡ ከልክላለች። በአሁኑ ወቅት በግብጽ በኩል የተወሰነ የምግብና ሌሎች የርዳታ ቆሳቁሶች እንዲገቡ ተፈቅዷል ቢባልም ጦርነቱ በምድርም በአየርም ተጠናክሮ በመቀጠሉ፤ ርዳታ ለማስገባትም ሆነ ለማሰራጨት አስቸጋሪ መሆኑን የርድታ ሰጪ ድርጅቶች እየገለጹ ነው።
ባለፈው ሳምንት የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች እዚህ ብራስልስ ባክሄዱት ስብሰባ፤ የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ርዳታ እንዲገባ ውሳኔ ቢያስተላለፉም፤ ከዚያ ወዲህ እንደውም እሥራኤል ዘመቻዋን በምድርም አጠናክራ ቀጥላለች። የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተኩስ አቁም ስምነት እንዲደረግ የሚጠይቅ ውስኔ ማስተላለፉ ታውቁል። እስራኤል ግን የተኩስ ማቆም ስምምነት ጥያቄ ከየትም ይምጣ ከየት እንደማትቀበለው ነው ጠቅላይ ሚኒስተር ቤንያም ናታኒያሁ ግልጽ ያደረጉት፤ «አሜሪካ ከኒውዮርክ የአሸዘባሪዎች ጥቃት በሁዋላ የተኩስ ማቆምን ጥያቄ ትቀበለው እንዳልነበር ሁሉ፤ እሥራኤልም መስክረም 26 አሰቃቂ ጥቃት ከፈጸመው ሀማስ ጋር የትኩስ ማቆም ስምምንነት ልታደርግ አትችልም» በማለት በአሁኑ ወቅት የተኩስ ማቆም ስምምነት ማድረግ፤ ለሀማስ እጅ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የደህንነት አማካሪ ጆን ኪርቢይም የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ መወሰኑን ተክትሎ የአሜሪካንን አቋም ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «አሁን የተኩስ ማቆም ጥያቄ ወቅታዊ ነው ብለን አናምንም» በማለት አሁን የተኩስ ማቆሙ የሚጠቅመው ሀማስን መሆኑን ገልጸዋል ።
ቀድሞ የአሜሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የነበሩት ሂላሪ ክሊንተንም በአሁኑ ወቅት በእስራኤልና ሀማስ መካከል የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ የሚያስተላለፉ ወገኖቾ ትክክል አይደሉም ባይ ናቸው፤ «አሁን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ያሚታቀርቡ ወገኖች ሃምስን የማያውቁ ናቸው። ይህ ከሆነ ለሀማስ ትልቅ ስጦታ ነው የሚሆነው። ምክኒያቱም ተኩስ የሚቆምበትን ግዜ እራሱን እንደገና ለማደራጀት ይጠቀምበታል» በማለት እሳቸውም ወቅቱ የተኩስ ማቆም ጥሪ የሚቀርብበት እንዳልሆነ አስታውቀውል።
በብርታኒያም ፖል ቢስቶው የተባሉ የምክት ቤት አባልና ሚንስተር ከመንግስታቸው አቋም በተለየ ሁኔታ የተኩስ ማቆምን ጥያቄ በመግፋትቸው ክስልጣናቸው እንድተነሱ በመገናኛ ብዙሀን ተገልጿል።። ይህም ብዙዎችን በጋዛ የተኩስ ማቆም ጥያቄ ትክክል የሚሆነው መቼ ይሆን? የሚለውን ትያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
መንግስታዊ ያልሆነው የአረብና ብርታኒያ ክውንስል ፕሬዝዳንትና የመካከለኛው ምስራቅ ኤክስፐርት የሆኑት ሚስተር ክሪስ ዶይለ አስተያየት ግን የተኩስ ማቆም ጥያቄ ወቅታዊና አስፈላጊ ሆኖ ሳለ የምዕራብ መንግስታት ይህን ጥያቄ መቃወማቸው የሚያስገርም ነው፤ «የተኩስ ማቆም በአሁኑ ወቅት በጣም አስፈላጊ ነው። የምራብ መንግስታት ይህንን አለመቀበላቸውና መቃወማቸው ግን የሚያስገርም ነው። የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ እርዳታ ማስገባትና ማሰራጨትም አይቻልም በማለት ጦርነቱ ከቀጠለ እንደውም በሃማስ የተያዙት ታጋቾች ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል» በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፤ ምንም እንኳ የዓለም ህዝቦች ከየአቅጣጫው ጦርነቱ እንዲቆም፤ የፍልስጤም ህዝብ የአመታት ችግርም መፍትሄ እንዲያገኝ እየጠየቁ ቢሆንም፤ የምራብ መንግስታት የጥያቄውን ፍትሀዊነት እስካለመኑበትና የእስራኤልመንግስትም በጦረኝነቱ ክቀጥለ፤ ጋዛ ስትወድም፤ ፍልስጤሞችም አሁንም ለሞትና ስቃይ ሲዳረጉና አካባቢውም የዋይትና ለቅሶ ምድር ሲሆን ማየት የማይቀር ነው።
ገበያው ንጉሤ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ