እሥራኤል ከኢራን ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት በኋላ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016እስራኤል፦ የእሜሪካና የአውሮጳ ወዳጆቿ ሃገራትን ምክር ሰምታ ከኢራን ጋር ወደ ቀጥተኛ ግጭት ከመግባት ብትቆጠብ እንደሚሻል ተገለጠ ። የዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሠር ማሪና ኦታዌ ቀጥተኛ ግጭቱ አያዋጣም ብለዋል ። ፕሮፌሠሯ ለዶቼ ቬለ እንደገለጡትም፦ እስራኤል ለኢራን አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት እንደተለመደው የተመረጡ ዒላማወችን ከመምታት ባለፈ ብቻዋን የምትጀምረው ጦርነት ውጤታማ ሊሆን አይችልም ።
እስራኤል የእሜሪካና የአውሮፓ ወዳጅ ሃገራት ምክር ሰምታ ከኢራን ጋር ከሚደረግ ቀጥተኛ ግጭት ብትቆጠብ እንደሚሻል ተገለጠ ። የዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሠር ማሪና ኦታዌ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት እስራኤል ለኢራን አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት እንደተለመደው የተመረጡ ዒላማዎችን ከመምታት ባለፈ ብቻዋን የምትጀምረው ጦርነት ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
ነገሩን በዚህ ይብቃ ብሎ እጅን መሰብሰብ ወይስ አጸፋዊ ምላሽ መስጠት? እስራኤል ከዘነበባት የሚሳእይልና የድሮን ጥቃት በኋላ ገና ምላሽ ያልተሰጠው ጥያቄ ነው። የመጀመሪያ የተባለውን ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትናያሁና የጦር ካቢኔያቸው ገና እየመከሩበት ይገኛሉ።
በዚሁ የኢራን ጥቃትና በቀጣይ የአካባቢው ሁኔታ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምስራቅ ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪና ኦታዌይ እሥራኤል በምዕራቡ ዓለም በተለይም በአሜሪካ ድጋፍ አየር ላይ ያከሸፈቻቸው ሚሳይሎችና ድሮኖች ከወታደራዊ ዕይታ አንጻር እጅግ ውጤታማ ቢሆኑም ከፖለቲካው አንጻር አንዳችም ርምጃ ወደፊት አላራመዷትም ። እስራኤል ችግሩን ለመቅረፍ የሚችል ግንኙነትና አልጀመረችም፤ አለያም አላደሰችም። የጋዛ ጦርነት የመቆም አዝማምያ ዐላሳየም። ሐማስ ትግሉን የማቆም ሐሳብ የለውም፣ ዌስት ባንክም እንዲሁ ትርምስ ውስጥ ነው፣ እናም እንደ ፕሮፌሰሯ ገለጻ እስራኤል በፖለቲካው አውድ እዛው በገባችበት ውጥንቅጥ ውስጥ ናት።
ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካንም ሆኑ ሌሎች ሃገራት እስራኤል ወደ ጥቃት ርምጃ ብትሄድ ድጋፍ እንደማያደርጉ ዐስታውቀዋል። የእስራኤልና ፍልስጤምን ችግሮች ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ኳታር ከአሜሪካ ጋር ተባብራ ደፋ ቀና ማለቷ የተለመደ ቢሆንም፤ ሌሎቹ የዓረብ ሃገራት ግን እጃቸውን ማስገባት እንደማይፈልጉ ፕሮፌሰር ማሪና ገልጸዋል። በተለይም የጋዛ ጦርነት የተዳፈነውን የፍልስጤም ደጋፊነት መንፈስ በአረቡ ዓለም ሕዝብ ዘንድ መልሶ እንዲያንሰራራ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
ለኢራን የሚሳይል ጥቃት የእሥራእኤል ምላሽ ምን እና መቼ ይሆን የሚለውን ለመገመት ያዳግታል ያሉት ፕሮፌሰሯ ቀጥተኛ ጥቃት ሳይሆን በተመረጠ ዒላማ ወይም ግለሰብ ላይ የሚወሰድ ርምጃ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል። ያም ሆኖ የትኛውም ጥቃት እሥራእኤል ብቻዋን የምትወስደው ከሆነ የማትወጣው ፈተና ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ፕሮፌሰር ማሪና ገልጸዋል። ለዚህም እሥራኤል የወዳጆቿን የአሜሪካንን እና የምዕራባውያን ምክር ይሰሙ ዘንድ ምኞታችው እንደሆነ ጠቁመዋል ።
ለበርካታ ዓመታት እሥራኤል የኢራንን የኑክሌር ተቋማት ታጠቃለች የሚል ስጋት እንደነበረ የገለጹት ፕሮፌሰሯ ይሄው ዓላማቸውም አሜሪካንን ወደ አካባቢው ግጭት ውስጥ ለመክተት የታለመ እንደሆነ ጠቁመዋል። ፕሮፌሰር ማሪና አሁን እሥራኤል ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ግን አሜሪካም ሆነ የአረቡ ዓለም እጃቸውን እንደማያስገቡ ያሳዩት ግልጽ አቋም ከቀጥታና ሰፊ ግጭት እንድትታቀብ የሚያሳስብ እንደሆነ ገልጸዋል።
ያም ሆኖ እስራኤል ራሷን የቻለች ነጻ ሃገር ፣ ብሎም ብዙ ጊዜ ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ወዳጅ ሃገራት በሚስጥርም ሆነ በአደባባይ የሚሰጧትን ምክርና ማሳሰቢያዎች አለመቀበሏ የተለመደ ስለሆነ ምላሿን ከወዲሁ ለመገመት አስቸጋሪ ነው ብለዋል። የኢራን ጥቃት ግን በእሥራኤል ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋትን ለማድረስ የታሰበ ሳይሆን ኢራን ጥቃት የመፈጸም አቅምና ቁርጠኝነት እንዳላት የማሳየትን ግብ የሰነቀ እንደሚመስል ፕሮፌሰሯ ገልጸዋል ። ዩናይትድ ስቴትስ እና ተገዳዳሪወቹ ቻይና እና ራሽያ በዚህ ቀጠናዊ ግጭት ውስጥ መግባት እንደማይጠቅማቸው የገለጹት ፕሮፌሰር ማሪና ኦታዌይ ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ከደረሰ ግን እስራኤልን ተቃውመው ድምፅ እንደሚሰጡ መላምታቸውን አስቀምጠዋል።
አበበ ፈለቀ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ