1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እቴጌ፤ ስለጡት ካንሰር መረጃ የሚሰጠው መተግበሪያ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 24 2015

በኢትዮጵያ በየዓመቱ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በጡት ካንሰር የሚያዙ ሲሆን ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በጡት ካንሰር ሳቢያ በየዓመቱ ይሞታሉ።ያም ሆኖ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው።ወጣቷ የጤና ባለሙያ ቤቴል ሳምሶን የህንን ችግር ለመቀነስ እቴጌ የተባለ በጡት ካንሰር ላይ መረጃ የሚሰጥ መተግበሪያ ሰርታለች።

https://p.dw.com/p/4Iv3E
Äthiopien | Dr. Bethel Samson | Etege App
ምስል Dr.Bethel Samson

መተግበሪያው በግንዛቤ እጥረት በጡት ካንስር የሚሞቱ ሰዎችን ይታደጋል


በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅምት፤ በየዓመቱ በጡት ካንሰር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሰጥበት ወር ነው። የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በጡት ካንሰር ላይ መረጃ በሚሰጥ አንድ መተግበሪያ ላይ ያተኩራል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር በሽታ በሴቶች ላይ ቀዳሚው የካንሰር በሽታ ነው።ያም ሆኖ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከጡት ካንሰር ጋር በተያያዘ የቅርብ ዘመዶቻቸውን በሞት ባጡ 800 በሚሆኑ ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል በጡት ካንሰር ህይወታቸውን ያጡ ህሙማን ስለበሽታው  እና ምልክቶቹ ብዙም የሚያውቁት ነገር አልነበረም።የእቴጌ መተግበሪያ መስራች እና በጥቁር አንበሳ የሕክምና ትምህርት ቤት የዘንድሮ ተመራቂዋ ዶክተር ቤቴል ሳምሶን እንደምትለው ችግሩ በከተማም ተመሳሳይ ነው። «ትውልዴም እድገቴም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው።በኛ አካባቢ ብዙ አክስስቶቻችን ጎረቤቶቻችን በዚህ በሽታ ተጠቂ ነበሩ።እና አንዳንዶቻቸው አሸንፈውት ድነው አሁንም ከኛ ጋር አብረውን አሉ።አንዳንዶቻቸው ግን የሉም።ይህንን እና ከብዙ ሰው እናቀው ነበር። ከሩቅ ሳይሆን ከቅርብ ከኛው ከምናየው ብዙ የአዲስ አበባ ሴቶች በበሽታው ይጠቃሉ። እና ብዙ ግንዛቤ የለም።ካንሰር ምን እንደሆነ፣ቸክ ማድረግ ምን እንደሆነ  መቼ መደረግ እንዳለበት ብዙ ሰው ግንዛቤ የለውም።እኛ ጋ የሚመጡት ብዙ ጊዜ የከተማ ሴቶች ናቸው። አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ሴቶች ስለሚያዙ ነገር ግን እነሱ ራሱ ወይ በዘር የሚመጣ ነው የሚመስላቸው፣ወይ ደግሞ የፈረንጅ በሽታ አድርገው ነው የሚያስቡት ካንሰርን።እኛ ሀገር ውስጥ ያለ አይመስላቸውም ካንሰር ሲባል»በማለት ገልፃለች። ነገር ግን የጡት እና የማህፀን ካንሰር በኢትዮጵያ በአብዛኛው ሴቶችን የሚያጠቁ በሽታዎች መሆናቸውን ተናግራለች።

Äthiopien | Dr. Bethel Samson | Etege App
ዶ/ር ቤተል ሳምሶንምስል Dr.Bethel Samson

ይህንን ችግር በሰፊው የተመለከተችው በህክምና ትምህርት ቤት ቆይታዋ  በጡት እና የማሕፀን ጫፍ ካንሰር  ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ «ደብል ኢምፓክት» በተባለ መርሃ ግብር ውስጥ ተሳታፊ በነበረችበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ስለጡት እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር በተለያዩ ተቋማት ግንዛቤ ትሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ጡታቸውን ራሳቸው እንዲፈትሹ አንዳች ጥርጣሬ ከገባቸውም ወደ ህክምና ተቋማት ሄደው የአልትራ ሳውንድና የማሞግራፊ ምርመራዎችን እንዲያደርጉ ጭምር  እሷ እና ጓደኞቿ ምክር ይለግሳሉ።በዚህ ወቅት ስለበሽታው  የተመለከተችው የግንዛቤ እጥረት ታዲያ እቴጌ የተባለ በጡት ካንሰር ላይ መረጃ የሚሰጥ መተግበሪያ ለመስራት መነሻ ሆኗታል።
ይህንን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተዘጋጀ የማስተማሪያ ፅሁፍ አለመኖርም እቴጌ መተግበሪያን ለመስራት ሌላው እና ሁለተኛው ምክንያቷ ነው።
መተግበሪያው ለአጠቃቀም ቀላል ሆኖ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጄ  ሲሆን ከጎግል ፕሌይ በነፃ ማውረድም ይቻላል።ይህ መተግበሪያ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ከተጫነ አንዲት ሴት ራሷን  በመፈተሽ ጤናዋን እንድትጠብቅ  በየወሩ የሚያስታውስ እና  የጡት ካንሰር ከተከሰተም ሳይባባስ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንድትችል ይረዳል።ስለበሽታው ቅድመ ጥንቃቄ፣  ስለምልክቶቹ፣ ስለህክምናው እንዲሁም በጊዜ ከታከሙ መዳን እንደሚቻልም ጭምር ዝርዝር መረጃ ይሰጣል።ይህም እንደ ዶክተር ቤቴል በኢትዮጵያ የኬሞቴራፒ አገልግሎት ሰጪ የጤና ተቋማት አነስተኛ በመሆናቸው  ወረፋ በመጠበቅ  በበሽታው የሚከሰት ሞትን እና ለህክምና የሚወጣውን ወጭ የመቀነስ ጠቀሜታዎች አሉት።

Äthiopien | Dr. Bethel Samson | Etege App
ምስል Dr.Bethel Samson

ዶክተር ቤቴል እንደምትለው መተግበሪያውን ለመስራት ስታስብ  ሙያዋ ህክምና በመሆኑ  ዕቅዷን ለማሳካት ያመራችው በቴክኖሎጅ ወደሚያግዛት የሶፍትዌር ኩባንያ ነበር።በኩባንያው ስልጠና ከወሰደች በኋላም እቴጌ የተባለች ኢትዮጵያዊት ሴት ገፀባህሪ በመፍጠር የህክምና መረጃው በዚህች ገፀባህሪ በኩል እንዲተላለፍ  ተደርጎ መተግበሪያው ተሰራ።
በዚህ ሁኔታ በ2019 ዓ/ም የተሰራው እቴጌ መተግበሪያ በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ጡት ካንሰር መረጃ ለማግኜት እየተጠቀሙበት ሲሆን፤ ከህክምና ባለሙያዎች እና ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጋር በመሆን መተግበሪያውን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ማቀዷንም ተናግራለች። 
የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን  ተወልዳ ባደግችበት አዲስ አበባ ከተማ ናዝሬት ስኩል በተባለው የሴቶች ትምህርት ቤት የተከታተለችው ወጣቷ የህክምና ባለሙያ ቤቴል፤ እሷ ያገኘችውን ዕድል ያላገኙ ሴቶችን መርዳት እና የሴቶችን ሕይወት የሚያሻሽል ስራ መስራት የሁልግዜ ምኞቷ ነው።ይህንን ምኞቷን ለማሳካትም በቅርቡ «ሳባ» የተሰኜ በሴቶች ጤና ላይ የሚያተኩር  ሌላ መተግበሪያም አገልግሎት ላይ ለማዋል ዝግጅቷን አጠናቃለች።«ሳባ የስነተዋልዶ ጤና ላይ የሚሰራ ነው።የወር አበባ ጤና እና ንፅህና አጠባበቅ ላይ በተጨማሪም ቤተሰብ ምጠናና የአባለዘር በሽታዎች ላይ ለመስራት አቅደን የተነሳነው,።የቤተሰብ ምጣኔ ለሚጠቀሙ ሴቶች ማስታወሻ አለ።በአማርኛ የቀን መቁጠሪያ ካሌንደርም አለ በተጨማሪ በእንግሊልዝኛ በአማርኛ በትግርኛ እና በኦሮምኛ በአራት ቋንቋዎች በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ መረጃ ይሰጣል።»በማለት ስለመተግበሪያው አገልግሎት ገልፃለች።በቴሌግራም አማካኝነትም እሷ እና ጓደኞቿ ሌሎች  ጤና ነክ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ  ጨምራ ገልፃለች።

Äthiopien | Dr. Bethel Samson | Etege App
ዶ/ር ቤተል ሳምሶንምስል Dr.Bethel Samson

እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም በሴቶች ላይ በምርመራ ከተረጋገጡ  የካንሰር በሽታዎች መካከል የጡት ካንሰር  30% በመቶ ያህሉን ይይዛል ። በ 2021 ዓ/ም ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ ከሚያዙ ዓመታዊ የካንሰር ህሙማን መካከል 12 በመቶውን ይይዛል። በግንዛቤ እጥረት ሳቢያ በአብዛኛው በዚህ በሽታ የሚሞቱትም በታዳጊ ሀገራት የሚገኙ ሴቶች ናቸው። 
በኢትዮጵያም የጡት ካንሰር በአዋቂ ሴቶች ላይ ቀዳሚው የካንሰር አይነት ሲሆን፤ከአምስት የካንሰር ህሙማን መካከል አንዱ  የጡት ካንሰር ነው። ማለትም ከአጠቃላይ የካንሰር ህሙማንም የጡት ካንሰር 32 በመቶ ያህሉን ይይዛል። በሀገሪቱ በየዓመቱ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በጡት ካንሰር የሚያዙ ሲሆን ከዘጠኝ  ሺህ በላይ  /9061/ ሰዎች ደግሞ በጡት ካንሰር ሳቢያ በየዓመቱ ይሞታሉ። ይህንን እና ሌሎች በግንዛቤ እጥረት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ዶክተር ቤቴል እንደምትለው ለወደፊቱ በህብረተሰብ ጤና ላይ በማተኮር የመስራት ዕቅድ አላት።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ